ዉይይት፤ የቤተ-እምነቶች መደፈርና የአማኞች መገደል
እሑድ፣ ሰኔ 4 2015ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት በሥልጣን፣ በጎሳ፣በኃይማኖት፣በግዛት ይገባኛል ሰበብ በየጊዜዉ በተጫረ ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃት መቶ ሺዎች እያለቁ፣ ሚሊዮኖች ይፈናቀላላሉ።
በአንዳዶች ግምት ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ያለቀበት፣ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጥ የተፈናቀለበት የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት መቆሙ ቢነገርም መዘዙ አሁንም ተመዝዞ ያበቃ አይመስልም።በአብዛኛዉ ኦሮሚያ ክልል ወትሮም ጋብ-ጋም ይልየነበረዉ ግጭትና የጎሳ ጥቃት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።ግጭቱ ቀጥሏልም።
የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት «የክልል ልዩ ኃይላትን ዳግም ለማደራጀት» ባለዉ ዉሳኔዉ በተለይ በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ፋኖ ላይ የከፈተዉ ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ደግሞ የከፍተኛ ባለስልጣናቱን ሕይወት ጭምር ጭዳ እያደረገ ነዉ።
ኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧ በድርቅና በተያያዥ ተፈጥሮዊ ችግሮች ተመፅዋች ነዉ።የኑሮ ዉድነት፣የሰላም መታወክና የሥራ እጦት ሌሎች ሚሊዮኖችን እያሰቃየ ነዉ።የፌደራሉና የአንዳድ ክልል መሪዎች ግን በቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር አብያተ-መንግስታትና አዲስ ከተማ እያስገነቡ መሆኑ በግልፅ እየተዘገበ ነዉ።
ገዢዎች ከዉጪ ምፅዋት ከሚለመንለት፣ ከተፈናቀለዉና በምግብና መድሐኒት እጦት ከሚሰቃየዉ፣ በፀጥታ እጦት ከሚሸማቀቀዉ ሕዝባቸዉ እየቀሙ አብያተ መንግስታት ማስገንባቱ አላሳፈራቸዉም።ይልቅዬ ለነሱ የቅንጦት ሕንፃ ለመስራት ሕጋዊ ያደረጉትን ግንባታ ተራ ዜጎች የቀለሱትን ጎጆ ግን «ሕገ-ወጥ» እያሉ መቶ ሺዎችን አዉላላ ሜዳ ላይ በትነዋል።
የኦሮሚያ መስተዳድር «አዲስ እገነባዋለሁ» ላለዉ ከተማ ለመገንባት መኖሪያ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን ከ20 በላይ መሳጂዶችን አፍርሷል።የመሳጂዶቹ መፍረስ ያሳዘነዉ ሙስሊም ምዕመን በተለይ የአዲስ አበባና የጂማ ነዋሪ ባለፈዉ ሳምንት አርብና ከዚያ በፊት በነበረዉ ሳምንት አርብ በየመሳጂዶቹ ተቃዉሞዉን ለማሰማት ሲሞክር ፀጥታ አስከባሪዎች በጥይት ደብድበዉታል።
የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ በትንሽ ግምት 7 ሰዎች ተገድለዋል።በመቶ የሚቆጠሩ አንድም በጥይት አለያም በዱላ ተደብድበዉ ቆስለዋል።አንዳዶች የሟቾቹ ቁጥር ከ10 ይበልጣል ይላሉ።
የመንግስት ኃይላት አዲስ አበባ፣ ጂማና ሸገር ከተማ ዉስጥ አማኞችን ሲግድሉ፣ ወይም ቤተ-እምነቶችን ማፍረስና ማርከሳቸዉ በሚነገርበት መሐል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምስራቅ ጎጃም ደብረ-ኤሊያስ ወረዳ በሚገኘዉ የቅድስ ስላሴ ገዳም ላይ ጥቃት መክፈቱ ተዘግቧል።የኢትዮጵያ የፀጥታና የደሕንነት ግብር ኃይል ባወጣዉ መግለጫ እንዳለዉ የሐገር መከላከያ ጦርና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ርምጃዉን የወሰዱት ግብረ-ኃይሉ «ገዳሙ ዉስጥ ምሽግ በመቆፈር ሕዝቡ ቅዱስ የሚለዉን ሥፍራ የጦር አዉድማ ለማድረግ» በቃጡ በእስክንድር ነጋና ግብረ አበሮቹ ላይ ነዉ።
በግብረ-ኃይሉ መግለጫ መሰረት የመንግስት ኃይላት በከፈቱት ጥቃት ገዳሙ ዉስጥ የመሸጉ 200 «ፅንፈኛ» የተባሉ ታጣቂዎች ተደምስሰዋል።ገዳሙ ዉስጥ የሚኖሩና ከጥቃቱ ያመለጡ አማኞች እንደሚሉት ግን ገዳማቸዉ ዉስጥ ታጣቂ አልነበረም።ሟች ቁስለኞችም መናኒያን፣ አገልጋዮችና ልጆች ናቸዉ።
መስጂዶቹንና በሙስሊሞች ላይ የደረሰዉን ግድያ በተለመለከተ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባኤ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድርና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር መነጋገሩን አስታዉቋል።የጉባኤ ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ 5 ሰዓት ያሕል ከፈጀዉ ዉይይት ተገኘ የተባለዉ ዉጤት የኦሮሚያ ክልል ለሸገር ከተማ በነደፈዉ ማስተር ፕላን መስጊድም ሆነ ሌላ ቤተ-እምነት የሚሰራበት ቦታ አለ የሚል ነዉ።
ለፈረሱት መሳጂዶች፣ለጠፋዉ ንብረት፣ ከሁለቱም በላይ ለተገደሉት ሰዎች ቤተ-ሰቦችም ሆነ ለቁስለኞች የሚከፈል ካሳ የለም።ገዳዮች ለፍትሕ ይቀርባሉ የሚል ስምምነት የለም።ባለፉት ሁለት አርቦች የተፈፀመዉ ጥቃት ላለመደገሙም ዋስትና የለም።
አዲስ አበባ፣ሸገርና ደብረ ኤልያስ በሚገኙ አማኞችና በእምነት ሥፍራዎቻቸዉ ላይ የደረሰዉ ጥቃት፣ምክንያቱና መፍትሔዉ የዛሬዉ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።በዉይይቱ ላይ እንዲሳተፉ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ባለስልጣናትን ለመጋበዝ በተደጋጋሚ ደዉለን፣ፅፈንም ነበር መልስ አልሰጡንም።
ነጋሽ መሐመድ