1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዐዉደ ጥናት፤ ዘመናዊ የአማርኛ ማስተማርያ ለዉጭ ዜጎች

Azeb Tadesse Hahn
ዓርብ፣ ጥር 16 2017

በኔፕልስ ዩኒቨርሲቲ፤ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በ1890ዎቹ መሰጠት መጀመሩን ዶ/ር ጌቲ ገላዬ ተናግረዋል። በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 125 ዓመታት የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ ነዉ። በጀርመን የሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላለፉት 105 ዓመታት ያለምንም ማቋረጥ እየተሰጠ መሆኑን ዶ/ር ጌቲ ገላዬ አክለዋል።

የአማርኛ ቋንቋ እና የሥነ ልሳን ምሁር
ዶክተር ሮኒ ማዬር ምስል፦ Getie Gelaye

ዐዉደ ጥናት - ዘመናዊ የአማርኛ ማስተማርያ ለዉጭ ዜጎች

This browser does not support the audio element.

አማርኛን እንደ ዉጭ ቋንቋነት ማስተማር - መደበኛነትን ያማከለ የጋራ ስርዓተ ትምህርት የቋንቋ ችሎታና የምዘና ማዕቀፍ ዝግጅት

 

«የምኖረዉ ዋርሶ ነዉ፤ ዋርሶ በሚገኝ ዩንቨርስቲ የአማርኛ አስተማሪ ነኝ። አማርኛ ማስተማር የጀመርኩት ከ22 ዓመት በፊት ነዉ። በዋርሶ ዩንቨርስቲ ስምንት የአማርኛ ተማሪዎች አሉኝ። በየጊዜዉ እንዲሁ አማርኛን ለመማር የሚፈልግ ሰዉ አለ፤ ልክ እንደኛ። እኔ አማርኛ ቋንቋን መማር የጀመርኩት ከ 40 ዓመት በፊት ነዉ።»

በፖላንድ መዲና ዋርሶ በአፍሪቃ ቋንቋዎች እና ባህሎች ተቋም በሥነ-ልሳን ክፍል የአማርኛ ቋንቋአስተማሪ እና አስተርጓሚ ዶ/ር ኤቫ ዎልክ-ሶሬ የተናገሩት ነዉ።  በዋርሶ ዩንቨርስቲ፤ የአፍሪቃ ቋንቋዎች እና ባህሎች ተቋም፤ በሥነ-ልሳን ክፍል የአማርኛ ቋንቋ ክፍል መምህርት ዶ/ር ኤቫ፤ በአዉሮጳም ሆነ በኢትዮጵያ የአማርኛ ቋንቋ ጥናት ላይ በሚደረጉ ዐዉደ ጥናቶች ላይ በየጊዜዉ ይሳተፋሉ። ባለፈዉ ወር ጀርመን በሐምቡርግ ዩንቨርስቲ የእስያ እና አፍሪቃ ጥናቶች ተቋም ባዘጋጀዉ ዐዉደ ጥናት ላይ ተሳትፈዋል። አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ ላልሆኑ ቋንቋዉን መማር ለሚፈልጉ መማርያ የሚሆን የመጽሐፍ ዝግጅትን በተመለከተ በተካሄደ ዐዉደ ጥናት ላይ ተሳትፈዋል። ዶ/ር ኤቫ ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በተካሄደው ዐዉደ ጥናት ላይ እንደተሳተፉም ተናግረዋል።

ዶክተር ጌቴ ገላዬ እና ዶክተር ሮኒ ማዬርምስል፦ Getie Gelaye

በሰሜን ጀርመንዋ በሐምቡርግ ከተማ በተካሄደዉ በዚህ ዐዉደ ጥናት ላይ፣ ዶ/ር ኤቫ ዎልክ-ሶሬን ጨምሮ፤ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዉስጥ፣ ከእስራኤል ፣ ከቻይና ብሎም ከኢትዮጵያ የመጡ አማርኛ ቋንቋን የሚያስተምሩ መምህራን ተሳትፈዋታል። ዐዉደ ጥናቱ የአራት ዓመታት ዝግጅት እንደተደረገበት በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሩስያን ጨምሮ በተለዩ የአዉሮጳ ሃገራት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ሲሰጥ ከ100 ዓመት በላይ ሆኖታል።

የአማርኛ ፊደላት ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ለምሳሌ በጣልያኑ የኔፕልስ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛ ቋንቋ ትምርት በ1890ዎቹ መሰጠት መጀመሩን ዶ/ር ጌቲ ገላዬ ተናግረዋል። ላለፉት 125 ዓመታት በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ ነዉ።  በጀርመን የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላለፉት 105 ዓመታት ያለማቋረጥ እየተሰጠ መሆኑን ዶ/ር ጌቲ ገላዬ አክለዋል። 

በዐዉደ ጥናቱ ላይ በአዉሮጳ የሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ ምሁራን፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ከእስራኤል፤ ከቻይና እንዲሁም ከኢትዮጵያ የተገኙ የአማርኛ የሥነ-ልሳን ባለሞያዎች ተካፋይ ነበሩ።  

አማርኛ መማር እና መናገር ከጀመሩ ወደ ሠላሳ አምስት ዓመት እንደሆናቸዉ የነገሩን ጀርመናዊዉ የአፍሪቃ ቋንቋዎች ጥናት ምሁር ዶ/ር አንድርያስ ቬተር፤ ሌላዉ የዐዉደ ጥናቱ ተሳታፊ ነበሩ። እንደ ዶ/ር አንድርያስ በቅርቡ የተካሄደው ዐዉደ ጥናት፣ በተለይ አማርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻቸዉ ላልሆኑ ሰዎች፤ በደረጃ ለማስተማር እና የማስተማር ሂደቱ አንድ አይነት መርህንም የያዘ እንዲሆን ያሰበ እንደሆነ ተናግረዋል። ዶ/ር አንድርያስ አልፎ አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ የኤምባሲ ሠራተኞች፤ የስድስት ወራት የአማርኛ ቋንቋ ስልጠና በጀርመን የዉጭ ጉዳይ መስርያ ቤት እንደሚሰጡ ነግረዉናል።

አማርኛን እንደ ዉጭ ቋንቋ ማስተማር - መደበኛነትን ያማከለ የጋራ ስርዓተ-ትምህርት የቋንቋ ችሎታና የምዘና ማዕቀፍ ዝግጅትምስል፦ Getie Gelaye

የአፍ መፍቻቸው አማርኛ ያልሆነ እና ቋንቋዉን ለሚማሩ ፤ የማስተማር ስርዓቱ አንድ ወጥ እንዲሆን ያለመዉ ይህ ዐዉደ ጥናት ፣ገቢራዊ የሚሆነዉ መቼ ነዉ ስንል፤ በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር፣ ዶክተር ጌቲ ገላዬን ጠይቀናቸዋል። ሙሉ ዝግጅትን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Azeb Tadesse Hahn Azeb Tadesse
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW