1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ የጌዲዖ ተፈናቃዮች ፈተና 

እሑድ፣ መጋቢት 8 2011

የኢትዮጵያ መንግሥት ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲዖ ዞን የተጠለሉ 198 ሺሕ 977 ሰዎችን ለመርዳት እንቅስቃሴ የጀመረው "ሰው ከሞተ፤ከተጎዳ፤ ከወደቀ በኋላ" ነው የሚል ወቀሳ ይቀርብበታል። የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ተፈናቃዮች የምግብ፤ የመጠጥ ውሐና የመጠለያ ችግር ተጋርጦባቸዋል።

Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

ውይይት፦ የጌዲዖ ተፈናቃዮች ፈተና 

This browser does not support the audio element.

ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጊዲዖ ዞን የተጠለሉ ዜጎች ፈተና የኢትዮጵያ መንግሥትን ለብርቱ ወቀሳ ዳርጎታል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ እንደሚሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ቸልተኝነት እና የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ማከፋፈል በማቆማቸው ተፈናቃዮች የከፋ ችግር ገጥሟቸዋል። ችግር ከገጠማቸው መካከል ሕጻናት እና እመጫቶች ጭምር ይገኙበታል። 

የሰላም ምኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያ ካሚል ግን የጌዲዖ ተፈናቃዮችን በተመለከተ በመንግሥታቸው ላይ የተነሱ ትችቶችን አጣጥለዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት ከተፈናቃዮቹ ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት "ለስምንት ወራት እርዳታ አናገኝም ነበር የተባለው ትክክል እንዳይደለ ተግባብተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጌዲዖ ተፈናቃዮች ተቸግረዋል የሚሉ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ መረጃዎች በተከታታይ ከወጡ በኋላ ወደ አካባቢው ተጉዘው ውይይት ያደረጉት ወይዘሮ ሙፈሪያት "ለስምንት ወር ምንም አላገኘንም ያሉ ነበሩ። ከዛ ውስጥ የለም እንዲህ ማለት አንችልም። እህል አልተቋረጥብንም። ነገር ግን በመሐል በተወሰነ ደረጃ እዚያ አካባቢ የጸጥታ ችግር ስላለ የተደራጁ ቡድኖች እርዳታውን የመቀማት፤ አልፎ አልፎ ለራሳቸው ጥቅም የማዋል" ችግሮች ነበሩ ሲሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርተዋል።  

ምኒስትሯ "በጌዲዖ ዞን ባሉ ወረዳዎች ያሉ ተፈናቃዮች ምንም አይነት መስተጓጎል አላጋጠማቸውም። እርዳታው እንደቀጠለ ነው" ሲሉም አክለዋል። የጌዲዖ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ "ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲዖ ዞን ብቻ የተጠለሉ 198 ሺሕ 977 ሰዎች ይገኛሉ" ሲሉ ገልጸዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው የተፈናቃዮች ቁጥር "ግማሽ ሚሊዮን አምስት ሺሕ የሚሆን ምናምን የሚባለውም ትክክል አይደለም። ቦታው ላይ የነበሩ ተፈናቃዮች አሉ። እነሱ ላይ ደግሞ የተጨመሩ ወደ 54 ሺሕ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ። ቁጥሩ በድምሩ ወደ 96 ሺሕ ገደማ ነው" ብለዋል። 

የችግሩ ጥልቀት ምን ያህል ነው? በእርግጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች እርዳታ ከማቅረብ ታግደዋል?  የጌዲዖ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ፣ ለተፈናቃዮች እገዛ የምታቀርበው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ወልዴ አየለ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ በሳምንታዊ የውይይት መሰናዶ የሚጠቅሷቸው ችግሮች ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚለው የተለዩ ናቸው። 

የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን የውይይት መሰናዶውን ያድምጡ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW