1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዉይይት በኢትዮጵያ ሰላም፣ግድጭትና ግድያ ላይ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 13 2015

ድርድሩን ከኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አኳያ በፈተሹበት በዚሁ የጥናት ጽሑፋቸው፣ፕሮፌሰር ይሌ ኢትዮጵያውያንን ይከፋፍላል ያሉት ሕገመንግስት ጋር የተጣጣመ የሰላም ሂደት፣ እንዴት የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ይቻለዋል ሱሉ ሞግተዋል።

Logo Vision Ethiopia

ርዕይ ለኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

             

ርዕይ ወይም ቪዥን ኢትዮጵያ የተሰኘዉ ርዕሰ መንበሩን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገ ድርጅት 11ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ዉን ሰሞኑን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ አድርጓል። የዘንድሮው ጉባዔ፣ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመዉን ስምምነትና  በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገዉን ግጭት፣ጥቃትና ግድያን አንስቶ ተነጋግሯል።

"ቪዥን ኢትዮጵያ ከማንም ያልወገነ፣ከመንግስት ወይም ከፖለቲካ ድርጅቶች ያልወገነ የሙያተኞችና የምሁራን ስብስብ ነው።በየወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላላቅ የሆኑ የፖለቲካ ፣የማኀበራዊና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እያነሳ በምሁራኖች በባለሙያዎች ተጠንተው የሚቀርቡ ነገሮችን ለሕዝብ እንዲዳረሱ ማድረግ ነው።"

የራዕይ ለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታቸው በጋሻው ጉባዔውን አስመልክቶ ለዶይቸ ቨለ የተናገሩት ነበር።እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ ፣በኢትዮጵያ የንጹሐን ዜጎች ግድያና መፈናቀል ወደከፋ ደረጃ እያመራ ነው።

"ከአሁን በፊት በታሪካችን አይተነው የማናውቀው፣የሕዝብ ፍጅት  በሚባል ደረጃ፣የሕዝብ መፈናቀል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፤እየተካሄዱ ናቸው።ሕዝብ በማንነቱን በእምነቱ እየተፈጀ ያለበት ጊዜ ነው።"

በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሚካሄደውን ድርድር አስመልክቶ፣በጉባዔው ላይ ጥናት ካቀረቡ ምሁራን መኻከል፣እዚህ አትላንታ የሚገኘው የሞርሐውስ ኮሌጅ የአሪፍቃና የዓለም ታሪክ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኀይሌ ላሬቦ ይገኙበታል።

ፕሮፌሰር ኀይሌ፣የንግግሩ ዋና ዓላማ ሰላም ማምጣት መሆኑ በጎ ጎኑ እንደሆነ ገልጸው፣ይሁንና ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በማንሳት አስረድተዋል።

"ሕዝብ የተሳተፈበት፣ምሁራን፣ባለሙያዎች የተሳተፉበት የሕዝቡ ምስለኔ ነው ተብሎ የሚታየው የሚታሰበው የብሔራዊ ሸንጎ የተወያየበት፣የተጎዳው አካባቢ የተመከረበት ነው ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል።በዚያ መልክ ሰላም መጥቶ ከሆነ እሰዬው ሁላችንም የምንወደው ነው።ይህ እየሆነ አይመስለኝም።"

ድርድሩን ከኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አኳያ በፈተሹበት በዚሁ የጥናት ጽሑፋቸው፣ፕሮፌሰር ኀይሌ ኢትዮጵያውያንን ይከፋፍላል ያሉት ሕገመንግስት ጋር የተጣጣመ የሰላም ሂደት፣ እንዴት የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ይቻለዋል ሱሉ ሞግተዋል።

"ዋናው ችግሩ ሕገመንግስቱ ራሱ የሰላም ዋስትና የማይሰጡ አንቀጾች አሉት።ከእነዚህም አንዱ የኢትዮጵያን የአንድነት ታሪክ፣የመወላለድ፣ የጋብቻ የእርስ በርስ አብሮ የመኖር ታሪክ የሚሸረሽር ነው።የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቀብሮ የሚያስቀር ነው።"

በመሆኑም የሰላም ሂደቱ ኢትዮጵያውያን ሌላ የሰላም መፍትሔ እንዲፈላልጉ ያበረታታቸው ይሆናል እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ሰላም አያሰፍንም ባይ ናቸው።

የሠላም ውይይቱን አስመልክቶ የተለያዩ አመለካከቶች በተንሸራሸሩበት በዚሁ ጉባዔ ላይ፣የኤርትራ ኀይሎች ከኢትዮጵያ መውጣትን አስመልክቶ የተናገሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ጉዳዩ ተቀባይነት የሌለው አመልከተዋል።

"ኤርትራ ከዐማራ ጋር ሲያያዝ የኤርትራ ወልቃይት አካባቢ መኖር ወሳኝ ነገር ነው።እነሱም አይፈልጉም እኛም አንፈልግም።ስለዚህ ኤርትራውያኖች እንዲወጡ አንፈልግም።ስለዚህ የዐማራና የኤርትራ አሊያንስ ተፈጥሯል።ያን መጠበቅ፣ አለብን ማክበር አለብን።እንግዲህ ማነው አስገድዶ የሚያስወጣቸው ኤርትራውያኖቹን አላውቅም።ኤርትራውያኖቹ ተገደው የሚወጡ አይመስለኝም።"

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአፍሪቃና አሜሪካ ለይ የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ በሚወጡበት ሁኔታ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም። 

ከዲሲ ግብረ ኃይል ጋር በመተባበር በተካሄደው በዚሁ የራዕይ ለኢትዮጵያ ጉባዔ፣ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመመስረት፣ ተሳታፊዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል።

ታሪኩ ኃይሉ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW