ዓለምአቀፉ ስፖርት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2005ሁለቱም ውድድሮች ጠንካራ የጸጥታ ጥበቃ በሰፈነበት ሁኔታ ሲካሄዱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ተሳታፊዎችም የቦስተኑን ማራቶን ሰለቦች በህሊና ጸሎት አስበዋል። በውድድሩ በሃምቡርግ ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊው አትሌት ልመንህ ጌታቸው ደግሞ ሁለተኛ ሆኗል። በሴቶች ቀደምት የሆነችው የሊቱዋኒያዋ ዲያና ሎባቼቭስኪ ነበረች።
በዓለም ላይ ቀደምት ከሚባሉት አንዱ በሆነው በለንደን ማራቶን የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ጸጋዬ ከበደ ያልተጠበቀው አሸናፊ ሊሆን በቅቷል። በለንደን ኦሎምፒክ ወቅት ለተሳትፎ ሳይመረጥ ቀርቶ የነበረው ጸጋዬ ተፎካካሪውን ኤማኑኤል ሙታይን በመጨረሻዎቹ ኪሎሜትሮች ደርቦ ከግቡ ሲደርስ አየለ አብሸሮም ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሴቶች ኬንያዊቱ ኤድና ኪፕላጋት ስታሸንፍ ዩኪኮ አካባ ከጃፓን ሁለተኛ፤ እንዲሁም አጸደ ባይሣና መሰለች መልካሙ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነዋል።
የለንደኑ ኦሎምፒክ አሸናፊ ቲኪ ገላና ደግሞ በሩጫው ባጋጠማት መሰናከል ውድድሩን 16ኛ በመሆን ፈጽማለች። የውድድሩን አጠቃላይ ሂደትና የኢትዮጵያን አትሌቶች ሁኔታ በተመለከተ በቦታው ተገኝታ የነበረችውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ዛሬ በስልክ አነጋግረናል።
በዚህ በአውሮፓ ሰንበቱን እንደተለመደው የቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር ሲካሄድ የውድድሩ ወቅት ሊያበቃ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ሻምፒዮንነቱም ይበልጥ እየለየለት መሄዱን ቀጥሏል። ቢሆንም በዚህ ሣምንት የተመልካቹን ሁሉ ልብ ስቦ የሚገኘው በአራቱ የጀርመንና የስፓኝ ክለቦች መካከል ነገና ከነገ በስቲያ የሚካሄዱት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ናቸው። በነገው ምሽት የመጀመሪያ ግጥሚያ ባየርን ሙንሺን ከባርሤሎና የሚገናኝ ሲሆን ዶርትሙንድ ደግሞ በማግሥቱ የሬያል ማድሪድ አስተናጋጅ ነው። የመልሱ ግጥሚያዎች ከሣምንት በኋላ ይካሄዳሉ። እርግጥ ከሁሉም በላይ የባየርንና የባርሤሎና ግጥሚያ የዓመቱ ታላቅ ትርዒት ነው።
ከስፖርቱ አንጻር ሁኔታው ይህን የመሰለ ሲሆን በሌላ በኩል የባየርን ሙንሺን ፕሬዚደንት የኡሊ ሄነስ ግብር ሳይከፍል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ስዊስ ባንኮች ማሸሽ መታወቅ ከሰንበቱ ወዲህ በዚህ በጀርመን ዓቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። በታላቁ የባየርንና የባርሤሎና ግጥሚያ ዋዜማ ይህ ሃቅ መከሰቱ በክለቡ ተጫዋቾች መንፈስ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ ለጠቅላላው ቡንደስሊጋስ ምን ማለት ነው? የዶቼ ቬለ የጀርመንኛ ፕሮግራም ክፍል የስፖርት ጋዜጠኛ ሽቴፋን ኔስትለር እንደሚለው ከወዲሁ እንዲህ ብሎ መናገሩ ቀላል አይሆንም።
«ጥያቄው ይሄ ታሪክ ቡድኑን ሰላም ሊያሳጣ ይችላል ወይ ነው። ምክንያቱም ቡድኑን ነገ በዚህ ዓመት ታላላቅ ከሚባሉት ግጥሚያዎች አንዱ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከባርሤሎና ጋር የሚያደርገው ይጠብቀዋል። ግጥሚያው ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ወሣኝ ነው። ታዲያ በዚህ ሰዓት በታላቅ አርአያነት ጭምር ሲታይ የኖረው የክለቡ ፕሬዚደንት ኡሊ ሄነስ ድንገት በሕገ ወጥ የገንዘብ ሽግሽግ ወቀሣ መወጠር ጥቂትም ቢሆን ተጽዕኖ ማሳደሩ ይቀራል ወይ? የሚሆነው እያደር የሚታይ ይሆናል»
ኡሊ ሄነስ በኳስ ተጫዋችነትና በክለብ ባለሥልጣንነት ብቻ ሣይሆን የፋብሪካ ባለቤት በመሆንም ዝናን ያተረፈ ሰው ነው። ማሕበራዊ አስተዋጽኦ በማድረግ ቢወደስም በሌላ በኩል በጠንካራ አንደበቱ ብዙ ተቺዎችን ማፍራቱም አልቀረም። እናም አሁን የተፈጠረው ሁኔታ በቡንደስሊጋው ላይም አንዳች ተጽዕኖ የለውም ወይም አይኖረውም ለማለት አይቻልም።
«ኡሊ ሄነስ ከብዙዎች ጋር መጋጨትን የሚወድ እንደነበር ነው ያለፉት ዓመታት ያሳዩት። ሆኖም ለ 30 ዓመታት የባየርን ሙንሺን ማኔጀር በመሆን ክለቡን ግዙፍ አድርጎ ለማነጽ ችሏል። በዚህ ችሎታው ደግሞ ሁሉም የሚያደንቀው ሲሆን የግል ባሕርዩ ግን ቅራኔ የተመላው ነው። እናም በቡንደስሊጋው ውስጥ ወዳጆችን ብቻ ሣይሆን ቀናተኞችና ተቃዋሚዎችን ጭምር አፍርቷል። እነዚህ ደግሞ አሁን እሰይ ማለታቸው አይቀርም። በጥቅሉ ጉዳዩ በቡንደስሊጋውና በአጠቃላይም በጀርመን እግር ኳስ ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም አይባልም»
ያም ሆነ ይህ ኡሊ ሄነስ ቃሉን አላከበረም። በሌሎች ላይ የጣለውን መስፈርት ራሱ አለማክበሩ ታዲያ ብዙዎችን ሲያስገርም ትራንስፓረንሢይ ኢንተርናሺናል የተሰኘው ግልጽነትን የሚከታተል ድርጅት የዓለምአቀፍ እግር ኳስ ጉዳይ ሃላፊ ሢልቪያ ሼንክም የጠበቁት አልነበረም።
«ኡሊ ሄነስ ራሱ ማሕበራዊ ተግባርም እንደሚያከናውን ሰው ግልጽ ንግግርን የሚያከብር ነው ብዬ ጠብቄ ነበር። ራሱ የሚሰብከውን ያከብራል የሚል ተሥፋ ነበረኝ። ግን ነገሩ እንዲህ አልሆነም»
ከዚህ አንጻር የባየርኑ ፕሬዚደንት ዝና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየጎደፈ መሄዱ የማይቀር ሲሆን ክለቡን በመምራት ይቀጥል አይቀጥል እያደር የሚታይ ጉዳይ ይሆናል።
ከዚህ ሻገር እንበልና በአፍሪቃ እግር ኳስ ሻምዮና ሊጋ ውድድር የኢትዮጵያው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሰንበት ካይሮ ላይ ከግብጹ ዛማሌክ 1-1 በመለያየት ወደ ምድቡ ዙር ለመሻገር ጥሩ ሁኔታን ለማመቻቸት በቅቷል። የአምሥት ጊዜው የሻምፒዮና ሊጋ ዋንጫ አሸናፊ ዛማሌክ ለመልሱ ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ መጓዝ የሚኖርበት ሲሆን ወደፊት የመራመዱ ዕድል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደላ ነው የሚመስለው።
በተቀረ ትናንት ባሕሪይን ላይ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ ጀርመናዊው ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ሆኗል። ያለፉት ሶሥት ዓመታት ሻምፒዮን በዘንድሮው ውድድር ቀዳሚ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
መሥፍን መኮንን
ተክሌ የኋላ