1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዓለም በዚህ (በ2022) ዓመት-ክፍል I

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2015

በፖለቲካ ቀዉስ ግራ-ቀኝ የሚላጉት ሱዳኖች፣ ኢትዮጵያዉያን ምናልባትም የሌሎች ብዙ ሐገራት ዜጎች የሐብታም፣ኃያል፣ተቀናቃኞቹ የምጣኔ-ሐብት፣የፀረ-ኑክሌር አንድ አቋም ካንጀት-ይሁን ካንገት ለማስተንተን ጊዜ አልነበራቸዉም።የሱዳኖች ፈጠነ።ጥር 2።የሐገሪቱ ጊዚያዊ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ስልጣን ለቀቁ።

Bilder des Jahres 2022 | Ukraine Russland Krieg
ምስል፦ GLEB GARANICH/REUTERS

ዓለም በ2022 የመጀመሪያዉ መንፈቅ ዓመት ቅኝት

This browser does not support the audio element.

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሰከነበት፣ምዕራብ ኢትዮጵያ ለዘር-እኩይ ዛር በሚፈሰዉ ደም የጨቀየበት፣የአፍሪቃ ቀንድ በረሐብ፣ምዕራብ አፍሪቃ በመፈንቅለ መንግስት የተንገረገቡበት፣መካከለኛዉ ምስራቅ ዶላር እየተዛቀ፣አስከሬን እየተለቀመ ጎል የተቆጠረበት፣ዩክሬን የጋየችበት፣ ኃያሉ ዓለም አርቆ አሳቢ ፖለቲከኛ፣ብልሕ ዲፕሎማት ተጠምቶ ጦረኞች ያናፈሩበት ዘመን በሌላ ሊተካ አምስት ቀን ቀረዉ። የግሪጎሪያኑ 2022 ዓለም በምግብ እጥረት፣ በዋጋ ንረት፣የተከነበት፣የዝናብ እጦትን ከጎርፍ ሙቀትን ከበረዶ በቀየጠ ተቃራኒ መቅሰፍት ሺዎች ያለቁ፣ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ዓመትም ነዉ። በመጀመሪያዉ መፈንቅ ዓመት የተከናወኑ አበይት ሁነቶችን ባጫሩ እንቃኛለን።                                          
ጥር 1፣ 2022 የኤሺያ-ኦሺኒያ 10 ተጎራባች ሐገራትን የሚያስተናብረዉ ትልቁ የዓለም ነፃ የንግድ ቀጠና ዉል ገቢር ሆነ።ማሕበሩ ጃፓን፣አዉስትሬሊያንና ኒዉዚላንድን የመሳሰሉ የዩናይትድ ስቴትስ ጭፍራዎችን ከኮሚንስታዊያኑ ቻይና፣ ቬትናምንና ካምቦዲያ ጋር ባንድ ማሰለፉ ፖለቲካዉ ያጦዘዉን ጠብ-ፍጥጫ ቁርቁስን ምጣኔ ሐብቱ በያኔዉ አዲስ ዓመት እያረገበዉ አስኝቶ ነበር።
የቻይና-ጃፓኖች ባንድ ማበር ማበር አስገምግሞ ሳያበቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ ቻይና፣ፈረንሳይ፣ሩሲያ፣ታላቅዋ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ አንድ መስለዉ፣ «የኑክሌር ጦርነት አሸናፊም-ተሸናፊም ስለማይኖረዉ መዋጋት የለብንም» የሚል መግለጫ አወጡ።ጥር አራት
በፖለቲካ ቀዉስ ግራ-ቀኝ የሚላጉት ሱዳኖች፣ ኢትዮጵያዉያን ምናልባትም የሌሎች ብዙ ሐገራት ዜጎች የሐብታም፣ኃያል፣ተቀናቃኞቹ የምጣኔ-ሐብት፣የፀረ-ኑክሌር አንድ አቋም ካንጀት-ይሁን ካንገት  ለማስተንተን ጊዜ አልነበራቸዉም።የሱዳኖች ፈጠነ።ጥር 2።የሐገሪቱ ጊዚያዊ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ስልጣን ለቀቁ።
                                        
«በገለፅኩት ምክንያት ሐላፊነቴን ለማስረከብ ወስኛለሁ።የተከበረችና ዉድ ሐገራችንንና የተከበረዉን ሕዝባችንን ለመምራትና ወደ ሲቢላዊ አስተዳደር  ለማሸጋገር የቀረዉን ሒደት ከግብ ለማድረስ ለሚሻ ወይም ለምትሻ ዕድል ለመስጠት የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣኔን ለመልቀቅ ወስኛለሁ።ሐገሪቱ ወደ ከፋ ጥፋት እንዳታዘቅጥ የምችለዉን ሁሉ ሞክሬያለሁ።ሱዳን ግን አሁን አጠቃላይ ሕልዉናዋን የሚያሰጋ አደገኛ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።»
የሱዳን ሕዝብም «ማዓሰላማ ሐምዶክ» እያለ በ2018 ማብቂያ በዳቦና ፉል መወደድ ሰበብ የጀመረዉን የአደባባይ ተቃዉሞ ሰልፍ፣የጦር ኃይል-የሲቢል ፖለቲከኞች አደገኛ ፍጥጫም ቀጠለ።

የዩናይትድ ስቴትስ ፓትርየት ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ምስል፦ Sebastian Apel/U.S. Department of Defense/AP/picture alliance
ከዓመቱ ምርች ፎቶዎች አንዱ-ዩክሬንምስል፦ EPA-EFE/TELEGRAM/V ZELENSKIY OFFICIAL HA

ለአፍሪቃዊቱ ትልቅ ደሴት ማዳጋስካር የፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ዉዝግብ ግጭቱ ረገብ ሲልላት ከከበባት ዉኃ «እየተጋተች» መቶዎችን የገበረችበት ዓመት ነበር።ጥር 15።11 ዜጎችዋን ጎርፍ በላቸዉ።በማግስቱ ራስዋን ማዳጋስካርን፣ ማላዊንና ሞዛምቢክን የመታዉ  አዉሎ ነፋስ 115 ሰዉ ገደለ።የካቲት 5 እንደገና ማዳጋስካርን ና ሞሪሽየስን የመታዉ ወዠቦ 123 ሰዉ ገደለ።
ጥር 16።ከ2020 ጀምሮ ማሊ፣ ጊኒ፣ ቻድ፣ ሱዳን ላይ የተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት ቡርኪና ፋሶ ላይ የተደገመ።ፕሬዝደንት ሮች ኮቤን ያስወገደዉን ወታደራዊ ሁንታ የመሩት ኮሎኔል ፓዉል-ሔንሪ ሳንዳጎ የመሪነቱን ስልጣን ያዙ።ከዘጠኝ ወር በኋላ ግን ኮሎኔሌም በሌላ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተወገዱ።
ዋጋዱጎ ለመጀመሪያዉ መፈንቅለ መንግስት እንደጨፈረች ሁሉ በሁለተኛዉም ቦረቀች።
የሁለተኛዉ መፈንቅለ መንግስት መሪ ሻምበል ኢብራሒም ትራኦሬ።ትራኦሬ እንደ ብዙዎቹ ወታደራዊ ሁንታ ሁመሪዎች ሁሉ ትራኦሬም ስልጣን ለማስረከብ ቃል ገቡ።
«በዓመቱ መጨረሻ የሚሰየመዉ ብሔራዊ ጉባኤ አዲስ ጊዚያዊ መሪ ይሰይማል።ከምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ ጋር በተደረገዉ ስምምነት መሰረት በ2014 ስልጣኑን የሲቢል አስተዳደር ይይዛል።»
በእልቂት-ዉድመት እስራኤል-ፍልስጤም፣ኢራቅን በልጣ የነበረችዉ ሶሪያ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ኃላ ላይ በዩክሬን መበለጧ እርግጥ ነዉ።ግን እንደ አምና ሐቻምናዉ ሁሉ ደም እንደፈሰሰባት ዘንድሮም አምና ሊሆን ነዉ።
የጎላዉ የየካቲት 3ቱ ግድያ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የእስላማዊ መንግስት ቡድን መሪ አቡ ኢብራሒም አል ሐሺሚ አል ቁሬሺን ሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ዉስጥ መግደሉን አስታወቀ።
የአሜሪካ ጦር ሶሪያ ዉስጥ አልቁሬሺን በገደለ በስድስተኛ ወሩ ከ2011 ጀምሮ አል-ቃኢዳን የሚመሩትን ግብፃዊዉን ዶክተር  አይማን አል ዙዋኺሪን ካቡል-አፍቃኒስታን ዉስጥ ገደለ።ኃምሌ 31 ነበር።
የካቲት 4።ቻይናና ሩሲያ የሰሜን አትላንቲካ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትን በተለይም AUKUS በመባል የምታወቀዉን የምዕራባዉያንን የፀጥታ ትብብርን አወገዙ።AUKUS-አዉስትሬሊያ፣ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ የተፈራረሙት ወታደራዊ ዉል ነዉ።
በዉሉ መሰረት ዩናይትድ ስቴትስ  በኑክሌር ኃይል የሚቀዝፍ ባሕር ሰርጓጅ የጦር ጀልባ ለአዉስትሬሊያ ታስታጥቃለች።ለአዉትሬሊያ ጀልባ ለመሸጥ ተዋዉላ የነበረችዉ ፈረንሳይም ስምምነቱን ተቃዉማለች።
የፓሪሶች ተቃዉሞ ከገበያ ማጣት ከመነጨ ኩርፊያ የዘለለ አልይደለም።የቤጂግ-ሞስኮዎች ቁጣ ግን ዓመቱ መጀመሪያ ላይ መስሎ የነበረዉ የምስራቅ-ምዕራብ ኃያላን መቀራረብን ያደፈረሰ፣የወደፊቱን መናጨት የጠቆመ ነበር።
የጊዜ ዑደት ግን ቀጠለ።የካቲት 24።ሩሲያ የዩክሬኖቹ የሉሐንስክ እና ዶኔትስክ ግዛቶች ራሳቸዉን የቻሉ ሕዝባዊ ሪፐብሊኮች ለመሆናቸዉ ዕዉቅና ሰጠች።ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸዉ «ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ» ያሉትን ወረራ በዩክሬን ላይ እንዲከፍት አዘዙ።
«ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲከፈት ወስኛለሁ።»
ከኪቭ እስከ ኻሪኮቭ፣ ከሊቪብ፣ እስከ ኦዴሳ የሚገኙ የዩክሬን ዉብ፣ምርጥ፣ዘመናይ ከተሞች፣ድልድይ፣ መንገድ፣ የእርሻ ማሳ፣ ፋብሪካዎች ይጋዩ ያዙ። የፖለቲካዉ ሴራ የሞስኮ፣ዋሽግተን፣ብራስልስ፣ ለንደኖች የዘመናት ሽኩቻ በቅጡ የማይገባዉ ሰላማዊ ሕዝብ ይረግፍ፣ የተረፈዉ እግሩ ወዳመራዉ ይግተለተል ገባ።
ቧልት፣ሽሙጥ፣ ቀልድ ትወና ማዝናናትን እንጂ ሥር የሰደደዉ የኃያላን የፖለቲካ ጥልፍልፍ፣ሐገርና ሕዝብን የማዳን ርዕይ፣ዲፕሎማሲ ጥበብ ብዙም የማይገባቸዉ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮልድሜር ዜሌንስኪ የኃያል ጎረቤታቸዉን በትርን በዘዴ ከማለፍ ብልሐት ይልቅ  ወረራዉን «ራስን የማጥፋት» ጥቃት በማለት አጣጣሉት። 
 «ሩሲያ ቁሻሻና አጥፍታ-የመጥፋት ጥቃትዋን  በሐገራችን ላይ ከፍታለች።»
ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የምስራቅ-ምዕራቦችን የኃይል ሚዛን አማክሎ ለሰባ ዓመት ያሕል የዘለቀዉ ሰላም ፈረሰ።አዉሮጳ እንደገና የዋሽግተን-ለንደን-ሞስኮዎች መቧቆሺያ መድረክ ሆነች።
ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብረዉ ዓለም በሩሲያ ላይ ዉግዘት፣ፉከራ፣ዛቻ፣ቅጣቱን ያወርዱት ያዙ።ፕሬዝደንት ጆ ባይደን።
«የሩሲያ ጦር በዩክሬን ሕዝብ ላይ የጭካኔ ጥቃት ጀምሯል። ማንም ሳይተነኩሰዉ፣ ያለምንም ምክንያት፣ ምንም ሳያስፈልግ አስቀድሞ የተዘጋጀ ጥቃት ነዉ።ፑቲን ወራሪ ነዉ።ይሕን ጦርነት የመረጠዉ ፑቲን ነዉ።እሱና ሐገሩ አፀፋዉን ይሸከሟታል።» 
የዋሽግተን ለንደን፣ ብራስልስ ተሻራኪዎች፣ የቶሮንቶ፣ ካምቤራ፣ የሶል፣ቶኪዮ ተከታዮቻቸዉ ጭምር ከሩሲያ ጋር ያደረጓቸዉን ስምምነቶች አፈረሱ።
የሩሲያ ባንኮች፣ኩባንዮች፣ አየር መንገዶች፣የቴሌቪዥንና የራዲዮ ስርጭቶች፣ዘፋኞች፣ ተዋኞች፣ አትሌቶች የእግርኳስ ቡድናት ሌሎችም ምዕራባዉያንና ተከታዮቻቸዉ ሐገራት ዉስጥ «ድርሽ እንዳይሉ» ታገዱ።የሩሲያ ቱጃሮች ገንዘብ ተያዘ።
በአፍሪቃ፣በመካከለኛዉ ምስራቅና በእስያ ስደተኞች ላይ ድንበራቸዉ ዘግተዉ ስደተኞቹ በብርድ ቆፈን ሲያልቁ ከድንበር ማዶ ይመለከቱ የነበሩት የዎርሶ ገዢዎች ግዛታቸዉን ለዩክሬን ስደተኖች ማረፊያና መተላለፊያነት ከፈቱ።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮችና ዘመናይ ጦር መሳራ ሩሲያን በሚያዋስኑ ሐገራት ሰፈረ።የአሜሪካ፣የብሪታንያ፣የፈረንሳይ፣የጀርመን ምርጥ ጦር መሳሪያ፣ሌላዉ ቀርቶ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አሮጌ ታንክና ሽጉጥ ሳይቀር  ወደ ዩክሬን ይጋዝ ያዘ። 
ይሔኔ ነዉ ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸዉ የኑክሌር  ቦምቡን ሳይቀር ለዉጊያ እንዲያዘጋጅ ያዘዙት።
«የሥራ ባልደረቦቼና እኔ-----ያዉ እንደምታዩት ምዕራባዉያን ሐገራት ወዳጅነትን የሚያፈርስ እርምጃ ብቻ ሳይሆን፣ በምጣኔ ሐብቱም በሌላዉም  መስክ ሕገ ወጥ ርምጃና ማዕቀብ እየጣሉ ነዉ።ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸዉ ስለሚያደርጉት ነገር ሁሉም ያዉቀዋል።የኔቶ ከፍተኛ መሪዎች ጭምር የጠብ ጫሪነት መግለጫ እየሰጡ ነዉ።ስለዚሕ የመከላከያ ሚንስቴርና የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች አዛዥ የሩሲያን ልዩ (የኑክሌር) የመከላከያ መሳሪያና ጦርን ለዉጊያ በከፍተኛ ተጠንቀቅ እንዲያቆሙ ሐገራችን ታዛለች።»
መጋቢት 7።ኔቶ ቡልጋሪያ፣ሩሜንያና ስሎቫኪያ ዉስጥ 40 ሺሕ ተጨማሪ ወታደሮችን ማስፈሩን አስታወቀ።
የዩክሬንና የሩሲያን ስንዴ፣ ጥራጥሬ፣የቅባት እሕሎችን የሚቀለበዉ፣ በሩሲያና ዩክሬን ማዳበሪያ ወይም የማዳበሪያ ንጥረ ነገሮች የሚያመርተዉ  አብዛኛዉ ዓለም፤የሩሲያን ጋዝና ነዳጅ ዘይት የሚጠጣዉ አዉሮጳም በፉርኖ ዱቄት፣በዘይት፣ በጥራጥሬ፣በጋዝና ነዳጅ ዘይት እጥረት ተራበ፣ተጠማም።
የተባበሩት መንግስታት ባለፈዉ ሚያዚያ እንዳስታወቀዉ ድርጅቱ የምግብ ሸቀጦችን ዋጋ ማነፃፀር ከጀመረበት ከ1990 ወዲሕ የምግብ ሸቀጥ ዋጋ የዘንድሮን ያክል አሻቅቦ አያዉቅም።
አመቱ አጋማሽ ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በቱርክ ሸምጋይነት ሩሲያ የወደብ መተላለፊያዎችን በመፍቀዷ የእሕል እጥረቱና የዋጋዉ ንረት ቢቀንስም፣  ዩክሬንን ከመዉድመት፣መሰነጣጠቅ ያዳናት፣አዉሮጳን በቅዝቃዜ ከመንዘፍዘፍ ያተረፋቸዉ የለም።
መጋቢት 7፣ አምናና ሐቻምና ዓለምን የገለበዉ የኮሮና ተሕዋሲ የገደለዉ ሰዉ ቁጥር ከ6 ሚሊዮን መብለጡ ተረጋገጠ።
መጋቢት 29።ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የምሥራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብ አባል ሆነች።ሰፊይቱ፣በማዕድን፣በዱር ሐብትና እንስሳ የበለፀገችዉ አፍሪቃዊት ሐገር የማሕበረሱ አባል መሆንዋ ከ100 በላይ አማፂ ቡድናት ጋር ለሚዋጋዉ ለኪንሻሳ መንግስት ሲበዛ ጠቃሚ ነበር።
ኮንጎ አባል በመሆንዋ የኬንያ፣የደቡብ ሱዳን፣ የቡሪንዲና የዩጋንዳ ወታደሮች በተለይ በሩዋንዳ የሚደገፈዉን M23 የተባለዉን አማፂ ቡድን ለመዉጋት ወደ ኮንጎ ዘምተዋል።
ሚያዚያ 13 የፓኪስታን ምክር ቤት ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካሕንን ሽሮ ተቃዋሚያቸዉን ሼሐበዝ ሸሪፍን ሾመ።የቀድሞዉ የኪሪኬት ጀግና ከስልጣን የተወገዱበትን ምክንያት የየምዕራባዉያንን በጣሙን የዩናይትድ ስቴትስን መርሕን አጥብቀዉ የመዉቀስ መተቸታቸዉ መዘዝ ያደርጉታል።
ግንቦት 9።የኑሮ ዉድነት ያስመረረዉ የሺራላንካ ሕዝብ በተከታታይ ያደረገዉ ያደባባይ ተቃዉሞ ሰልፍ የጠቅላይ ሚንስትር ማሒንዳ ራጃፓካሳን መንግስት አፈረሰ።ራኒ ቪከሬሜሲንጌሕ ተተኩ።ተቃዉሞዉ ግን አልበረደም።
ኃምሌ 19።ፕሬዝደንት ጎታባያ ራጃፓካሳን በተቃዋሚዎቹ ግፊት ሐገር ጥለዉ ኮበለሉ።ኃምሌ 21 ሁለቱ ወንድማማቾች በሕዝብ ግፊት ከስልጣን የተወገዱላቸዉ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ  ራኒ ቪከሬሜሲንጌሕ የፕሬዝደንትነቱን ስልጣን ተቆጣጠሩ።
ግንቦት 15።የሶማሊያዉ ፖለቲከኛ ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዝደትነት ተመረጡ።የ66 ዓመቱ ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ በሐገሪቱ ምክር ቤት የተመረጡት በ2012 በተደረገዉ ምርጫ ያሸነፏቸዉን ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆን) ጨምሮ 35 ተፎካካሪዎቻቸዉን በልጠዉ ነዉ።
«ብቀላ የለም» አሉ ሰዉዬዉ-ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ።«ምንም ዓይነት ቂም በቀል ቢኖር ለመፍታት ዝግጁ ነኝ።እንደምወዳደር ባስታወቁበት ወቅት እንዳልኩት ማንንም ኢላማ ያደረገ ብቀላና የፖለቲካ ክትትል የለም።ሐገሪቱ በቂ ሕግጋትና ደንቦች አሏት።ልዩነት ከተፈጠረ በነዚያ ሕግጋትና ደንቦች መፈታት አለበት።»
ከ1978 ጀምሮ ሐንስ በተባለችዉ ደሴት ይገባኛል ሰበብ «የዉስኪ ጦርነት» በሚል ቅፅል የሚታወቀዉን ዉዝግብ የገጠሙት ካናዳና ዴንማርክ ደሴቲቱን ለሁለት ሰንጥቀዉ ተካፈሉና ታረቁ።ሰኔ 14 ነበር።
«የዉስኪ ጦርነት።» ነገሩ እንዲሕ ነዉ። በ1984 የካናዳ ፌዘኛ ወታደሮች ሐንስ ደሴት ላይ የካናዳን ባንዲራ ተክለዉ፣ ባንዲራዉ አጠገብ ጠርሙስ ዊስኪ አስቀምጠዉ ሔዱ።የዴንማርኩ የግሪንላንድ ክፍለ-ግዛት ሚንስትር በካናዳ ባንዲራ ምትክ የዴንማርክን ሰቅለዉ፣ በዉስኪዉ ፋንታ የዴንማርክ አልኮሕልን አስቀምጠዉ «እንኳን ወደ ዴንማርክ መጣችሁ የሚል ፅሑፍ ትተዉ ተመለሱ።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያቺን ደሴት ቀድሞ የረገጠ የሁለቱ ሐገራት ወታደር ወይም ፖለቲከኛ የሌላዉን ባንዲራ እየነቀለ፣የራሱን እየተከለ፣ አልኮሆል እየለወጠ ኖረ።ዘንድሮ ሰኔ ግን የዉስኪዉ ጦርነት አበቃ። የግማሽ ዓመቱ ቅኝታችንም አበቃ።

ምስል፦ Kilaye Bationo/AP Photo/picture alliance
የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ሁንታ መሪ ሻምበል ኢብራሒም ትራኦሬምስል፦ Kilaye Bationo/AP Photo/picture alliance
ከሐገር የኮበለሉት የሲሪላንካ ፕሬዝደንት ጉታባያ ራጃፓካሳምስል፦ Eranga Jayawardena/AP/picture alliance
የቀድሞዉ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክምስል፦ Hannibal Hanschke/REUTERS
ሱዳን ተቃዉሞ ሰልፍምስል፦ AFP/Getty Images

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW