ዉይይት፣ የትራምፕ ድል፣ መርሐቸዉ፣ የዓለም ሥጋትና ተስፋ
እሑድ፣ ኅዳር 1 2017071124
ዩናይትድ ስቴትስ የመሐል ግራ ፖለቲካን እንቢኝ ብላ ሴትና ጥቁር ፖለቲከኛን ጥላ፣ ዳግም ወደ ቀኝ ተስፈነጠረች።ነጭ፣ ወንድና ቱጃር ፖለቲከኛን መርጠችም።45ኛዉ ፕሬዝደንት አራት ዓመት እንደፎከሩት እንደገና 47ኛዉ ፕሬዝደንት ሆነዉ ተመርጠዋል።ዶናልድ ጆ ትራምፕ።
ወግ አጥባቂዉ የዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ ሪፐብሊካን በፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በሕግ መወሰኛዉ ምክር ቤትም 52 መቀመጫዎችን በመቆጣጠር አሸናፊነቱን አረጋግጧል።
የ78 ዓመቱ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ብዙዎች እንደሚሉት ዘረኛ፣ስደተኛና ደሐን የሚጠየፉ፣ጋዜጠኛ፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ባለሥልጣኖቻቸዉን ሳይቀር የሚሳደቡ፣ ለሐብታሞች የወገኑ፣ በወንጀል የተፈረደባቸዉ፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ትብብር ደንታ ቢስ፣ የተናጥል (አሜሪካ ብቻ) የሚል መርሕ አቀንቃኝ መሆናቸው የሚታወቅ፣ በጀመሪያዉ ዘመነ ሥልጣናቸዉ የተረጋገጠ ነዉ።
የአሜሪካ ሕዝብ ግን ወዶ መርጧቿል።የምርጫዉን ሒደት በንቃት ይጠብቅ ከነበረዉ ዓለም እንደ ፖለቲካ-ጥቅም ዝንባሌዉ ጥቂቱ በትራምፕ ድል ሲደሰት፣ ምዕራብ አዉሮጶችን ጨምሮ አብዛኛዉ ዓለም ቅር ብሎታል።
ሶቭየት ሕብረት የምትመራዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት በአብዛኛዉ ዓለም ከፈራረሰ (እጎአ) ከ1991 ወዲሕ በጦር ኃይል፣ በሐብት፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስና ርዳታ ከዓለም ቀዳሚዉን ሥፍራ የምትይዘዉ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቢያንስ ለአራት ዓመት የምትመራዉ በትራምፕ ይሁንታና ፍቃድ ነዉ።የተቀረዉ ዓለም ዩናይትድ ስቴትስ ጠላትም ሆነ ወዳጅ የትራምፕን መርሕና ርምጃ ማማተር፣ አቆብቁቦ መጠበቅ ግድ አለበት።
የአሜሪካኖች ዴሞክራሲ እንዴትነት፣ የትራምፕ ድል፣ የዉጪ መርሐቸዉ ምንነትና የዓለም የወደፊት ጉዞ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ለዉይይቱ እንግዶች ሳይሆን ጋዜጠኞች ነዉን የጋበዝነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።
ነጋሽ መሐመድ