1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቶችን በሀገራዊ ውይይቱ ለማሳተፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 3 2015

በ5 ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱና ወጣቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩ 7 ሀገር በቀል የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ወጣቶች ኢትዮጵያ በጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ እና እንዲነቃነቁ ለማድረግ ዛሬ ጥምረት መሠረቱ። የተማረም ያልተማረም፣ ሥራ ያለውም ሥራ ያጣም፣ በበጎ ሥራም፣ በጥፋትም የሚሳተፍ ወጣት ይገኛል ብለዋል ድርጅቶቹ።

Treffen Youth Civil Society for National Dialogue
ምስል Solomon Muche/DW

በብሔራዊ ምክክሩ የወጣቶች ተሳትፎ

This browser does not support the audio element.

በአምሥት ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና ወጣቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩ ሰባት ሀገር በቀል የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ወጣቶች ኢትዮጵያ በጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ እና እንዲነቃነቁ ለማድረግ ዛሬ ጥምረት መሠረቱ። በኢትዮጵያ ውስጥ የተማረም ያልተማረም፣ ሥራ ያለውም ሥራ ያጣም፣ በበጎ ሥራም ፣ በጥፋትም ውስጥ የሚሳተፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ይገኛል ብለዋል ድርጅቶቹ። ወጣቶች ለግጭት እና ጦርነት የጥፋት ድርጊቶች የሌሎች መጠቀሚያ ሲሆኑ የመታየታቸውን ያህል ሀገራዊ ምክክሩን በመሰሉ በጎ ንቅናቄዎች ውስጥ ባለቤት እንዲኑ ማስቻል እነዚህ ድርጅቶች የተሰባሰቡበት ምክንያት ነውም ተብሏል።

ወጣቶችን ብቻ የተመለከተ ሥራ ላይ አተኩረው የተሰማሩ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት የዛሬው ጥምረት የመመስረት ውይይት በገጠርና በከተማ የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮን የሚገመቱ ወጣቶችን በብሔራዊ ምክክሩ የማሳተፍ ግብ ያለው ነው። ኅዳር ላይ ይጀመራል በተባለው ይህ ሀገራዊ ውይይት ላይ ወጣቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ንቅናቄ የመፍጠር ታሪክ ውስጥ በነበራቸው ድርሻ ልክ ሊወከሉና የነገ ሀገር ተረካቢዎች የሚለው የተለመደ ብያኔ የዛሬ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ የተገለሉ እንዳይሆኑ የማድረግ ውጥን ይዟል። አቶ ብሩክ ይርጋለም ጣምራ ለማሕበራዊ ልማት የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እና የዚህ ጥምረት ጊዜያዊ አስተባባሪ ስብስብ ሰብሳቢ ሆነው ይሠራሉ።
«ወጣቶች በደንብ አድርገው ተሳትፈው በሀገራችን ብሔራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ ተሳትፈው ባለቤቶችም ጭምር እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ይህንን መድርክ እየፈጠርን ያለነው» ብለዋል።ለዘላቂ ሰላም የሲቪል ማኅበረሰቡ ሚና

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሲቪል ማሕበራት የወጣቶች መዋቅር በብሔራዊ ውይይቱ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከማድረግ የሚገድባቸው ችግሮች ታይተዋል ብሏል። ይህንን ለመቅረፍ ምክር ቤቱ ከወጣቶች ጋር በመተባበር «የወጣቶች የሲቪል ማህበራት ሕብረት ለሀገራዊ ውይይት» እንዲመሰረት አስተባብሯል። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ።
«ለብዙ ግጭቶች ለጦርነቶች ዋነኛ ተዋናዮች ወጣቶች ናቸው። በቂ መረጃ እና ተሳትፎ ካለማግኘት አንፃር በቀላሉ ለተለያየ ፍላጎት መዋያ ይሆናሉ። ነገር ግን በእንደዚህ ያለ ቁምነገር ወደፊት ስናመጣቸው እና ስናሳትፋቸው ግጭትን ሊፈጥሩ ወደሚችሉ ነገሮች መግባታቸው ይቀንሳል» ብለዋል።የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ቃለ መጠይቅ

በዚህ ሀገራዊ ምክክር ውስጥ ወጣቱ ቢሳተፍ ሀገር ምን ያተርፋል፣ ባይሳተፍስ ምን ይቀራል ፣ ምን ለውጥስ ይኖራል ብለን የጠየቅናት ወጣት «የወጣቱ አጀንዳ የተጣለ አጀንዳ እንዳይሆን ያደርጋል» ትላለች። ብሔራዊ ምክክሩ ወጣትቱን በሂደቱ ማካተት ግዴታው መሆኑን ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ወጣት መኖሩ መዘንጋት እንደሌለበት እና ተሳትፏቸው ዝቅተኛ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል የሚሉት የዚህ ጥምረት አማካሪ ዶክተር ይታገሱ ዘውዱ ከምንም በላይ የገለልተኛነቱን ወሳኝነት አንስተዋል።

ወጣቶችን በብሔራዊ ውይይት ለማሳተፍ የተካሄደው ጉባኤ በከፊልምስል Solomon Muche/DW

«ወጣቶች እንደ ጥፋት አጥፊም ፣ ሰለባም ተደርገው ነው የሚታዩት። ይሄ ከሆነ ለምንድን ነው ለሰላምና ለሀገራዊ ምክክር ብቁ የማይሆኑት የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል። ስለዚህ በሚመለከታቸው ጉዳይ ላይ ዛሬ ላይ ተወክለው መምጣት አለባቸው» ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን «ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ ፣በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ» ማስፈለጉ መገለፁ ይታወሳል። 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW