1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዋሪስ ዲሪ በበርሊን የከፈቱት የህክምና ማዕከል

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2006

በሶማሊያ የተወለዱት የሴቶች ተሟጋች እና ሞዴል ዋሪስ ዲሪ ባለፈው ረቡዕ የሴት ልጅ ግርዛት ሰለባ የሆኑ የሚረዱበት «ዴዘርት ፍላወር ሴንተር» የተባለ ማዕከል በርሊን ውስጥ መርቀው ከፍተዋል።

Waris Dirie, somalische Bestsellerautorin ("Wüstenblume") und Aktivistin gegen Genitalverstümmelung, kommt am 11.09.2013 als Schirmherrin zur Eröffnung des "Desert-Flower-Centers" am Krankenhaus Waldfriede in Berlin an. Es ist das europaweit erste Krankenhaus, das von Genitalverstümmelung betroffenen Frauen psychologisch und chirurgisch hilft. Die WHO geht davon aus, dass derzeit täglich tausende Mädchen bei der sogenannten rituellen Beschneidung verstümmelt werden, jedes vierte sterbe an den direkten oder langfristigen Folgen des Eingriffs. Foto: Stephanie Pilick/dpa
Berlin Eröffnung Desert-Flower-Center Krankenhaus Waldfriedeምስል picture-alliance/dpa

በየl1 ሰከንዱ አንድ ለአቅመ አዳም ያልደረሰች ልጅ ትገረዛለች። ይህም በሹል ድንጋይ፣ በቢለዋ ተሻለ ቢባል በምላጭ ወይም በመቀስ መሆኑ ነው። የጎጂ ልማዱ አፈፃፀም እንደየ ሀገሩ ይለያያል። በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ የመዋለጃ አካላቸዉ የሚተለተልበት፣ ከዚህም አልፎ ትንሽዬ ቀዳዳ ብቻ ለሽንት ተትቶ ሙሉ በሙሉ የሚሰፋበት አጋጣሚ አለ። በብዛት በአፍሪቃ በመካከለኛው ምስራቅ እና እስያ የሚፈፀመውን Female Genital Mutilation FGM ይሉታል። አብዛኛውን ጊዜ እድሜያቸው ከ4-7 ባልበለጡ ህፃናት ላይ ይረፀማል። ኃላም እድሜ ልክ የሚቆይ ህመም እና ትውስታ ይዘው ይኖራሉ። በዚህ የተነሳም የFGM ሰለባዎች በቀዶ ጥገና ለማከም ሀኪሞች መንገድ ፈጥረዋል። በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነው እና በዋሪስ ዲሪ ድጋፍ ባለፈው ሳምንት በበሊን ከተማ የተከፈተው የህክምና ማዕከል በጀርመን የሚኖሩ ቁጥራቸው ከ25,000 እስከ 50,000 የሚደርሱ ህፃናት እና አዋቂዎች ሊረዱ ይቻላል ተብሎ ይገመታል። በህክምና ማዕከሉ ጋዜጠኛ ናዎሚ አግኝታ ካነጋገረቻቸው ውስጥ ሰናይት አንዷ ናት።

ሰናይት በዴዘርት ፍላወር የህክምና ማዕከልምስል DW/N. Conrad

« ትንሽዬ ልጅ ነበርኩ። በትክክል አላስታውስም የ7 ወይም የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። ትላለች ሰናይት። የሀኪም ቤት አልጋ ጠርዝ ላይ ቆማ ቀዶ ህክምና የምታደርግበትን ሰዓት እየጠበቀች፤ ያኔ ስለገጠማት ታወራ ጀመር። የሰፈሩ ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ምግብ እና ፌስታ ነበር። ሰናይት ሁለት ጓደኞቹ ሲገረዙ የፈሰሳቸውን ደም እና ለማምለጥ የሞከረችው ትዝ ይላታል።«ከዛ ያዙኝ። የሆነውን ሁሉ በደንብ አላስታውስም። ፤ ናዎሚ፣ መቼም በጣም ህመም ነበረው አይደል? ስትል ትጠይቃለች።« አላስታውስም። ምናልባት አእምሮዬን ስቼ ነበር። ከዛ በኋላ ስለሆነው ነገር ምንም አላስታውስም።»

የ 34 ዓመቷ ሰናይት ከጥቂት ወራት በፊት ነው አዲስ ስለሚከፈተው የህክምና ማዕከል የሰማችው። እንደ እሷ ሙሉ በሙሉ የመዋለጃ አካላቸዉ የተተለተለ እና ከዚህም አልፎ ትንሽዬ ቀዳዳ ብቻ ለሽንት መሽኛ ተትቶ ሙሉ በሙሉ ብልታቸው የተሰፋ ልጃ ገረዶች ፤ ሲያድጉ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ወይም ልጅ ሲወልዱ አስከፊ ችግር ይገጥማቸዋል። ስለሆነም ሰናይት ወዲያው ነው ከምትኖበት ፖላንድ ወደዚህ ጣቢያ ለመምጣት የወሰነችው። « የተሟላ ሰው መሆን እፈልጋለሁ። የቆረጡብኝ እንዲመለስልኝ እፈልጋለሁ» ቀዶ ህክምናዋ ለሚቀጥለው ቀን ተዛውሯል። ብዙም አልፈራም ትላለች ሰናይት። ሀኪሟ ዶክተር ሮላንድ ሼረር ግን ጉዳይዋን በጥንቃቄ ይመለከቱታል።« ሁኔታው ከተፈፀመ በኃላ ጊዜው በራቀ ቁጥር በርግጥ ቀዶ ህክምና ቀላል አይሆንም። ደረቅ ጠባሳ ነው የሚኖረው ስለዚህ ይህ ቀዶ ህክምና በሚከናወንበት ጊዜ የተወሰነ ልምድን ይጠይቃል።»

ዶክተር ሮላንድ ሼረር አዲስ በዋሪስ ዲሪ አማካኝነት የተከፈተውን ማዕከል በኃላፊነት ይመራሉ።ምስል imago/epd

ዶክተር ሮላንድ ሼረር አዲስ በዋሪስ ዲሪ አማካኝነት የተከፈተውን ማዕከል በኃላፊነት ይመራሉ። ማዕከሉ የህክምና እና የስነ ልቦናዊ አገልግሎት ይሰጣል። ከዛም በተጨማሪ «ዴዘርት ፍላወር ሴንተር» የማነቃቃት ስራ ያካሂዳል። ሼረር የመልሶ ጥገናውን ህክምና ከሚያደርጉት ሀኪሞች ይመደቡ እንጂ በርካታ ሀኪሞች በዚህ ረገድ ተገቢውን ስልጠና እንዳላገኙ ከአህን ዮንቨርሲቲ ዳን ኦዴይ ያብራራሉ። « ቀድመው በማህፀን ሀኪሞች አማካኝነት ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ምን ያህል ሴቶችን እኔ እንደገና ቀዶ ህክምና እንዳደረኩ መገመት ይዳግተዎታል። »

በአግባቡ ያልተካሄደ ቀዶ ህክምና የታካሚዎቹ ሌላ ሁለተኛ ስቃይ እንደሆነ ኦዴይ በብስጭት ይገልፃሉ። ስኬታማ በሆነ ቀዶ ህክምና የታካሚዎቹን የወሲብ ፍላጎት ማሻሻል እና የሙሉነትን ስሜት በማዳበር በራስ መተማመንን ማጠንከር እንደሚቻል ይገልፃሉ። ሰናይት እንድ ቀን እንደ ዋሪስ ዲሪ ይህን ጎጂ ልማድ ለማስቆም ተሟጋጅ መሆን እንደምትፈልግ ለናዎሚ አጫውታታለች።« ከሆነ ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ ማስተማር እፈልጋለሁ። ልጆችን ከዚህ ለማዳን ሰው ሊገርዛችሁ ሲመጣ ፖሊስ ጥሩ እላቸዋለሁ። ያኔ ልጆቹም በታገል ይጀምራሉ።»

የዋሪስ ዲሪ መፅሀፍምስል Majestic

እንደ ሰናይት ምኞት ልጆቹ ፖሊስ መጥራት መቻላቸው አጠራጣሪ ነው። በብዛት ልጆቹ ገና በልጅነት እድሜያቸው ነው የሚገረዙት። ነገር ግን ችግሩን ይፋ ያደረጉ እንደ ዋሪስ ዲሪ ያሉ የሴት ልጅ የመብት ተሟጋቾች አሉ። ዲሪ ገና የ4 ዓመት ልጅ ገደማ ሳሉ መገረዛቸውን ባሳተሙት መፅሐፋቸው አስፍረዋል። እንደ „ Terre des Femmes“ የተሰኘው የርዳታ ድርጅት ከሆነ ጀርመን ውስጥ ከ24 000 የሚበልጡ ሰለባዎች ይገኛሉ። ወደ 5 ሺ የሚጠጉ እንደውም እጅግ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። እንደ የበርሊን የህግ ጉዳይ ተመልካች የምክር ቤት አባል ፦ ቶማስ ኃይልማን ከሆነ የጀርመን ፖለቲካ የሚገርዙ የግለሰብ ክሊኒኮችን መከታተል፣ ጠንካራ የወንጀል ህግ ማውጣት እና ወንጀል መከታተል እንደሚገባው ይገልፃሉ። የብዙ ሴቶችን ህይወት ከዚህ ስቃይ ለማስቆም ዋንኛው መንገድ ወንጀለኞችን የማጋለጡ ስራ ነው። በዚሁ በጀርመን ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሴት ልጆችን የሚገርዙ ሀኪምን በማጋለጥ እና ማስረጃ ለማሰባሰብ የተባበሩ አንድ ሰው የሆነውን እንዲህ ያስረዳሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት ጀርመን ውስጥ የራሱ የሆነ የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ አይኑረው እንጂ በህግ ያስቀጣል። በፈረንሳይም እንዲሁ የወንጀሉ ቅጣት ከፍተኛ ነው፣ ልጃቸውን የሚያስገርዙ ወላጆች ከ10-30 አመት እስራት ይቀጣሉ ወይንም ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ ።ይሁንና በድብቅ የማይሆን ነገር የለም።

የሴት ልጅ ግርዛት በአፍሪቃ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በእስያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፖ በሚኖሩ መጤዎች ምክንያትም መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ሆኗል። ምንም እንኳን የ«ዴዘርት ፍላወር ሴንተር» ለአቅም አዳም ያልደረሱ ልጆችን ከማስገረዝ ለማስቆም ባይችልም፤ የጎጂ ልማዱ ወንጀል የደረሰባቸውን ሰዎች ከእድሜ ልክ ህመምን ለማስቆም ስራውን ጀምሯል።

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW