1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዓለም አቀፉ የብዙሃን መገናኛ መድረክ

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2012

ዶይቸ ቬለ ዲ ደብሊው በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የብዙሃን መገናኛ መድረክ በዚህ  ሳምንት ተጀምሯል። ውይይቱ በዲጂታል መገናኛ የተካሄደ ሲሆን የተሳሳቱ መረጃዎች የኮሮና ተዋህሲ ስርጭትን ማፋጠናቸው ተመልክቷል።ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ፌስቡክ ለ50 ሚሊዮን አሳሳች መልክቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል።

GMF20 Artikelbild Datum Thema: July 6-7, 2020 | Pluralism. Populism. Journalism.

ዓለምአቀፍ የብዙኃን መገናኛ ጉባዔ እና የኮሮና ስጋት

This browser does not support the audio element.

ለወትሮው ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጋዜኞች፣የብዙሃን የመገናኛ ባለቤቶችና አጋሮች ይሳተፉበት የነበረው  የዶቼ ቬለ ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የብዙሃን መገናኛ መድረክ  ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በዲጂታል መገናኛ ነበር  ጉባኤው የተጀመረው።በሳምንቱ አጋማሽ የተጀመረው ይህ ጉባኤ  በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የብዙኃን መገናኛ ኃላፊነት ምን መምሰል አለበት ? በሚል ርዕስ የተሰናዳ ሲሆን የዲጂታል የዜና ምንጮች ተአማኒነት የውይይቱ ዋና ማጠንጠኛ ነበር። የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ትክክለኛ መረጃ ወሳኝ ቢሆንም  አሉባልታ፣ ሀሰት እና የተምታቱ መረጃዎች ደንቃራ መሆናቸው በውይይቱ ተወስቷል።የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት አርጀንቲናዊቷ  ተባባሪ ፕሮፌሰር ማሪያ እሳፓሬንዛ ካሱሎ  የውይይቱ ተሳታፊ ናቸው።ለእሳቸው ተአማኒነትን በተመለከተ አካባቢያዊ ጋዜጠኝነት ጠቃሚ ነው።


«አስተማማኝ እና እምነት የሚጣልበትን መረጃ ከሀሰተኛው ለማጣራት ከባድ ነው። በእነዚህ ወራት ውስጥ የአከባቢ፣ የክልል ወይም የከተማ ጋዜጦች  ከብሔራዊ  መገናኛ ብዙሃን የበለጠ አስተማማኝ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ምክንያቱም  መሬት ላይ ዘጋቢ ስላላቸው የበለጠ ተጨባጭ አሃዞችና መረጃዎች አላቸው።»
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ኬንያዊው  ጆን አለን ናሙ በበኩላቸው ወረርሽኙ እንደነዚህ ላሉ የአከባቢ ጋዜጠኞች ተደራሽነትን አስቸጋሪ ሊያደርግባቸው  እንደሚችል ጠቁመዋል ፡፡
«ወደ ሰዎች በቀረብክ ቁጥር ለታሪኮችህ ቅርብ ትሆናለህ።በተለይ መረጃና የተፃፉ መዛግብት ማግኘት አስቸጋሪ በሆነባቸው የአፍሪካ የተለያዬ አካባቢዎች።የጤና ችግር መሬት ላይ ያሉ የመጀመሪያ ምንጮች ለአንዳንድ ጋዜጠኞች ተደራሽ ላይሆኑ ይችላሉ።»


በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሚና ሌላው የውይቱ ዋና ትኩረት ሲሆን የማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ጓደኛ ወይስ ጠላት? በሚል በተለይ ፌስቡክ ብዙ ክርክርና ውይይት ተደርጎበታል። ፌስቡክን ወክለው የተገኙት ጊዲ ቡሎው እንደሚሉት  ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ፌስቡክ የኮቪድ-19 መረጃ ማዕከል መክፈቱን ጠቅሰው አሳሳች መረጃዎችን ለመዋጋት እየሰራ ነው ብለዋል።  «የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመዋጋት እየሞከርን ነው።ከኮሮ ተዋህሲ ጋር የተያዙትን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የተዛቡ መረጃዎችን ።የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመዋጋትም በዓለም  ዙሪያ ከ 70 በላይ ከሆኑ የእውነታ አጣሪዎች  ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡» በዚህ የማጣራት ስራም ፌስቡክ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለ50 ሚሊዮን አሳሳች መልክቶች ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አብራርተዋል።


የተሕዋሲውን ስርጭት ለመግታት በአንድ ወገን የተሳሳቱ መረጃዎች በሌላ ወገን የግንዛቤ እጥረት ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሀላፊነት የሚሰማቸውና ተዋህሲውን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ሊመሰገኑ የሚባቸው ጋዜጠኞች መኖራቸውን ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።

 

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሠ

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW