ወደ ትግራይ የሚጓዙ የዉጪ መንገደኞች የገጠማቸዉ ክልከላ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 5 2017
ወደ ትግራይ በሚጓዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችና ሌሎች መንገደኞች በአዉሮፕላን ማረፊያ የጎዞ ክልልከላና መስተጓጎል እየገጠማቸው መሆኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ። በተለይም ከግንቦት 2 ቀን ወዲህ የጉዞ ክልከላ መኖሩን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጾ፣ ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራሉ መንግስት አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑ አስታዉቋል።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል
የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በትላንትናው ዕለት ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓመተምህረት፥ ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ቱሪዝም ሚኒስቴር የፃፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ወደ ትግራይ ለጉብኝት የሚጓዙ ቱሪስቶች ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች ያሏቸው የውጭ ዜጎች ወደ ክልሉ እንዳያመሩ በኤርፖርቶች ክልከላ እየተደረገባቸው መሆኑ ያመለክታል። ጦርነቱ እንዲሁም በቅርቡ በነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት ወደ ትግራይ የሚደረጉ ጉዞዎይ ተደናቅፈው እንዲሁም የቱሪስቶች ቁጥር ቀንሶ መቆየቱ የሚያነሳው የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፥ በቅርቡ ግን የተወሰነ የቱሪስቶች እንቅስቃሴ መታየት ጀምሮ እንደነበረ ጨምሮ ይገልፃል። ይሁንና ካለፈው ሳምንት ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓመተምህረት ጀምሮ ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ቱሪስቶች እና የውጭ ፕሮጀክቶች ባለድርሻዎች ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ የጉዞ ክልከላ በኤርፖርቶች እንደገጠማቸው የክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
የተበላሸው የቱሪዝም ምስል ለመመለስ ጥረት በሚደረግበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት ክልከላ 'አሳዛኝ እና የህዝቡ ሞራል የሚጎዳ' ነው ያለው የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከዚህ በተጨማሪም የሚፈለገው ሰላምና መረጋጋት እንዳይመጣ የሚያደረግ ሲል ኮንኖታል። ለዶቼቨሌ የተናገሩት የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ሃይላይ በየነ ይህ ችግር ለመፍታት ከፌዴራሉ መንግስት የሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ብለዋል። እንደ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ በትግራይ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ በአወንታ የሚታይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መኖሩ የሚገልፅ ሲሆን፥ በተለይም ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ተያይዞ በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸው ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪ በ2017 ዓመተምህረት 9 ወራት ብቻ ከ9 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸው የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሐላፊ አቶ ሃይላይ በየነ ተናግረዋል። ፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ የተለያዩ ሀገራት በየወቅቱ የሚያወጧቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች እና ክልከላዎች የትግራይ የቱሪዝም ዘርፍ ፈተናዎች መሆናቸው ተነግሯል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ