1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉጊያና ዉጥረት-በሁለቱ የጎጃም ዞኖች

ረቡዕ፣ ግንቦት 21 2016

አንድ የደንበጫ ወረዳ ነዋሪ እንዳሉት ከግንቦት 18 ጀምሮ በወረዳው “ዘለቃ” በተባለች የገጠር ቀበሌ ከባድ ውጊያ እንደነበርና 4 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ አንድ ሴት ደግሞ በከባድ መሳሪያ ጥይት ፍንጣሪ ህይወታቸው ማለፉን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፣

በምሥራቅ ጎጃም ጎን አንዳድ አካባቢዎች ሰሞኑን በመከላከያ ሠራዊት በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ዉጊያ ነበር
በአማራ ክልል ከምሥራቅ ጎጃም ዞን አካባቢዎች አንዱ።ሰሞኑን በአንዳድ የዞኑ ወረዳዎች ዉጊያ ሲደረግ ነበርምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ዉጊያና ዉጥረት-በሁለቱ የጎጃም ዞኖች

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞንች በሚገኙ  አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መደረጉን ነዋሪዎች አስታወቁ።ዉጊያዉ ዛሬም መቀጠሉን  ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለም ነዉ መኮንን ያነጋገራቸዉ የፈረስ ቤትና የደንበጫ ነዋሪዎች እንዳሉት በሁለቱ ከተሞች ዉጥረቱ ተባብሶ ቀጥሏል።

አንድ የደንበጫ ወረዳ ነዋሪ እንዳሉት ከግንቦት 18 ጀምሮ በወረዳው “ዘለቃ” በተባለች የገጠር ቀበሌ ከባድ ውጊያ እንደነበርና 4 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ አንድ ሴት ደግሞ በከባድ መሳሪያ ጥይት ፍንጣሪ ህይወታቸው ማለፉን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፣ የቆሰሉ ሰዎች ደግሞ “ዋድ” በተባለ ጤና ጣቢያ ህክምና እየወሰዱ እንደሆነ አመልክተዋል፣ በአካባቢው ያለው የተኩስ ልውውጥ ገና አንዳልለየለት ነው አስተያየት ሰጪው የሚያስረዱት፡፡

“ደንበጫ ወረዳ ዘለቃ ቀበሌ ... መከላከያዎች ገብተው አደሩ፣ ትናንት ንጋት 12 ሰዓት አካባቢ ተኩስ ተጀመረ፣ ዘለቃ ላይ ከባድ መሳሪያዎች ወደ ከተማው መተኮስ ጀመሩ ህዝቡ ከከተማው ወጣ፣ እኛ ቤት ውስጥ ተኝተን ነው የዋልነው፡፡”

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በምስራቅ ጎጃም ዞን አንድ አማኑኤል ከተማ ነዋሪ ባለፈው እሁድና ሰኞ በከተማዋ ሁለት አቅጣጫዎች ውጊያዎች እንደነበሩ ነው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የገለፁት፡፡

“እሁድና ሰኞ ነው ተኩስ የነበረው፣ የተቃጠለ ቢሮ አለ ሁለት ቀን ሙሉ ነው ተኩስ የነበረው፣ እስከ ምሽት ውጊያ ነበረ፡፡” ብለዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ባለፈው ሰኞ ውጊያ እንደነበርና አሁን አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም በከተማዋ ውጥረት እንዳለ ነው ያመለከቱት፣

ነዋሪው እሁድ እለት የነበረውን ውጊያ ሲገልፁ፣ “ እሁድ ጠዋት ከአንድ ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ድረስ በከተማዋ ውጊያ ነበር፣ አሁን ከተማዋ ሰላም ብትመስልም (የተኩስ ድምፅ ባይሰማም) ውጥረት ግን አለ፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡” ነው ያሉት፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ነዋሪ በበኩላቸው ባለፈው ማክሰኞ በከተማዋና አካባቢዋ በመከላከያና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊ እንደነበር አስረድተዋል፣ አሁን በከተማዋ የመከላከያ ሰራዊት እንደሚታይ አመልክተው፣ ሆኖም ችግሩ ሊያገረሽ ችላል የሚል ስጋት በነዋሪው ላይ እንደሚሰተዋል ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ የጎጃም ዞኖች በአንዳድ ወረዳዎች ሰሞኑን ዉጊያ እንደነበር የየአካባቢዉ ነዋሪዎች አስታዉቀዋልምስል AP/picture alliance

“የጉዳት መጠን ዝርዝር ሁኔታው በደንብ የታወቀ ነገር የለኝም፣ ... ቀን 6 ሰዓት አካባቢ ዝቋላና አካባቢው እስከ 8 እና 10 ሰዓት አካባቢ ውጊያ ነበር፣ ጉዳቱን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ የለኝም፡፡”

አሁን በከተማዋ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንደሌለ የነገሩን እኝሁ አስተያየት ሰጪ አንዳንድ የንግድ መደብሮች ስራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

“... አሁን የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ በከተማው አለ፣ የተፈራራ ነው፣ የተወሰነ እንቅስቃሴ በእርግጥ ይታያል፣ ተሸከርካሪ የሚባል ነገር አይንቀሳቀስም፣ ወደከተማም ውስጥም ከከተማ ውጪም፣ በከተማም የለም፣ የሰዎች እንቅስቃሴ በመጠኑ ይታያል፣ የንግድ መደብሮች ለ7 ቀናት ክል ተዘግተው ቆይተዋል፣ አሁን በኮማንድ ፖስት የሚመራ ጥምር ኮሚቴ ተቋቁሞ መደብሮችን ማስከፈት ጀምሯል፣ የተወሰኑ ሱቆች ተከፍተዋል፡፡” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬሌ የሰጡት፡፡

አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደቀጠሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፣ ስለሰሞኑ ውጊያ ተጨማሪ አስተያየት ከመንግስትም ሆነ ከፋኖ ታጣቂዎች ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

በጎጃም ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን እንደገና በተቀሰቀሰው የፀጥታ መደፍረስ መንገዶች በመዘጋታቸው እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፡፡ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የፀጥታ ችግር መፍትሔ ሳያገኝ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ቀርተውታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW