1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ሰኞ፣ መጋቢት 17 2004

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የሻምፒዮንነቱ ፉክክር ይበልጥ ቅርጽ እየያዘና ውድድሩም ቀስ በቀስ ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ነው። በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የሻምፒዮንነቱ ፉክክር ይበልጥ ቅርጽ እየያዘና ውድድሩም ቀስ በቀስ

ምስል DPA

ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ነው። በስፓን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያል ማድሪድ ከሁለት ተከታታይ እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ እንደገና ለድል በመብቃት ባርሤሎናን በስድሥት ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ መምራቱን ቀጥሏል። ሬያል ማድሪድ ሬያል ሶሲየዳድን በለየለት ሁኔታ 5-1 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ካሪም ቤንዜማ እያንዳንዳቸው ሁለት፤ እንዲሁም ቀሪዋን ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበር።

ሆኖም ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪኞ ባለፈው ረቡዕ ግጥሚያ ዳኛን በመተቸት ከመቀመጫው በመታገዱ በዚህ ሰንበትም ጨዋታውን ከርቀት መመልከቱ ግድ ነው የሆነበት። የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ሊጠቃለል ዘጠኝ ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ አሁን ሬያል ማድሪድ ሊጋውን በ 75 ነጥቦች ይመራል። ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ ሬያል ማዮርካን 2-0 ሲረታ በ 69 ነጥቦች ሁለተኛ ነው።

ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሣ ብቸኛው የሬያል ማድሪድ ተፎካካሪ ሲሆን የሪያል አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአሥር ወደ ስድሥት ማቆልቆል የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ያለውን ተሥፋ ይበልጥ እንዳጠናከረ ጨርሶ አያጠራጥርም። ሶሥተኛው ቫሌንሢያ በጌታፌ 3-1 በመሸነፍ ባለፈው ስንበትም ይብስ ሲያቆለቁል ከሁለተኛው ከባርሤሎና እንኳ 23 ነጥቦች ይለዩታል። እንግዲህ የስፓኝ ላ-ሊጋ ዘንድሮ ከመቼውም የበለጠ የሁለቱ ዝነኛ ክለቦች የሬያልና የባርሣ ልዕልና የሰፈነበት ሆኖ ነው የሚገኘው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምቱ ማንቼስተር ዩናይትድ ሰንበቱን ምንም እንኳ ባይጫወትም በደስታ ነው ያሳለፈው። ለዚህም ምክንያቱ የቅርብ ተፎካካሪው ማንቼስተር ሢቲይ ከስቶክ ሢቲይ በ 1-1 ውጤት መወሰኑ ነበር። በውቅቱ ማንቼስትር ሢቲይና ማንቼስተር ዩናይትድ እኩል ሰባ ነጥብ ሲኖራቸው ሢቲይ የሚመራው እርግጥ በጎል ብልጫ ብቻ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በዛሬው ምሽት በጎደለው ግጥሚያ ፉልሃምን ካሸነፈ እንዲያውም በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ሊመራ ይችላል።

እንደ ስፓኙ ሊጋ ሁሉ እዚህም ሻምፒዮናው በሁለት ክለቦች መካከል የሚለይለት ሲሆን አርሰናል፣ ቶተንሃም ሆትስፐርና ቼልሢይ ደግሞ በመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ለተሳትፎ ለመብቃት ፉክክራቸውን አጠንክረዋል። አርሰናል ኤስተን ቪላን 3-0 በማሸነፍ ሶሥተኝነቱን ሲያረጋግጥ ተከታዮቹ ቼልሢይና ሆትስፐር እርስበርሳቸው ተጋጥመው 0-0 በመለያየት ጠቃሚ ነጥቦችን አጥተዋል። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ምናልባትም ያልተጠበቀው አስደናቂ ውጤት ሊቨርፑል በገዛ ሜዳው በዊጋን አትሌቲክ 2-1 መረታቱ ነበር።

ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ትናንት ከኋላ ተነስቶ ኮሎኝን 6-1 በማሸነፍ በአምሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ሁለቱ ክለቦች በ1-1 ውጤት እረፍት ሲወጡ የዶርትሙንድ የጎል ናዳ የተከተለው በሁለተኛው አጋማሽ ውስጥ ነበር። የክለቡ ተጫዋች ስቬን ቤንደር እንዳለው ለዶርትሙንድ የትናንቱ ድል በሻምፒዮንነት አቅጣጫ በሚያደርገው ዕርምጃ እጅግ ጠቃሚ ነው።

«ዛሬ ሶሥት ነጥቦችን ለመውሰድ መቻላችን ለኛ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን እናውቅ ነበር። እናም ያቀድነውን ገቢር ባለማድረጋችን በመጀመሪያው አጋማሽ ይሄው ነው የሆነው። ግን በሁለተኛው አጋማሽ ያሰብነውን ስናደርግ እንደ አሸናፊ ከሜዳ መውጣታችን ተገቢ ነው። ለሶሥቷ ነጥብና በሣምንት ውስጥ ለሶሥት ድሎች በመብቃታችን በጣም ነው የምንደሰተው»

ዶርትሙንድ በደመቀ ጨዋታ ወደፊት ሲገሰግስ ወደ 14ኛው ቦታ ላቆለቆለው ተጋጣሚው ለኮሎኝ በአንጻሩ ሽንፈቱ በጣሙን አደገኛ ነው። በወቅቱ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ከሚያወርደው ቦታ የምትለየው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። ያለፉትን ሣምንታት በጎል ፌስታ ያሳለፈው ሁለተኛው ባየርን ሙንሺን ደግሞ ሃኖቨርን 2-1 ሲያሸንፍ ለሻምፒዮንነት ጭብጥ ዕድል ኖሮት ይቀጥላል። የሰንበቱ ድልም በዚህ ረገድ በጣሙን ጠቃሚ እንደነበር ነው አጥቂው ማሪዮ ጎሜስ የተናገረው።

«እጅግ ጠቃሚ ድል ነበር። ሲበዛ ጠቃሚ ድል!ወደ መጨረሻ ከበድ ያለን እንደሚታሰበው ባለፈው ረቡዕ የፌደሬሺን ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ረጅም ጨዋታ የተነሣ ሣይሆን ሃኖቨር በአራትና አምሥት አጥቂዎች ግፊት በማድረጉ ነበር። እርግጥ ውጤቱን 3-1 ለማድረግ በቻልን ነበር። ግን አልተሳካልንም። ቢሆንም በመጨረሻ በአግባብ ነው ያሸነፍነው»

በነገራችን ላይ በፊታችን ግንቦት በርሊን ላይ ለሚካሄደው የጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የደረሱትም ሁለቱ ቀደምት ክለቦች ባየርንና ዶርትሙንድ ናቸው። ወደ ቡንደስሊጋው ውድድር እንመለስና ሌቨርኩዝንን 2-0 ያሸነፈው ሻልከ የቅርብ ተፎካካሪውን የግላድባህን መሸነፍ በመጠቀም ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። አሁን ከባየርን ሙንሺን የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ናቸው።

በሌላ በኩል ብሬመን በሜዳው ከአውግስቡርግ 1-1 በመለያየት ከስድሥት ወደ አምሥተኛው ቦታ ለመመለስ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ሲቀር በአንጻሩ በዚሁ በብሬመንና በሌቨርኩዝን መጎተት በተለይም ሽቱትጋርትና ቮልፍስቡርግ ለአውሮፓ ሊጋ ውድድር ተሳትፎ ወደሚያበቃው አምሥተኛና ስድሥተኛ ቦታ መቃረቡ እየተሳካላቸው ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤሲ ሚላን ካኋላ ተነስቶ ሮማን 2-1 በመርታት ሻምፒዮንነቱን መልሶ ለማረጋገጥ በሚያስችለው በአመራሩ ቀጥሏል። ሁለተኛው ጁቬንቱስም በበኩሉ ግጥሚያ ትናንት ኢንትር ሚላንን 2-0 ሲያሸንፍ ኤሲ ሚላን የሚመራው በአራት ነጥቦች ልዩነት ነው። ሌላው የሮማ ክለብ ላሢዮ ደግሞ ካልጋሪን 1-0 በመርታት ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ በሚያበቃወ በሶሥተኛው ቦታ ላይ ተቆናጧል። ናፖሊና ኡዲኔዘም የላሢዮ የቅርብ ተፎካካሪዎች ናቸው።

በፈረንሣይ ሻምፒየና ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከቦርዶ 1-1 ሲለያይ ሣንት ኤቲየንን 1-0 ያሸነፈው ሞንትፔሊዬር ደግሞ በጎል ብልጫም ቢሆን መልሶ አመራሩን ሊይዝ ችሏል። ያለፈው ሻምፒዮን ሊል ሰባት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን ቱሉዝ አራተኛ ነው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አልክማር ቫልቪክን 1-0 በመርታት በአመራሩ ቀጥሏል።

አያክስ አምስተርዳም ደግሞ አይንድሆፈንን 2-0 ሲያሸንፍ አንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ቀደምቱ ፖርቶና ቤንፊካ በየፊናቸው ባካሄዱት ግጥሚያ በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰናቸው ብራጋ በዛሬው ምሽት አካዴሚካን ካሸነፈ አመራሩን የመያዝ ዕድል ይጠብቀዋል። እንግዲህ በአውሮፓ የቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር ከሞላ ጎደል ይህን የመሰለ ነበር።

በእግር ኳሱ መድረክ የያዝነው ሣምንት አጋማሽም የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ዙር ውድድር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። በነገው ምሽት እስክዚህ መድረሱ ያልተጠበቀው የቆጵሮስ ክለብ አፓል ኒኮዚያ ከሬያል ማድሪድ የሚጋጠም ሲሆን በምሽቱ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ቤንፊካ ሊዝበንና ቼልሢይ ይገናኛሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን በማግሥቱም ማራኪ ግጥሚያዎች ይጠብቋቸዋል።

በዚሁ ምሽት የፈረናሣዩ ኦላምፒክ ማርሤይ ከጀርመኑ ባየርን ሙንሺን የሚገጠም ሲሆን ከሁሉም በላይ በተለየ ጉጉት የሚጠበቀው የኤሲ ሚላንና ያለፈው ዋንጫ ባለቤት የባርሤሎና ግጥሚያ ነው። የዚሁ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ በፊታችን ሚያዚያ የሚጠናቀቅ ሲሆን ፍጻሜው ግጥሚያ ግንቦት 11 ቀን ሚዩኒክ ውስጥ ይካሄዳል።

ምስል dapd

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

በማሌይዚያ-ሴፓንግ ትናንት በተካሄደው በሁለተኛው የዘንድሮው ውድድር ወቅት የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የስፓኙ የፌራሪ ዘዋሪ ፌርናንዶ አሎንሶ አሸናፊ ሆኗል። የሜክሢኮው የፌራሪ ተወዳዳሪ ሴርጆ ፔሬስም ሳይጠበቅ ሁለተኛ በመሆን ብዙዎችን ሲያስደንቅ እሽቅድድሙን ከመጀመሪያው ተርታ የጀመረው የብሪታኒያው ተወዳዳሪ ሉዊስ ሃሚልተን በሶሥተኝነት ተወስኗል።

ለጀርመናዊው የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለዜባስቲያን ፌትል እንደ መጀመሪያው ሁሉ የትናንቱም እሽቅድድም የቀና አልነበረም። ወጣቱ የሬድ-ቡል ዘዋሪ በትናንቱ እሽቅድድም በ 11ኝነት ተወስኖ ቀርቷል። በአጠቃላይ ነጥብ ፌርናንዶ አሎንሶ በ 35 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን የብሪታኒያ ተወላጆቹ ሉዊስ ሃሚልተንና ጄንሰን ባተን ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነው ይክተላሉ። አራተኛው የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ነው።

ምስል AP

አትሌቲክስ

ደቡብ አፍሪቃይቱ የቀድሞ የ 800 ሜትር ሩጫ የዓለም ሻምፒዮን ካስተር ሴሜኒያ በመጪው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ መሳተፍ መቻሏ አጠያያቂ ሆኗል። ለዚህም ምክንያቱ አትሌቷ ባለፈው ቅዳሜ ባደረገችው ሙከራ ለኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃ ጊዜ ለማስመዝገብ ሳትችል መቅረቷ ነው። ሴሜኒያ የኦሎምፒክ ዕድሏን ለመጠበቅ ከፈለገች ትልቅ መሻሻል ማድረግ ይኖርባታል።

የኦሎምፒኩ ተሳትፎ መስፈርት 1 ደቂቃ ከ 59 ሴኮንድ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰችው አትሌት የፈጀችው ጊዜ ከሁለት ደቂቃ በላይ ነበር። የ 21 ዓመቷ ሴሚኒያ በ 2009 በርሊን ላይ የዓለም ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ የጾታዋ አጠያያቂነት ብዙ ማነጋገሩ አይዘነጋም። ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺንም በአትሌቷ ላይ የጾታ መለያ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዙ የሚታወስ ነው።

ምስል dapd

ቴኒስ

በአሜሪካው የማያሚ የቴኒስ ዓለምአቀፍ ውድድር በሴቶችም ሆነ በወንዶች ጠንካሮቹ ተጫዋቾች ሶሥተኛውን ዙር በስኬት ማጠቃለሉ ተሳክቶላቸዋል። በወንዶች የዓለም ሁለተኛው ራፋኤል ናዳል የቼክ ተጋጣሚውን ራዳክ ስቴፓኔክን በለየለት ሁኔታ 6-2,6-2 ሲያሸንፍ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አራተኛው የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ደግሞ ያላንዳች ድካም ነው ወደ ተከታዩ ዙር ያለፈው። መሪይ ሰንበቱን በእረፍት ያሳለፈው የካናዳ ተጋጣሚው ሚሎሽ ራኦኒች በአካል ጉዳት ሊጫወት ባለመቻሉ ነበር።

ከነዚሁ በተጨማሪ ሁለቱ የፈረንሣይ ተወላጆች ዢል ሲሞንና ጆ-ዊልፍሪድ-ትሶንጋም ወደ አረተኛው ዙር ሲሻገሩ ጀርመናዊው ፍሎሪያን ማየርም ባለፉት ጊዜያት አይሎ የታየውን የአሜሪካ ተጋጣሚውን ጆን ኢስነርን በማሸነፍ ታዛቢዎችን አስደንቋል። በሴቶችም የዓለም አንደኛዋ የቤላሩስ ቪክቶሪያ አዛሬንካ እንግሊዛዊቱን ሄዘር ዋትሰንን በቀላሉ 6-0,6-2 ስታሸንፍ በተቀረ አና ኢቫኖቫ፣ ቬኑስ ዊሊያምስ፣ ማሪያ ኪሪሌንኮና ማሪዮን ባርቶሊም ወደ አረተኛው ዙር ማለፉ ተሳክቶላቸዋል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW