1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ ስፖርት

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2005

ብራዚል ውስጥ የሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አጅቦት የተካሄደው የፊፋ ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር በአስተናጋጇ አገር አሸናፊነት ተፈጽሟል።

ምስል Reuters

የብራዚል ብሄራዊ ቡድን «ሤሌሣዎ» የዓለምና የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት የሆነችውን ስፓኝን ባለፈው ሌሊት በዝነኛው ማራካና ስታዲዮም በተደረገ ፍጻሜ ግጥሚያ 3-0 ሲረታ በዚያው በብራዚል የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አንድ ዓመት ቀርቶት ሳለ ትንሣዔ ማድረጉ ሰምሮለታል።

የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በድንቅ አጥቂዎቹ በኔይማርና በፍሬድ፤ በተከላካዩ በዴቪድ ሉዊስና በመሃል ሜዳው መንኮራኩር በፓውሊኞ አንቀሳቃሽነት ድንቅ ጨዋታ ሲያሳዩ 29 ጊዜ ሳይሸነፍ የቆየው የስፓኝ ቡድን የድል ጉዞ እንዲያበቃ አድርገዋል። ፍሬድ ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ለብራዚል የመጀመሪያዋን ጎል ሲያስገባ ኔይማርም ከእረፍት በፊት በ 41 ኛዋ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል ያስቆጥራል። ብራዚል በፍሬድ አማካይነት ሶሥተኛ ጎል በማስገባት የስፓኝ ተሥፋ እንዲመነምን ያደረገችው ደግሞ ከእረፍት መልስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ነበር።

የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቪንቼንቴ-ዴል-ቦስክ የተሻለው ቡድን ብራዚል ነበር ሲሉ ሽንፈታቸውን አምነው ሲቀበሉ በሌላ በኩል የብራዚል ተጫዋቾች የፈጸሟቸውን 26 የረገጣና የጠለፋ ድርጊቶች በማንሣት ትችት መሰንዘራቸውም አልቀረም። የብራዚሉ አሰልጣኝ ፌሊፔ ስኮላሪ በበኩላቸው ብሄራዊው ቡድን ለአምሥተኛ ጊዜ የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በመብቃቱ መደሰቱን ነው የመረጡት። ስኮላሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሶሥት ለዜሮ ውጤት ማሸነፉን የጠበቁት ነገር እንዳልነበር አስረድተዋል። በ 2002 ብራዚልን ለዓለም ዋንጫ አብቅተው የነበሩት አሰልጣኝ በውድድሩ በጠቅላላ በታየው አጨዋወት ብቁ ቡድን አለን ብለው ሊመኩና በመጪው የዓለም ዋንጫም ለከፍተኛ ድል ሊያልሙ ይችላሉ።

ምስል Reuters

የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ዓመታት የቀድሞ ግርማ-ሞገሱን አጥቶና ግንባር ቀደም ቦታውን አስረክቦ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ለብራዚል ያለፈው ሌሊት የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ድል በተከታታይ ሶሥተኛው መሆኑ ነበር። የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ጃፓንን፣ ሜክሢኮን፣ ኢጣሊያን፣ ኡሩጉዋይንና ስፓኝን በሙሉ ሲያሸንፍ የስኮላሪ በአሰልጣኝነት መመለሰ ፍሬያማ መሆኑን ነው ያሳየው። እርግጥ ሴሌሳዎው ለስድሥተኛ የዓለም ዋንጫ ለመብቃት በቀሪው ጊዜ ብዙ ስራ ነው የሚጠብቀው። ምክንያቱም የቀድሞውን ብራዚል አሁንም ገና አላየንም።

በኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ኢጣሊያም ቢሆን ግሩም ጥንካሬ ለማሳየት በቅታለች። ብሄራዊው ቡድን፤ በአገሩ እንደሚጠራው «ስኩዋድራ አዙሪ» በውድድሩ ሂደት የተገታው በፍጹም ቅጣት ምቶች በለየለት ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ በስፓኝ ለጥቂት 7-6 ከተረታ በኋላ ነበር። በጨዋታው እንዲያውም ጠንካራው ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ምሽት ለሶሥተኝነት ከኡሩጉዋይ ጋር ባደረገው ግጥሚያም ጨዋታው በፍጹም ቅጣት ምት ሲለይለት ዕድል እንደገና አልከዳውም። በከባድ ሙቀት የተካሄደው አድካሚ ግጥሚያ ከመደበኛና ጭማሪ ጊዜ በኋል የተፈጸመው 2-2 ነበር።

ኢጣሊያ በመጨረሻ 3-2 በማሸነፍ ሶሥተኛ ለመሆን በመብቃቷ በተለይም ሶሥት የኡሩጉዋይ ፍጹም ቅጣት ምቶችን በመያዝ ከንቱ ያደረገውን ድንቅ በረኛዋን ጃንሉዊጂ ቡፎንን ልታመሰግን ይገባታል። በተረፈ ዘንድሮ ባርሤሎናን የሚቀላቀለው የብራዚሉ ወጣት ኮከብ ኔይማር የውድድሩ ድንቅ ተጫዋች ሲባል በጎል አግቢነት ደግሞ እያንዳንዳቸው አምሥት ያስቆጠሩት የስፓኝና የብራዚል አጥቂዎች ፌርናንዶ ቶሬስና ፍሬድ ወርቃማ ጫማ ተሸልመዋል።

በተረፈ የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ከጎርጎሮሳውያኑ 1992 ዓ-ም ወዲህ ዘጠኝ ጊዜ ሲካሄድ አርጄንቲና፣ ዴንማርክና ሜክሢኮ እያንዳንዳቸው አንዴ፣ ፈረንሣይ ሁለቴና ቀደምቷ ብራዚልም አምሥት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።

ምስል DW/H. Turuneh

በብራዚል ላይ ካተኮርን በመጪው 2014 ዓ-ም በዚያው ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለመድረስ በአፍሪቃ በሚደረገው ማጣሪያ በምድብ-አንድ ኢትዮጵያ የነበራት የአምሥት ነጥቦች የበላይነት ወደ ሁለት መልሶ ማቆልቆሉን ሱዊስ ውስጥ ተቀማጭ የሆነው የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በይፋ አረጋግጧል። ኢትዮጵያ ሰሥት ነጥቦች የሚቀነሱባት በቢጫ ካርዶች ክምችት የተነሣ ማረፍ የነበረበትን ምንያህል በየነን ከቦትሱዋና ጋር ባካሄደችው ግጥሚያ በማሰለፏ ነው።

በጊዜው ኢትዮጵያ ቦትሱዋናን 2-1 ማሸነፏ አይዘነጋም። ፊፋ ለዚሁ ውዥንብር ስህተቱን ባመነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ላይ የ 6,300 ዶላር መቀጮም ጥሏል። ውሣኔውን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ላይ የ 3-0 ድል የተፈረደላት ቦትሱዋና በዚሁ በምድብ-አንድ ውስጥ ከሶሥት ወደ ስድሥት ነጥቦች ከፍ ለማለት ችላለች። ኢትዮጵያ 10 አላት፤ ደቡብ አፍሪቃም በ8 ነጥቦች በቅርብ ትከተላለች።

የፊፋ ብያኔ አዲስ አበባ ላይ ተሸንፋ ከውድድሩ ተሰናብታ ለነበረችው ለደቡብ አፍሪቃ ወደ ፊት የመዝለቅ አዲስ ዕድልን የሚሰጥ ሲሆን ኢትዮጵያ በፊታችን ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ከማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ በምታደርገው ጨዋታ ነጥብ እንዳትጥል እጅጉን መጠንቀቅ ይኖርባታል። ፊፋ በሱዳንና በጋቦን ላይ ተመሳሳይ ቅጣት ሲያደርግ የቶጎንና የኤኩዋቶሪያል ጊኒን ሁኔታም እየመረመረ ነው።

ምስል Reuters

ትናንት እንግሊዝ-በርሚንግሃም ላይ ተካሂዶ በነበረው የአትሌቲክስ ዳያመንድ-ሊግ ውድድር የኢትዮጵያ ተሳታፊዎችም ከሞላ-ጎደል ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በቅተዋል። በወንዶች 100 ሜትር ጃማይካዊው ኔስታ ካርተር በ 9,99 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በ 110 ሜትር መሰናክል ቀዳሚ የሆነው ደግሞ የባርቤዶሱ ራያን ባርትዌይት ነበር። በ 800 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊው መሐመድ አማን የደቡብ አፍሪቃ ተፎካካሪውን አንድሬ ኦሊቪየርን በማስከተል ሲያሸንፍ አሜሪካዊው ኤሪክ ሶዊንስኪም ሶሥተኛ ወጥቷል።

በ 1,500 ሜትርም ድሉ የኢትዮጵያ ነበር። አማን ወቴ ሁለት የሞሮኮ ተፎካካሪዎቹን አብዳላቲ ኢጉደርንና ሞሐመድ ሙስታዊን ከኋላው በማስቀረት አሸናፊ ሆኗል። በሌላ በኩል በ 5000 ሜትር ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ሞ ፋራህ ለኢትዮጵያ አትሌቶች የሚበገር አልሆነም። የለንደኑ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን አሸናፊ ሲሆን የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎቹ የኔው አላምረው፣ ሃጎስ ገ/ሕይወትና ኢብራሂም ጄይላን ከሁለት እስከ አራት በመከታተል ከግባቸው ደርሰዋል።

በሴቶች 200 ሜትር ናይጄሪያዊቱ ብሌሢንግ ኦካግባሬ ስታሸንፍ በ 400 ሜትር ደግሞ የብሪታኒያዋ ክሪስቲን ኦሁሩጉ ቀደምቷ ሆናለች። በ 800 ሜትርም ሁለት የብሪታኒያ አትሌቶች ጀሢካ ጀድና ማሪሊን ኦኮሮ ሲያሸንፉ ፋንቱ ማጂሶ ሶሥተኛ ለመሆን በቅታለች። በ 1,500 ሜትር ባለድሏ ለስዊድን የምትወዳደረው አበባ አረጋዊ ነበረች። ከዚሁ ሌላ በ 3000 ሜትር መሰናክል ድሉ የኬንያ ሲሆን ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛ፣ ሕይወት አያሌው ሶሥተኛና እቴነሽ ዲሮም አምሥተኛ በመሆን ብርቱ ጥንካሬ አሳይተዋል።

ምስል picture-alliance/dpa

ባለፈው ቅዳሜ በባስቲያ የተጀመረው ቱር-ዴ-ፍራንስ የቡስክሌት እሽቅድድም ዛሬ ሶሥተኛ ደረጃ ውድድሩን ያጠቃልላል። በውድድሩ መክፈቻ ደረጃ ብዙዎች ተወዳዳሪዎች በተጨናነቀ ጅማሮ የተነሣ ተጋጭተው ሲሰናከሉና የተወሰኑትም ጉዳት ሲደርስባቸው ጀርመናዊው ማርሤል ኪትል አሸንፎ ቢጫውን ሸሚዝ መረከቡ የተጠበቀ አልነበረም። ሆኖም ኪትል ትናንት በሁለተኛው ደረጃ በአጃቺዮ የ 154 ኪሎሜትር እሽቅድድም አንደኝነቱን ለቤልጂጉ ተወላጅ ለያን ባከላንትስ ማስረከቡ ግድ ነው የሆነበት።

ውድድሩ በዛሬው ዕለት በሶሥተኛ ደረጃው የቀጠለ ሲሆን ታሪካዊቱን የናፖሊዮን ቦናፓርትን የትውልድ ስፍራ የኮርሢካን ደሴት 145 ኪሎሜትር ርቀት የሚያቋርጥ ነው። ታላቁ የቢስክሌት እሽቅድድም ቱር-ዴ-ፍራንስ መቶኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ወቅት «የውበት ደሴት» ወደተሰኘችው የሜዴትራኒያን ደሴት ኮርሢካ ሲዘልቅም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

ውድድሩ ዛሬም እንዳለፉት ቀናት ሁሉ በሞቃት አየር የሚካሄድ ሲሆን ቢስክሌተኞቹን የ 3,3 ኪሎሜትር ኮረብታማ መንገድ ፤ ከባድ ዳገትም ይጠብቃቸዋል። እሽቅድድሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈረንሣይ ዋና ምድር ከኒስ የሚደርሰው ነገ በአራተኛ ደረጃው ነው።

ምስል Getty Images

በትናትናው ዕለት ተካሂዶ በነበረው የብሪታኒያ ታላቅ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው ዘዋሪ ኒኮ ሮዝበርግ አሸናፊ ሆኗል። ከመጀመሪያው ረድፍ የተነሣው የብሪታኒያ ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን በአገሩ ሳይቀናው በጎማ ብልሽት የተነሣ ሲሰናከል ያለፉት ሶሥት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል እንዲያውም በቴክኒካዊ ችግር ውድድሩን ማቋረጥ ግድ ነው የሆነበት።

በእሽቅድድሙ ከሮዝበርግ ቀጥሎ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሁለተኛ ሲወጣ የፌራሪው ዘዋሪ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶም ሶሥተኛ ሆኗል። ሉዊስ ሃሚልተን አራተኛ፣ ኪሚ ራይኮነን አምሥተኛ! በአጠቃላይ ነጥብ ፌትል በ 132 መምራቱን ሲቀጥል አሎንሶ በ 111 ነጥቦች ሁለተኛ በመሆን ልዩነቱን ጠበብ ለማድረግ ችሏል፤ በ 98 ነጥቦች ሶሥተኛው የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ነው።

ምስል picture-alliance/dpa

እንግሊዝ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የዊምብልደን የቴኒስ ውድድር ወደ አራተኛ ዙሩ ሲሻገር በዛሬው ዕለትም ጠንካራ ግጥሚያዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ከነዚሁ መካከልም ታላላቆቹን ኮከቦች ኖቫክ ጆኮቪችንና ሤሬና ዊሊያምስን የመሳሰሉትን የሚጠቀልሉ ይገኙበታል። የሚጫወቱት ከጀርመናውያን ጋር ሲሆን ጆኮቪች ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ለማለፍ ከቶሚይ ሃስ፤ ሤሬና ዊሊያምስም የዛቢነ ሊዚኪ ተጋጣሚዎች ናቸው።

ከዚሁ ሌላ የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ከሩሢያው ተወላጅ ከሚካኢል ዩዥኒ፣ የስፓኙ ዴቪድ ፌሬር ደግሞ ከክሮኤሺያው ኢቫን ዶዲግ ይገናኛሉ። ከዛሬው ዕለት ግጥሚያዎች በወቅቱ የተጠቃለሉ ሲኖሩ በሴቶች ነጠላ የቤልጂጓ ኪርስተን ፒፕከንስ ኢጣሊያዊቱን ፍላቪያ ፓኔታን፤ እንዲሁም ፔትራ ክቪቶቫ ከቼክ ሬፑብሊክ የስፓኟን ካርላ-ሱዋሬስ-ናቫሮን በየፊናቸው በሁለት ምድብ ጨዋታ አሸንፈዋል። የቻይናዋ ሊ ናም ኢጣሊያዊቱን ሮቤርታ ቪንቺን አሸንፋ ለሩብ ፍጻሜው አልፋለች።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW