1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዎላይታ ዞን የመምህራን እሥር

ዓርብ፣ ጥቅምት 15 2017

በዎላይታ ዞን በርካታ መምህራን በፖሊስ እየታሠሩ መሆኑን የታሳሪ ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ። እሥሩ የተፈፀመው መምህራኑ ከደሞዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፊርማ በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ አቤቱታቸውን ለማስገባት መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ነው።

ዎላይታ ዞን
በዎላይታ ዞን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንዱ ፎቶ ከማኅደርምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዎላይታ ዞን የመምህራን እሥር

This browser does not support the audio element.

ፖሊስ መምህራኑን የሚያስረው አመፅ ለመቀስቀስ ተንቀሳቅሰዋል፤ የዞኑን ገጽታ አጥፍተዋል በሚል መሆኑን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል። በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው የዞኑ መስተዳድር የመብት ጥያቄ በሚያነሱ መምህራን ላይ የሚያደርሰውን እሥር እና ወከባ እንዲያቆም ጠይቀዋል።     

የመምህራን እሥር በዎላይታ ዞን

መምህር ዳንኤል ፋልታሞ በዎላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በእንግሊኛ ቋንቋ መምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። መምህሩ በዞኑ ፖሊስ አባላት እስከታሠሩበት እስካለፈው ሰኞ ድረስ የመምህራን ደሞዝ እንዲከፈል ለመጠየቅ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ ነበሩ ይላሉ የሚያውቋቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው። ይሁንእንጂ መምህሩን ሌሊት ፖሊሶች ከቤት ይዘዋቸው እንደሄዱ ነው የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ባለቤታቸው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት።

ፖሊሶች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ወደ ቤት እንደመጡ የጠቀሱት የመምህሩ ባለቤት «በወቅቱ ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበረም። ቤተሰቡ በሙሉ በእንቅልፍ ላይ ነበር። ቤቱን አስከፍተው ከገቡ በኋላ አልጋ እና ፍራሽ ሳይቀር ፈትሸው ምንም ሊያገኙ አልቻሉም። በመጨረሻም ግን ባለቤቴን ይዘውት ሄዱ» ብለዋል።

«እረፉ»

ለደህንነታችን ሲባል ሥማችን አይጠቀስ ያሉ ሌላ ሁለት የዚሁ ወረዳ ነዋሪዎችም ባሎቻቸው ደሞዝ ይሰጠን ብለው የዳቦ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ታሰረውብናል ይላሉ። « ፖሊሶች ወደ ቤት ሲመጡ ምንም አይነት የፍርድ ቤት መያዣ ወረቀት አላሳዩም» ያሉት የመምህራኑ ቤተሰቦች የተሳሳተ መረጃ አሰራጭታችኋል በሚል መያዛቸውን ከአንድ ፖሊስ አባል መስማታቸውን ተናግረዋል።

እማኞች በዎላይታ ዞን መምህራኑ የታሠሩት ከደሞዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፊርማ በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ አቤቱታቸውን ለማስገባት መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ መሆኑን ይናገራሉ።ፎቶ ከማኅደር፤ ዎላይታ ዞን ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የመምህራን ደሞዝ ይከፈል በሚል የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ሲያከናውኑ ከነበሩት መካከል ሦስት በቅርብ የሚያውቋቸው መምህራን መታሠራቸው ለዶቼ ቬለ የተናገሩ አንድ የዳሞት ወይዴ ወረዳ መምህር አስተባባሪዎቹ ከመታሠራቸው በፊት «እረፉ» የሚል መልዕክት ከወረዳው አመራሮች ተልኮባቸው ነበር ይላሉ።

የሙያ ማህበሩ እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይላሉ ?

ስለመምሀራኑ እሥር የዳሞት ወይዴ ወረዳ እና የዎላይታ ዞን የፖሊስ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም ምላሽ የሚሰጥ አካላ ባለመገኘቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም። ያምሆኖ የመምህራኑን እሥር አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል ጳውሎስ «መምህራን ደሞዝ የመጠየቅ መብት መንግሥትም የመክፈል ግዴታ አለበት። የደሞዝ ጥያቄ በማቅረባቸው እሥርና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል የሚል መረጃ እስከአሁን እኛ አልደረሰንም። ነገር ግን ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ትክክል አይደለም። እኛም የምንታገለው ይሆና» ብለዋል።

አቶ ጎበዜ ጎኣ በመምህራን የደሞዝ ጥያቄ ላይ በተደጋጋሚ አቋማቸውን በመግለጫ እየገለጹ ከሚገኙት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የዎላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ዎህዴግ ሊቀመንበር ናቸው። በዞኑ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የተለያዩ «ታፔላዎችን» መጥለፍ የተለመደ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ «መምህራኑ ከሚገባቸው ውጭ የጠየቁት የተለየ ነገር የለም። ደሞዛችን ይከፈል ብለው ነው የጠየቁት። ደሞዝ የጠየቀን አመፅ ቀስቀሰሃል ብሎ ማሰር ከሥነምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ነው» ብለዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW