ዓለምአቀፉ ስፖርት በ 2009 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2002በእግር ኳሱ መድረክ ታላቁ የዓመቱ ድርጊት እርግጥ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ኬፕታውን ላይ የተካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ነበር። በክለቦች ንጽጽር የስፓኙ ግንባር-ቀደም ክለብ ባርሤሎና በአንድ የውድድር ወቅት ስድሥት ድሎችን በመጎናጸፍ ልዩ ታሪክ አስመዝግቧል። የዓመቱ ታላቅ የአትሌቲክስ ትርዒት ደግሞ ዩሤይን ቦልትና ቀነኒሣ በቀለ ገነው የታዩበት በርሊን ላይ የተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነበር።
ደስታና ሃዘን የተዋሃደው የእግር ኳስ ዓመት
መጪው አዲስ ዘመን 19ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪቃ ምድር የሚካሄድበት ነው። በመሆኑም በቅርቡ ኬፕ-ታውን ላይ የተካሄደው የምድብ ዕጣ-አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ራሱ የተለየ ታሪካዊ ባሕርይ ነበረው። ደቡብ አፍሪቃ መላውን ክፍለ-ዓለም ወክላ ዓለምን በዚህ ታላቅ ፌስታ ለማስተናገድ መዘጋጀቷን በደመቀ ትርዒት ስታበስር ከእንግዲህ የሚቀረው ዋንጫዋ በዚያው እንድትቀር በማድረግ የተለየ ታሪክ መሥራቱ ብቻ ነው። የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በበኩላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪቃን ምድር የምትረግጠው ዋንጫ ተመልሳ አትወጣም ብለዋል። ይህ ምናልባትም የአፍሪቃ እግር ኳስ ዛሬ የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ሲታሰብ ብዙ የተጋነነ አይሆንም። አስተናጋጇን ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ ስድሥት የአፍሪቃ አገሮች የውድድሩ ተሳታፊዎች ሲሆኑ ቢቀር በዓመቱ ብራዚልን በአስደናቂ የፍጻሜ ግጥሚያ በማሸነፍ ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶችን የዓለም ዋንጫ ያገኘችው ጋናና አይቮሪ ኮስት በብዙዎች አስተያየት ለትግሉ የሰከኑት ናቸው። እርግጥ ሁሉንም ከመንፈቅ በኋላ እንደርስበታለን።
በዚህ በመገባደድ ላይ በሚገኘው 2009 ዓ.ም. በክለቦች ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ዘንድሮ ታሪክ ሰሪው የስፓኙ ሻምፒዮን ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ነበር። ባርሣ ባለፈው ቅዳሜ አቡ-ዳቢ ላይ የአርጄንቲና ታጋጣሚውን ኤስቱዲያንቴስን 2-1 በመርታት ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የክለቦች ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። ታላቁ የካታሎኒያ ክለብ ከዚሁ ሌላ የስፓኝ ሊጋ፣ ኪንግስ-ካፕ፣ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ፤ እንዲሁም የስፓኝና የአውሮፓ ሱፐር-ካፕ፤ በአጠቃላይ በዓመቱ የስድሥት ድሎች ባለቤት በመሆን በዓለም ላይ አቻ ያልታየለት ነበር። አሠልጣኙ የቀድሞው የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ጉዋርዲዮላ ካለፈው ቅዳሜ ዋንጫ በኋላ ከደስታ ብዛት እንባ በእንባ እስከመሆን ነው የደረሰው። ባርሤሎና በኤስቱዲያንቴስ 1-0 ከተመራ በኋላ የጨዋታውን ውጤት ሲቀይር ሁለተኛዋን የድል ጎል በማስቆጠር የአገሩን ልጆች ለሽንፈት የዳረገው ደግሞ የአርጄንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር።
ሜሢን ካነሣን አይቀር በአርጄንቲና የማራዶና ተተኪ ሆኖ የሚቆጠረው የኳስ ጠቢብ ዘንድሮ ድንቁ የአውሮፓ ተጫዋች በመባልም በቅርቡ ተመርጧል። ፊፋ ዛሬ ዙሪክ ላይ በሚያካሂደው ምርጫ ደግሞ የዓመቱ የዓለም ድንቅ እግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ ለመሰየምም ትልቅ ዕድል ነው ያለው። ቀደምት ተፎካካሪዎቹ ያለፈው ዓመት ተሸላሚ የፖርቱጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶና የብራዚሉ ካካ ይበልጡታል ተብሎ አይጠበቅም። ያም ሆነ ይህ በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው ውድድር በአብዛኛው ወደ መጀመሪያው ዙር ፍጻሜ ሲዳረስ በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ዓመቱ የሚገባደደው ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ በረኛ ሮበርት ኤንከ አሳዛኝ አሟሟት ጥላውን አሳርፎበት ነው። ኤንከ በፕሮፌሺናሉ እግር ኳስ ውስጥ ባለው ግፊት የደረሰበትን የመንፈስ ችግር ሸፍኖ ይዞ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሕዳር ወር ሕይወቱን እስከማጥፋት ሲደርስ ሁኔታው በተለይም ለወጣቶች የስፖርት ተሃንጾ ሃላፊነት ያለባቸውን የፌደሬሺን ባለሥልጣናት ብቻ ሣይሆን ሕብረተሰቡን በሰፊው ያነጋገረረ ጉዳይ ነበር።
የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቴዎ ስቫንሲገር በኤንከ የሃዘን ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር ”በሕይወት ውስጥ ትልቁ ነገር እግር ኳስ ብቻ አይደለም” ሲሉ ነበር ወላጆችና ወጣቶችን የሚያሰለጥኑ ክለቦች ከግፊት ቆጠብ እንዲሉ ያስገነዘቡት። በእግር ኳሱ ዓለም የኤንከ ሞት ካስከተለው ሃዘን ሌላ ተገባዳጁ ዓመት የስፖርቱን ዝና የሚያጎድፍ የውርርድ ማፊያ ወንጀል ተጋልጦ የወጣበትም ነበር። ይሄው የዓመቱ ታላቅ ወንጀል ገና በመጣራት ደረጃ ላይ በመሆኑ በመጪውም ዓመት አነጋጋሪ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። የውርርድ ማፊያው ወንጀል እንደገና ዓለምአቀፉን እግር ኳስ ሃፍረት ላይ ሲጥል ከ 200 የሚበልጡ ግጥሚያዎች ውጤት የተጭበረበረ፤ ማለት በማፊያው ተጽዕኖ የተበረዘ መሆኑ እስካሁን ተደርሶነታል። በጀርመንም 32 ግጥሚያዎች መበረዛቸው ሲታወቅ እያደር ገና ብዙ ጉድ ሊወጣም የማይችልበት ምክንያት የለም። የውርርድ ማፊያው ይህን የሚያድገው ተጫዋቾችን ጭምር በመጠቀም ሲሆን የሚያሳዝነው በዛሬው የኤኮኖሚ ቀውስ ዘመን ብዙ ገንዘብ አፍሶ ስታዲዮም የሚገባው ኳስ አፍቃሪ የውሸት ጨዋታ ተመልካች መደረጉ ነው።
የዓመቱ ታላላቅ አትሌቶች ቦልትና ቀነኒሣ
በተገባዳጁ ዓመት ቀደም ባለው የ 2008 የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ጨዋታ ላይ እንደታየው ሁሉ በአትሌቲክሱ መድረክ ታላላቆቹ እንደገና የጃማይካው የአጭር ርቀት መንኮራኩር ዩሤይን ቦልትና የኢትዮጵያ አኩሪ ተጠሪ ቀነኒሣ በቀለ ነበሩ። ሁለቱ ድንቅ አትሌቶች ባለፈው ነሐሴ ወር በርሊን ላይ ተካሂዶ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር እያንዳንዳቸው ድርብ ድል በማስመዝገብ ልዕልናቸውን እንደገና አስመስክረዋል። የበርሊኑን የዓለም ሻምፒዮና ካነሣን በአጠቃላይ ውጤቱ እርግጥ ለኢትዮጵያ የሰመረ አልነበረም። ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ ጠንካራ አትሌቶች በእግር ጉዳት የተነሣ አለመሳተፋቸው ብዙ የሜዳሊያ ዕድል ከንቱ እንዲሆን አድርጓል። በዚሁ የተነሣም የኢትዮጵያ ብርቱ ተፎካካሪ ለሆነችው ለኬንያ በር ከፋች ነበር የሆነው። ኬንያ ማራቶንን ጨምሮ በማሸነፍ አራት ወርቅ፣ አምሥት ብርና ሁለት ናስ ሜዳሊያዎች በማግኘት በጠቅላላ ውጤት ሩሢያን አስከትላ ሶሥተኛ ለመሆን በቅታለች። አሜሪካ በአሥር ወርቅ አንደኝነቱን ስትይዝ ከሁሉም አስደናቂው ደግሞ ጃሜይካ በሰባት ወርቅ ሁለተኛ መሆኗ ነበር። ዓመቱ የጃማይካ ወንድና ሴት አትሌቶች በተለይ በአጭር ርቀት ሩጫ አሜሪካን ከቆየችበት ዙፋን ያወረዱበት ነበር ሊባል ይቻላል።
የበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ደቡብ አፍሪቃዊቱ የ 800 ሜትር ሩጫ አሸናፊ የካስተር ሤሜኒያ የጾታ ባህርይ ብዙ ሲያከራክር የታየበትም ነበር። የ 18 ዓመቷ አትሌት ወዲያው ሜዳሊያዋን ተቀብላ ደስታዋን ሳትጨርስ ወንድ ናት ወይስ ሴት? በሚለው የመገናኛ አውታሮች የዜና ቅብብል መዓት ትወጠራለች። ሁኔታው በደቡብ አፍሪቃ ባለሥልናትና በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር መካከል የውዝግብ መንስዔ እስከመሆንም ደርሶ ነበር። በጉዳዩ የአያያዝ ድክመት የደቡብ አፍሪቃ የአትሌቲክስ ማሕበር ሃላፊ ከስልጣን ሲሰናበቱ ሤሜኒያ ከብዙ ውጣ-ውረድ በኋላ በመጨረሻ የወርቅ ሜዳሊያዋንና በአሸናፊነት ያገኘችውን ገንዘብ ሳትነጠቅ ቀርታለች። የደቡብ አፍሪቃ አትሌቲክስ ማሕበር በውድድሩ ዋዜማ ምርመራ ማካሄዱ የኋላ ኋላ ሲገለጽ ውጤቱን በሚገባ ማጤንና አትሌቷን ከወዲሁ በጉዳዩ ማነጋገሩ በጠቀመ ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ አትሌቶች መለስ እንበልና እርግጥ የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ልዩ ተሰጥኦና ብቃት እንዳላቸው ሲያስመሰክሩ በዓመቱ የዓለምን ትኩረት ከሳቡት ረጫዎች አንዱ የመስከረሙ የበርሊን ማራቶን ነበር። ሃይሌ ገ/ሥላሴ አንድ ዓመት ቀደም ሲል በዚያው ያስመዘገበውን ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ባይችልም ድሉን ግን መልሶ ይደግመዋል። በዓለም የማራቶን ታሪክ ውስጥ ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች በመሮጥ የመጀመሪያው የሆነው ሃይሌ ከግቡ ለመድረስ ሩቡ ርቀት ያህል ሲቀረው በሙቀት ሳቢያ ለዘብ ይበል እንጂ እስከ ሰላሣኛው ኪሎሜትር ድረስ በአዲስ ክብረ-ወሰን የጊዜ ክልል ውስጥ ነበር። ይህም ራሱን የቻለ ትልቅ የጥንካሬ ምልክት ነው።
የፎርሙላ-አንድ ዓመት
በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው ጄሰን ባተን ከ 17 ውድድሮች በኋላ በአጠቃላይ 95 ነጥቦች ዓመቱን በአንደኝነት ፈጽሟል። 11 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ የሆነው ወጣቱ የጀርመን ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ነው። የ 29 ዓመቱ ባተን አሥረኛው የብሪታኒያ የፎርሙላ-አንድ ሻምፒዮን ሲሆን በሚቀጥለው የውድድር ወቅት ክብሩን ለማስጠበቅ ምናልባትም ታሪክን ጭምር ማሸነፍ ሳይኖርበት አይቀርም። እስካሁን ከብሪታኒያ ቀደምቶቹ ድሉን የደገመ አንድም አልነበረም። በዘንድሮው የውድድር ሂደት እርግጥ ዋነኛው ተደናቂ የ 18 ዓመቱ ወጣት ጀርመናዊ ዜባስቲያን ፌትል ነው። ፌትል በዚህ በጀርመን ባለፈው ምሽት የዓመቱ ስፖርተኛ ተብሎ ተሽልሟል። ሌላው በዓመቱ መገባደጃ በአውቶሞቢሉ የስፖርት መድረክ ላይ ትኩረትን የሳበው የሰባት ጊዜው ሻምፒዮን ጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር ወደ ውድድሩ የመመለሱ ዜና ነው። የ 41 ዓመቱ ሹማኸር የመመለስ ሃሣብ ብዙዎች አድናቂዎቹን አስደስቷል፤ መልሱን ለማረጋገጥ የሚቀረው ከሜርሤደስ ጋር መፈራረሙ ነው።
መሥፍን መኮንን፣
ተክሌ የኋላ፣