1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱት የትግራይ 1.2 ሚልዮን ሕጻናት እና አዳጊዎች

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሰኞ፣ መጋቢት 29 2017

በትግራይ 1.2 ሚልዮን ሕጻናት እና አዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በትግራይ ከጦርነቱ በኋላ ጭምር የቀጠሉት ሰብአዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲሁም መፍትሔ ያላገኘው የተፈናቃዮች ጉዳይ አሁንም በትግራይ ሚልዮኖች ከትምህርት እንዲርቁ ማድረጉ ተገልጿል።

የትግራይ ክልል የትምህርት ቢሮ
የትግራይ ክልል የትምህርት ቢሮምስል፦ Million Hailesillasie/DW

ወደ ትምህርህርት ገበታ ያልተመለሱት የትግራይ 1 ነጥብ 2 ሚልዮን ህፃናት እና ታዳጊዎች

This browser does not support the audio element.

 በዚህ ዓመት በትግራይ 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ይገባሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በትምህርት ያሉት 1 ነጥብ 3 ሚልዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው ተብሏል።

የትግራዩ ጦርነት ተከትሎ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኃላ በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ዳግም ቢጀመርም፥ ይሁንና በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ የሚገኙ ህፃናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች አሁንም ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸው የክልሉ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። የትግራይ ትምህርት ቢሮ እንደሚለው፥ በያዝነው ዓመት በትግራይ 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርት ሊገቡ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ወደ ትምህርት የገቡ ግን ከ1 ነጥብ 3 እንደማይበልጥ ይገልፃል። አሁንም በርካታ ተፈናቃይ በመጠልያዎች እየኖረ መሆኑ፣ አስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ሁኔታ መቀጠሉ፣ በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ የደረሰ ውድመት ተከትሎ በተፈጠረ አስቸጋሪ ሁኔታ እና ሌሎች ጦርነቱ ያስከተላቸው ጥፋቶች በትግራይ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ውጭ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።ትግራይ ክልል 60 ከመቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ተገለጠ

የትግራይ ትምህርት ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ «በዚህ ዓመት ወደ ትምህርት ገበታ ሊመጡ ይጠበቁ የነበሩ ሕጻናት፣ አዳጊዎች እና ወጣቶች ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሲሆኑ፥ ከነዚህ መካከል ወደ ትምህርት ገበታ የመጡት 1 ነጥብ 3 ሚልዮን ብቻ ናቸው። የፕሪቶርያው ውል በሙሉእነት ተግባራዊ ባለመሆኑ፣ ጦርነቱ በፈጠረው ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ቀውስ እና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚልዮን በላይ ህፃናት አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው» ብለዋል።

መቀሌ፤ ካላሚኖ ልዩ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትምስል፦ Kallamino Special High School

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በትግራይ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ሰፊ ክፍተት እየተስተዋለ መሆኑም ይገለፃል። የትግራይ ትምህርት ቢሮ እንደሚለው በትግራይ በገጠር እና ከተማ እንዲሁም በግል እና መንግስት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ሰፊ ልዩነት አላቸዉ። ዶክተር ኪሮስ፤

«በትምህርት ተደራሽነት ይሁን በተማሪዎች ውጤት በገጠርና ከተማ፣ በመንግስት እና ግል ትምህርት ቤቶች ትልቅ ልዩነት እየተመለከትን ነው። ይህ ችግር በትኩረት በአጭር ግዜ ካልተፈታ በቀጣይነት በማሕበረሰባችን ላይ ሰፊ ክፍተት የሚፈጥር ስለሆነ የትምህርት ፍትሓዊነት ማረጋገጥ የሁሉም አጀንዳ መሆን አለበት» ሲሉ አክለው ገልፀዋል። በትግራይ የመምህራንና መንግሥት ሠራተኞች የ18 ወራት ውዝፍ ደሞዝ አቤቱታ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት በመቐለ በተደረገ ሥነ-ስርዓት በትግራይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሆነው ጭምር የመማር ማስተማር ስራቸው ያስቀጠሉ እንዲሁም ምስጉን የተባሉ አስተማሪዎች እና የትምህርት አመራሮች የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በሌላ በኩል በትግራይ የሚገኙ መምህራን የጦርነቱ ወቅት የ17 ወራት ደሞዛቸው መንግስት እንዲከፍላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ያለ ሲሆን ይሁንና መንግስት ምላሽ አልሰጠንም በማለት በክልሉ መምህራን ማሕበር በኩል በፌደራሉ መንግስት፣ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የትግራይ ትምህርት ቢሮ ላይ ክስ መመስረታቸው መዘገባችን ይታወሳል። የትግራይ መምህራን ማሕበር በመንግስት አካላት ላይ የጀመረው ክስ በትግራይ ከፍተኛ ፍርድቤት እየታየ ያለ ሲሆን በመጪው ሚያዝያ ወር መጀመርያ ለብይን መቀጠሩም ከማሕበሩ ሰምተናል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW