1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐቢይ «ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ» ያሏቸው ማን ናቸው?

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2015

በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚፈልጉ «ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ» የተባሉ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመዝናኛ ቦታ ባስመረቁበት ወቅት ተናገረዋል ።

Äthiopien Begeisterter Empfang für Präsident Isaias an Adis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

የፖለቲካ ተንታኙ ኤርትራን ቀዳሚ ያደርጋሉ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚፈልጉ «ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ» የተባሉ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመዝናኛ ቦታ ባስመረቁበት ወቅት ተናገረዋል ። «ኢትዮጵያን በማበጣበጥ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ዐውቀው የእኛን ጉዳይ ለእኛ ትተው ሥራቸውን በምድራቸው ይሥሩ» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው አካላት እነማን እንደሆኑ ግን በግልጽ አልተናገሩም ። ለመሆኑ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ይገባል የተባለው የውጭ ኃይል ማን ይሆን?

የአፍሪቃ ቀንድ አገራት አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ የሚገባበት፣ በተለይ በፀጥታና በወታደራዊ መዋቅሮች በጥቅም ግንኙነት መተሳሰራቸው ባህሪያዊ ነው ያሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ቀጥታ ለኤርትራ ነው ሲሉ ምክንያታቸውን ዘርዝረዋል።

በተኩስ አቁም ስምምነት ከተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም በተለይም ከ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት እንደነበር ይታወቃል። አፍሪቃ ቀንድ በጦርነት፣ በድርቅ፣ በድህነት ለእረፍት የለሽ መጎሳቆል የተጋለጠ አካባቢ ከመሆኑም በላይ ሦስት አህጉሮች የሚገናኙበት ቁልፍ የንግድ ቀጣና ሆኖ መገኘቱ ኃይል ያላቸው መንግሥታት ዐይን የማይነቀልበት ነው።

የአካባቢው አገራት በጥቅም የተሳሰረ ባህሪያዊ ግንኙነት መመስረታቸውና ይህም በተለይ በፀጥታና በወታደራዊ መዋቅሮች ጭምር መሆኑን የሚገልፁት የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ዶክተር ሙዐዝ ግደይ ኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ኃይሎች ውስጥ ቀዳሚ አድርገው የሚጠቅሱት ኤርትራን ነው። 

"ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ሚና ተክታ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዋና ፖሊስ እና ኃላፊ የሆነችበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ በእያንዳንዷ የአፍሪካ ቀንድ አገር መዲና ውስጥ የምትካሄድ የፖለቲካ ፣ የፀጥታ እንዲሁም የወታደራዊ እንቅስቃሴ በኤርትራ ቅኝት ለማስካድ ከፍተኛ ሥራዎች እየሰራ ነው ያለው" በማለት የኢሳያስ አፈወርቂን አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከዓመታት በፊት ወዳጅነታቸው በዓለም አደባባይ ለሙገሳ ሲበቃ የተስማሙባቸው ነጥቦች ግልጽ አልነበሩም። ኢትዮጵያ ቀይ ባህር እና የአሰብ ወደብን የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኤርትራ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ተጽእኖ የመንጠቅ ፍላጎት ሊኖራት እንደሚችል ይገመት ነበር። ዶክተር ሙዐዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማሳሰቢያ በግልጽ ለኤርትራ ነው የሚል አቋም አላቸው። 

ዘወትር ግጭት እና ችግር የማይርቀው የአፍሪቃው ቀንድምስል DW

"በአሁኑ ሰዓት አልሸባብ ብለህ ሶማሊያን ልትጠረጥር አትችልም፣ ጅቡቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ የምትገባ አይደለችም፣ ሱዳን በራሷ ጉዳይ እየተናጠች ነች ያለችው፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሰላማዊ ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ሌላ ማን ሊመጣ ይችላል" በማለት ምክንያት ያሉትን ይዘረዝራሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ከወራት በፊት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ኤርትራንም ሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነትን አስመልክቶ ተከታዩን ብለው ነበር። "የኤርትራ መንግሥት ተከዜን ተሻግረን በኤርትራ ዞረን ፣ በዛላንበሳ በአዲግራት ለመምጣት ስለፈቀደልን፣ ስላገዘን ነው ይህ ጦርነት የተቀለበሰው። ይህንን ያደረጉልን ሕወሓት እንዲጠፋ ስለሚፈልጉ ነው" በማለት ገልፀው ነበር።

የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ዶክተር ሙዐዝ ግደይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያደረገት ንግግር ለኤርትራ ሊሆን ይችላል ያሉበትን ምክንያት ሲጠየቁ የፕሪቶሪያው የተኩስ ማቆም ስምምነት ኤርትራን አለማስደሰቱን በመግለጽ በአዲስ አበባ እና አስመራ መካከል የግንኙነት መሻከር መከሰቱን አስረጂ ጠቅሰዋል።

"በሕግ ማስከበር እና ትጥቅ ማስፈታት ስም ዐቢይ አማራ ክልል ላይ እየፈፀመ ያለውን ነገር አይፈልጉትም ኢሳያስ አፈወርቂ እና ሕግደፍ። ምክንያቱም በዘላቂነት ትግራይን እረፍት የሚነሳ ኃይል ይኖር ከሆነ ትግራይና አማራ ሁሌም እየተዋጉ መኖር አለባቸው ማለት ነው። ይሄ ደግሞ የኢሳያስ አፈወርቂ ሕልም ነው። ይህ ከሆነ ደካማ ኢትዮጵያ ነው የምትኖረው። ደካማ ኢትዮጵያ በምትኖርበት ቀጣና ውስጥ ደግሞ ጠንካራ ሆኖ ሊወጣ የሚችል ቀጣናዊ ኃይል ኤርትራ ናት" ብለዋል። በስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ኢትዮጵያን ለተደራራቢ የምዕራቡ ዓለም እና የዩናይትድ ስቴትስ ጫና ሰለባ አድርጓት ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW