1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና

እሑድ፣ ሐምሌ 22 2010

በቅርቡ በተደረገዉ ዉይይት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ፤ የፌደራሊዝም ጥያቄ፤ ብሔራዊ መግባባት፤ ተባብሮ መሥራት ወዘተ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች መነሻ ሐሳብ እንዲያመጡ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አገላለፅ ጠቅላይ ሚንስትሩ «የቤት ሥራ-ሠጥተዋቸዋል።»

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ዉይይት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ናቸዉ?

This browser does not support the audio element.

ለዛሬዉ ዉይይታችን የኢትዮጵያ የተሐድሶ ለዉጥ እና የተቃዋሚዎች ሚና የሚል ጥቅል ርዕሥ ሰጥተነዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት የሚያራምድዉ ፖለቲካዊ ለዉጥ (Reform) የሐገሪቱ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቀዉ እና ሲጠብቀዉ ለነበሩ ጥያቄ እና ጉዳዮች ፈጣን መልስ እየሰጠ ነዉ።መንግሥት ባለፈዉ አራት ወራት ግድም የወሰዳቸዉ እርምጃዎች እንደ አብዛኛዉ ሕዝብ ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤የሲቢክ ማሕበራት እና የፖለቲካ አቀንቃኞች ለ27 ዓመታት ያክል ካነሷቸዉም ጥያቄዎች አብዛኞቹን መልስ ሰጥቷል።

የታሰሩ ቃዋሚ ፖለቲከኞች መፈታት፤የተመሠረተባቸዉ ክስ መሠረዝ፤ ፖለቲከኞች እንዲታሰሩ እና እንዲወነጀሉ ሰበብ የሚሆኑ (እንደ ፀረ-ሽብር ዓይነት ሕጎች መሻር )፤  በስደት የሚገኙ ፖለቲከኞች ወደ ሐገር ቤት እንዲመለሱ መፈቀዱ ወዘተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች 27 ዘመን ትግል እና ጥያቄ መልስ ለማግኘቱ አብነት ናቸዉ።

ዶክተር አብይ ዐሕመድ ሥልጣን እንደያዙ «በእራት ግብዣ» የተጀመረዉ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና  የገዢዉ ፓርቲ መቀራረብ አድጎ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ተወያይተዋል።ያነጋገርናቸዉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪች እንዳሉት ዉይይቱ በመግባባት መንፈስ የተደረገ ነዉ።ለወደፊቱ ተመሳሳይ ዉይይት ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟልም።የገዢ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች መወያያየት፤ መግባባት፤ለተጨማሪ ዉይይት በቀጠሮ መለያየታቸዉም ልዩነትን በዉይይት መፍታት ለማይታወቅባት ሐገር በርግጥ ጥሩ ጅምር ነዉ።

ይሁንና እስረኞችን ከመፈታት እስከ ሕግ መሻር፤ ከእራት ግብዣ እስከ ቅርቡ ዉይይት ወሳኙ፤ጋባዡ፤ አዘጋጁ በሙሉ የገዢዉ ፓርቲ መሪ ዶክተር ዐብይ እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም።በቅርቡ በተደረገዉ ዉይይት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ፤ የፌደራሊዝም ጥያቄ፤ ብሔራዊ መግባባት፤ ተባብሮ መሥራት ወዘተ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች መነሻ ሐሳብ እንዲያመጡ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አገላለፅö ጠቅላይ ሚንስትሩ «የቤት ሥራ-ሠጥተዋቸዋል።»

የኢትዮጵያ ወጣቶች ማንም ሳያደራጃቸዉ በየአደባባዩ ለለዉጥ ሲታገሉ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የወጣቱን ትግል እና መስዋዕትነት አልተጋሩም ተብለዉ ተብለዉ ሲወቀሱ ነበር።ዶክተር ዐብይ በወሰዱ እና በሚወስዱት እርምጃ ተቃዋሚዎችን አጀንዳ አሳጡቸዉ ሲባል ነበር።አሁን ደግሞ እንቃወመዋለን ከሚሉት ገዢ ፓርቲ ወይም መንግስት መሪ ፈቃድ፤ይሁንታ እና ጥሪ እየተሰበሰቡ የቤት ሥራ ከተቀበሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ፖሊሲ አቅራቢ መሆናቸዉ የቱ ላይ ነዉ የሚል ጥያቄ አስከትሏል።ፖሊሲ እና ስትራቴጂስ አላቸዉ ወይ? ካለ ምን? በዉይይታችን የምናሰሳቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW