ዉይይት፣ የአሜሪካ ረቂቅ ሕግጋት ይዘት፣ጥቅምና ጉዳት ለኢትዮጵያ
እሑድ፣ መጋቢት 25 2014
ጤና ይስጥልኝ እነምን ዋላችሁ።በአዛኛዉ ሰሜን ኢትዮጵያን ያወደመዉ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ አለማግኘቱ ያነሳሳቸዉ የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች ለጦርነቱ፣ ጦርነቱ ላደረሰዉ ጥፋትና ለሌች ግጭቶች ተጠያቂ የሚባሉ ወገኖችን ለመቅጣት ያለሙ ሁለት ሕግጋትን አርቅቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትሱ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት (House ይሉታል ባጭሩ) አባል ቶም ማሊኖቭስኪ ያረቀቁት HR 6600 የተባለዉ ሕግ ተቀባይነቱ አነጋግሮ ሳያበቃ፣የሕግ-መወሰኛዉ ምክር ቤት (ሴኔት) የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሮበርት ቦብ ሜኔንዴዝ S.3199 የተባለ ሌላ ረቂቅ ሕግ አርቅወዋል።
በS.3199 ረቂቅ ላይ በተከታታይ ሲነጋገሩ የቆዩት የሴኔቱ የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ አባላት ረቂቁን ከማሻሻያ ጋር ተቀብለዉ ለሴኔቱ ጉባኤ መርተዉታል።«ኢትዮጵያጵያ ዉስጥ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚለዉ HR 6600ም ሆነ «የኢትዮጵያ የሰላምና የመረጋጋት ደንብ» የሚለዉ S.3199 ሕግ የሚሆኑት ወይም የሚፀኑት የሁለቱ ምክር ቤቶች አፅድቀዋቸዉ ፕሬዝደንቱ ሲቀበሏቸዉ ነዉ።
የረቂቅ ሕግጋቱ ይዘት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ይመስላል።ከፀደቁ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጦርነትና ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ፣ ተኩስ አቁም፣ ድርድርና ስምምነት እንዳይደረጉ የሚያዉኩ፣ ሰዉ የገደሉ-ያስገደሉ፣ሴቶችን የደፈሩና ያስደፈሩ፣ ሰላማዊ ሰዎችን ያሰደዱ ወይም ያፈናቀሉ፣ የእርዳታ እሕል ለችግረኛ እንዳይደርስ ያገዱ የመንግስት፣ ያማፂያን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የዉጪ መንግስታትን ባለስልጣናትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ዝርዝሩ ብዙ ነዉ።በሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን፣ የጦር ወንጀሎችን፣ ዘር ማጥፋት ወዘተ ያደረሱና ለማድረስ የሞከሩ ወገኖችን የሚቀጣ ነዉ።የቅጣቱ ዓይነትም አፈፃጸሙም ዉስብስብ ነዉ።ማዕቀብ፣ቪዛ ክልከላ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍና ርዳታ እንዳይገኝ ማሳገድን ያካትታል።
የአሜሪካ ምክር ቤት ሕወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም የተለያዩ ረቂቅ ሕጎች ቀርበዉለት በየጊዜዉ ዉድቅ ሆነዋል።የቀድሞዎቹም ሆኑ ያሁኖቹን ረቂቅ ሕግጋት የኢትዮጵያ መንግስታት አጥብቀዉ ተቃዉመዋቸዋል።
ኢትዮጵያዉን ግን በተለይ ያሁኖቹን ረቂቆች በመቃወምና በመደገፍ ለሁለት ተከፍለዉ እየተከራከሩ ነዉ።የረቂቅ ሕግጋቱ ይዘት፣ አሜሪካኖች ስለኢትዮጵያ የተጨነቁበት ምክንያት?፣ የኢትዮጵያዉያዉያን ድጋፍ-ተቃዉሞ እንዴትነት የዛሬዉ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ሶስት እንግዶች አሉን።
ነጋሽ መሐመድ