1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወደ ከተሞች የሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት የቤት አቅርቦት ቀውስ ፈጥሯል-ተመድ

እስክንድር ፍሬው
ዓርብ፣ ሚያዝያ 23 2018

ጊዜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2030፣እቅዱ ደግሞ ሰዎች ደረጃውን የጠበቀ ፣ደህንነቱ አስተማማኝ የኾነና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። የተመድ ካስቀመጣቸው 17 ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች አንዱ ነው።

Eco Africa | DW | Guinea
ምስል፦ DW

 


ጊዜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2030፣እቅዱ ደግሞ ሰዎች ደረጃውን የጠበቀ ፣ደህንነቱ አስተማማኝ የኾነና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካስቀመጣቸው 17 ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች አንዱ ነው።በአፍሪካከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት፣የኪራይ ውድነትና የዋጋ መናር ግን ሲሻሻል አልታየም።

ከከተማ ወደ ገጠር የሚደረግ ፍልሰት

አካታች፤ ደህንነታቸው የተጠበቀና ቀጣይነት ያላቸው ከተሞችና ማህበረሰቦችን በመፍጠር ላይ በማተኮር የሚሰራውና ባጭሩ "ዩኤን ሐቢታት" ተብሎ የሚጠራው የተባበሩት መንግስታት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ፣አናክላውዲያ ሮዝባች የዚህ አንዱ ምክንያት ወደ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት መኾኑን ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።

"አፍሪካን በተመለከተ ያለው ነጥብ ምንድን ነው፣ አፍሪካ አሁንም በከተሜነት መስፋፋት ላይ ናት። ደቡብ ምስራቅ እስያን ጨምሮ አፍሪካ፣ከተሜነት በጣም በፍጥነት እየተስፋፋባቸው ካሉ የአለም አካባቢዎች አንዷ ናት።እና በሚቀጥሉት ሃያ አመታት፣በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ-ከ600-900 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ከተሞች በተለይም ወደ አዳዲስ ከተሞች ይፈልሳሉ።ወደ ከተሞች የሚጎርፈውን ሰው ቁጥር በተመለከተ የምንገምተው ይሄንን ነው" ብለዋል።

ይህ ማለት ደግሞ፣መጀመሪያውንም የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ያለባቸው ከተሞች፣በብዛት የሚመጣውን ይሄንን ቁጥር ማስጠለል አለባቸው ማለት እንደኾነ ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።ወደ ከተሞች የሚጎርፉት ሰዎች ከገጠር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ከተሞች የሚመጡ ሊኾኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

ይኼም ሆኖ፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ውድነት ችግር አለምአቀፍ ገጽታ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል። እኛ የምንጠራውም "አለምአቀፍ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ቀውስ" በማለት ነው ሲሉ ነው የገለፁት።

አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የልማት ግብ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትና የአፍሪካ ሕብረት በከተሞች ላይ ያተኮረውንና 11ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተቀመውን ይሄንን ግብ ጨምሮ ከ17ቱ ግቦች በአምስቱ ላይ ያለውን አፈጻጸም አዲሰ አበባ ውስጥ ገምግመዋል። ከቤት ጋር የተያያዘው ግብ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኘ መገለጹን ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2030 ለማሳካት የታቀዱትን 17 የልማት ግቦች ይፋ ያደረገው በ2015 ዓ/ም ነው።ምስል፦ Getty Images/AFP/S. Jensen

"ዛሬ ይፋ እንደተደረጉት ሪፖርቶች ከኾነ፣አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት የልማት ግቦች ጋር ነው የሚመደበው-መሻሻል አለማሳየት ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውን አካሄድ መቀየር ከሚያስፈልግባቸው ግቦች መካከል- እና አስፈሪ ነው" ብለዋል።

የመኖሪያ ቤት የሁሉም ግቦች መሠረት ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2030 ለማሳካት የታቀዱትን 17 የልማት ግቦች ይፋ ያደረገው በ2015 ዓ/ም ነው።
ከተሜነት በአፍሪካ ግን አሁንም አስቸጋሪ ነው። በተለይ የአፍሪካ አገራት መዲናዎች ነዋሪዎች፣ ከገቢያቸው አብዛኛውን ክፍል ለቤት ኪራይ እንዲያወጡ ይገደዳሉ፣ አቅምን ያገናዘበ ቤት ማግኘትም ፈተና ኾኗል።ሮዝባች እንደሚችሉት የሌሎቹ የልማት ግቦች መሳካት፣ዜጎች አስተማማኝ የኾነና የኢኮኖሚ አቅምን ያገናዘበ ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው።

"በመኖሪያ ቤት ላይ መስራት የሁሉም ዘላቂ የልማት ግቦች ጣሪያ መኾኑን በተደጋጋሚ እናገራለሁ። ምክንያቱም ሰዎች በቂየመኖሪያ ቤት ከሌላቸው ፣ ልጆች እንዴት በቤታቸው ጤነኛ ኾነው ይኖራሉ? ተመልሰው የሚመጡበትና የቤት ስራቸውን የሚሰሩበት ቤት ከሌላቸው እንዴት ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ?" በማለት ጠይቀዋል።

የ2030ን የልማት ግብ ከማሳካት አንጻር አሳሳቢ ቢኾንም፣ከፖሊሲ አንጻር ግን የተሻሉ ስራዎች እንዳሉም ዋና ዳይሬክተሯ ይናገራሉ። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትና የአፍሪካ ሕብረት በከተሞች ላይ ያተኮረውንና 11ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተቀመውን ይሄንን ግብ ጨምሮ ከ17ቱ ግቦች በአምስቱ ላይ ያለውን አፈጻጸም አዲሰ አበባ ውስጥ ገምግመዋል።ምስል፦ Eskinder Frew/DW

"በአፍሪካ ከብሔራዊ የከተማ ልማት እቅድ አንጻር መሻሻል አለ። ይህ ከልማት ግቦቹ ስኬት ማሳያዎች አንዱ ነው።ስለዚህ ከመዋቅር አንጻር መሻሻል አለ። የከተሜነት መስፋፋት ስላለው ተጽዕኖና የከተሜነትን መስፋፋት የወደፊት እጣ ፋንታ በተመለከተም መሻሻል አለ።በብሔራዊ ደረጃ ትክክለኛ ፖሊሲ ከማውጣት አንጻርም ያልተጠናቀቀ ስራ አለ። ከአተገባበር አንጻር ግን ቀጠናው አሁንም ወደ ኋላ ቀርቷል" በማለት አብራርተዋል።

ዜጎች ደረጃውን የጠበቀ ፣ደህንነቱ አስተማማኝ የኾነና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው መስራት እጅግ አስፈላጊ መኾኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።

እስክንድር ፍሬው
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW