1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፤እያሽቆለቆለ ለመጣው የተማሪዎች ውጤት እና የትምህርት ጥራት መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

እሑድ፣ መስከረም 12 2017

በኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ብዙዎችን እያሳሰበ ነው። በስርዓተ ትምህርቱ ፣በትምህርት ጥራት እና አሰጣጥ ላይም ጥያቄ እንዲነሳ እያደረገ ነው። ታዲያ የችግሩ መንስኤ ምንድነው? ተማሪዎች መምህራን ወይስ ስርዓተ ትምህርቱ?መፍትሄውስ?

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር ሎጎ
የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር ሎጎምስል Hanna Demisse/DW

ውይይት፤እያሽቆለቆለ ለመጣው የተማሪዎች ውጤት እና የትምህርት ጥራት መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

This browser does not support the audio element.

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ  ጳጉሜ 04 ቀን 2016  የአምናውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ  ትምህርት ሚንስትር በሰጠው  መግለጫ፤ በአጠቃላይ 1 ሺህ 363  ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላለፈም።  ከሀረሪ ክልል ውጭ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ 4 ትምህርት ቤቶችንጨምሮ በሁሉም ክልሎች  አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ተገልጿል።
ከአምናው የተሻለ ነው  የተባለው ይህ ውጤት፤አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ከ10ሺ በላይ ተማሪዎችን ከክልሎች ደግሞ ሀረር 337 እና ኦሮሚያ 8ሺ በላይ ተማሪዎች ማለፋቸውን  የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልፀዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስትር ምስል Hanna Demissie/DW

ውጤቱ በአጠቃላይ ሲታይ በዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት መካከልም ፈተናውን ያለፉት  5 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ ናቸው። ማለትም ፈተናውን ከወሰዱት  ከ600 መቶ ሺህ ተማሪዎች   መካከል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 36 ሺ 4 መቶ ተማሪዎች ብቻ ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በዚሁ ሁኔታ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ብዙዎችን እያሳሰበ ነው። በስርዓተ ትምህርቱ ፣በትምህርት ጥራት እና አሰጣጥ ላይም  ጥያቄ እንዲነሳ እያደረገ ነው።  
የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ብቻ  ሳይሆኑ የመውጫ ፈተና /Exit exam /ላይ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሆነ ከመንግሥት ዩንቨርስቲዎች የሚወድቁት ተማሪዎች  ቁጥራቸው በርካታ  ነው።

ይህንንም ተማሪዎች፣ መምህራን እና የስርኣተ ትምህርትባለሙያዎችም እየተቹ  ነው፡፡በዚህ ሳምንት የእንወያይ ዝግጅት እያሽቆለቆለ ለመጣው የተማሪዎች  ውጤት እና የትምህርት ጥራት መፍትሄ ይኖረው ይሆን? በሚል  በችግሩ ስፋት፣ ችግሩ በወጣቶች የወደፊት ተስፋ እና  በሀገር  በሚያስከትለው መዘዝ እንዲሁም  በችግሩ መነሻ እና  መፍትሄዎች ላይ እንግዶችን ጋብዞ አወያይቷል።ከኢትዮጵያ የትምህርት ሚንስቴር  ባለስልጣናትን  ለማሳተፍ  ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በውይይቱ የተሳተፉ እንግዶች ፤

1⦁ ፕሮፌሰር ሀምቢሳ ቀንዓ------  ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፤የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ ናቸው።
2⦁ ዶክተር አለማየሁ ተክለማርያም ----በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  የትምህርት እና ባህሪ ኮሌጅ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት መምህር እና ተመራማሪ ናቸው።
3⦁ ዶክተር ዮሀንስ  በንቲ ---------የኢትዮጵያ የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው

ሙሉ ውይይቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW