ዉይይት፤ የኢትዮጵያዉያን ማህበራዊ መስተጋብር እንዴት ይመለስ?
እሑድ፣ ጥር 7 2015በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀዉን የእርስ በርስ ጦርነት በስምምነት ካበቃና፤ የሰላም ንፋስ ከአዲስ አበባና ከመቀሌ ፖለቲከኞች መንፈስ ከጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። በትግራይ ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረዉ የባንክ፤ የስልክ፤ የኢንተርኔት እና የአየር በረራ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተጠግነዉ፤ ቀስ በቀስ ስራ እየጀመሩ ነዉ። መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የርዳታ እህል፣ መድሐኒት እና የህክምና ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ እያደረሱም መሆኑ እየተዘገበ ነዉ። ባለፈዉ ሰሞን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ 30 በላይ የሚሆኑ፤ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች፤ የተመድ እና የአዉሮጳ ህብረት ተወካዮች፤ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪቃ በየነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) መቀሌ ተገኝተዉ የሰላም ስምምነቱን ፍሪ አወንታዊ ሲሉ አወድሰዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እርቅ ሲፈፅሙ በጦርነት ዉስጥ የነበረዉ ማኅበረሰብ እፎይ ይበል እንጂ፤ ማኅበረሰቡ ለዘመናት አብሮት ከኖረዉ ህዝብ ጋር አሁንም እንደተራራቀ ነዉ።የሰን ኢትዮጵያ ጦርነት ማብቂያው የት ይሆን? የሁለት ዓመቱ የእርስ በርስ ጦርነት በሰሜን የኢትዮጵያ በሚገኘዉ ማኅበረሰብ ዘንድ በነበረዉ ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ጠባሳን ጥሎ ነዉ ያለፈዉ። ይህ ጠባሳ እንዲፈወስ በህብረተሰቡ ውስጥ እውነተኛ እርቅና ይቅርታ እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት ? የኢትዮጵያዉያኑ ማህበራዊ መስተጋብሩ እንዴት ይመለስ?
በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን ሊያካፍሉን የቀረቡት ?
አቶ ዮሃንስ ሰለሞን: ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፤ አቶ ዩሴፍ ኃይለሥላሴ: የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ በአጭሩ ባይቶና የህግ ጉዳይ ኃላፊ ፤ መላከ መዊ ልሳነ ወርቅ ዉቤ: በጀርመን ፍራንክፈርት የምስካኤ ዙናን መድሐንያለም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ፤ አቶ አዲሱ ጌታነህ -ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸዉ ።
ተወያዮች አስጠያየት የሰጡባቸዉ ጥያቄዎች፤
- የሰሜን ኢትዮጵያዉ የእርስ በርስ ጦርነት በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ካደረሰው ጉዳትና ውድመት በላይ በህዝቦች ማህበራዊ ትስስር፣ አብሮነትና አንድነት ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም ሲሉ ብዙዎች ይናገራሉ።እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ወዴት? በዚህ በኩል ያላችሁ አስተያየት ምንድን ነው?
- በሌላ በኩል ግን ጦርነቱ የፖልቲከኞች ወይም የፖለቲክ ድርጅቶች እንጂ የህዝቦች አይደለም በማለት በህዝቦች ግንኙነትና ትስስር ላይ ያደርሰው ጉዳት ብዙ አይደለም ወይም በቀላሉ የሚፋቅ ነው የሚሉ አሉና በዚህ በኩልስ ምን አስተያየ አላችሁ።
- ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሁሉም አክባቢዎች ተፈጸሙ የሚባሉት ወንጀሎችና አስገድዶ መድፈሮች ከዚህ ቀደም ብዙም የማይታወቁ እንደሆኑ ይጠቀሳል። ምን ይሆን ምክኒያቱ በዚህ ወቅት በዚህ ትውልድ እንደዚህ አይነት አስከፊ ወንጀሎች የተፈጸሙት ምክንያት?
- የሰላም ስምምነቱ በጦርነት ዉስጥ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂዎችን ለፍትህ የማቅረብ ጉዳይን ብዙም አላካተተም የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚባለዉ ከህብረተሰቡ ጋር ግንኙነት አለዉ ወይ?
- በአፋር እና በትግራይ በትግራይ እና በአማራ የደረሰዉ የስነ ልቦና እና ማኅበራዊ ቀዉስ በነዋሪዎች መካከል የደረሰዉ መቃቃር ከፍተና ደረጃ ላይ መሆኑ ይነገራል። ይህን እናንተ እንዴት ነዉ የምታዩት_ ከፍተኛ ሲባልስ ምን ማለት ነዉ?
- የፌደራል መንግሥቱ ሚና ከትግራይ የፓለቲካና ተጠሪዎች ጋር በመነጋገር እነሱን ወደ ኃላፊነት በመመለስና መሠረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋም ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ወይ መሆን ያለበት?
- የሃይማኖት መሪዎች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማብቂያው የት ይሆን?የሃገር ሽማግሌዎች የመብት ተሟጋቾች የሲቢክ ማኅበረሰብ የፓርላማ ተወካዮች በየአካባቢዉ የሚኖረዉን ህዝብ የደረሰበትን በደል አንስተዉ ያላነጋገሩት ለምንድን ነዉ? ከዚህ በኋላስ ምን መደረግ አለበት?
- አሁን ከስምምነት ተደርሷል ስምምነቱም ተግባራዊ እየተደረገ ነው፣ ግን እርቁ እንዲጸናና ዘላቂ እንዲሆን በህዝቡ መካከል የተፈጠረው ቁስል መዳን አለበት፤ የተበደለ መካስ አለበት ጥፋቱና ጥፋተኝውም መገለጽ አለበት፤ በዚህ በኩል ምን መደረግ አለበት?
- ይህን የሕዝቦች መቀራረብ ለመሥራት የመንግሥትና የኃይማኖት ድርጅቶች ኃላፊነትና ምን መሆን አለበት?
ሃሳባቸዉን ያካፈሉንን ተወያዮች በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ዉይይት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ