1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአይኤምኤፍ ያጸደቀው የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የፖሊሲ አላባዎች የሚሳኩ ናቸው?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያጸደቀው የተራዘመ የብድር አቅርቦት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ያሉበትን ሥር የሰደዱ ችግሮች ለመቅረፍ የተወጠኑ አምስት የፖሊሲ አላባዎች አሉት። የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ በየአይነቱ ምግብ
የብር የመግዛት አቅም ሲዳከም በኢትዮጵያ ገበያ የምግብ ማብሰያ ዘይትን ጨምሮ በርካታ ከውጪ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። ምስል DW/E. Bekele

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያጸደቀው የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የፖሊሲ አላባዎች የሚሳኩ ናቸው?

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ80 ብር ገደማ ገዝቶ በ81 ብር ከ60 ገደማ ይሸጣል። የባንኩ የምንዛሪ ተመን ዛሬ ብቻ ሁለት ጊዜ ተቀይሯል። የዛሬው ተመን በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና በፍላጎት መከናወን ከመጀመሩ በፊት ከነበረው በ23 ገብር ገደማ ከፍ ያለ ነው። የግል ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተመን እየተከተሉ የዶላር መግዣ እና መሸጫቸውን ይፋ ሲያደርጉ ታይተዋል።

የብርን የመግዛት አቅም በኃይል ያዳከመው ውሳኔ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) መርሐ-ግብር ውስጥ የተካተተ ነው። መርሐ-ግብሩ ከጸደቀ በኋላ ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሰጠበትን ሥምምነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያጸደቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “ይኸ ፕሮግራም የእኛ ፕሮግራም ነው። የልማት አጋሮችን አግዙን ብለን የጠየቅናቸው እኛ ነን። የሚፈታው የእኛን የኤኮኖሚ ችግር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

መርሐ-ግብሩ “ሁሉም ዘርፎች በተቀናጀ መልኩ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተቀረጸ” እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አሕመድ “ረዥም ጊዜ ድርድር ሲካሔድበት የነበረ” እንደሆነ ለምክር ቤቱ አስታውሰዋል። “በሕብረተሰብ ላይ የሚያመጣውን ጫና” ለመቋቋም “በከፍተኛ ደረጃ ቅድመ ዝግጅት” መደረጉን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ “የዕዳ ሥጋታችን ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ይወርዳል” ሲሉ ፋይዳውን አስረድተዋል።

ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲሆን የሀገር ውስጥ ገቢ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ አሕመድ “የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ያለውን ረብሻ አሻሽለን፤ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ የወጪ ንግዳችንን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ኢትዮጵያ ከውጪ የምትሸምተው በተገቢው መልኩ እንዲገራ የሚያደርግ ይሆናል። ይኸ ደግሞ ለውጭ መዋዕለ-ንዋይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ባለሀብቱንም በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ይሆናል” ሲሉ አብራርተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “ይኸ ፕሮግራም የእኛ ፕሮግራም ነው። የልማት አጋሮችን አግዙን ብለን የጠየቅናቸው እኛ ነን። የሚፈታው የእኛ የኤኮኖሚ ችግር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ ሲያደርግ በመጀመሪያው ዕለት ብቻ ብር 30 በመቶ የመግዛት አቅሙን አጥቷል። የውጭ ምንዛሪ በገበያው ፍላጎት እና በአቅርቦት እንዲወሰን ማድረግ ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች ቢኖሩትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ ለቆዩ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ጭምር የሚዋጥ አልሆነም።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም እርምጃውን የዐቢይ መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ተግባራዊ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ከነበረው “ሕዝባዊ ቅቡልነት” እና “አንጻራዊ የማክሮ ኤኮኖሚ መረጋጋት” አኳያ የሚገርም እንዳልነበር ይናገራሉ። አቶ ጌታቸው እንደሚሉት “መቼ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር የሆነ ጊዜ ሊሆን እንደሚገባ ሁሉም ሰው ያምናል።”

ኢትዮጵያ በተረጋጋ የማክሮ ኤኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ በተለምዶ ጥቁር እየተባለ የሚጠራውን የጎንዮሽ ገበያ ከይፋዊው የምንዛሪ ተመን ለማመጣጠን በገበያ የሚመራ የገንዘብ ፖሊሲ ብትከተል “አልገረምም” ይላሉ። ነገር ግን ለውጡ የሚያስከትላቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም ምን ያክል ዝግጁ ነች? የሚለው ጥያቄ ይከተላል።

በውሳኔው መሠረት ከዚህ ቀደም ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ ባንክ ከግብይቱ እጁን አውጥቷል። ግብይቱ ከእንግዲህ በቀጥታ በባንኮች እና በደንበኞቻቸው አማካኝነት የሚከናወን ነው። ወደፊት “ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች” ፈቃድ ተሰጥቷቸው በግብይቱ እንዲሳተፉ ይደረጋል። ሀገሪቱ ትከተላቸው የነበሩ የውጭ ምንዛሪ ግብይት መመሪያዎች እና ደንቦችም ተሻሽለው በአንድ መመሪያ እንዲካተቱ መደረጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምኅረቱ ተናግረዋል። 

የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተሰኘውን መርሐ-ግብር ለማስፈጸም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጽድቋል። በአራት ዓመታት ከሚሰጠው የአይኤምኤፍ ብድር ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚለቀቅ ነው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አዲስ ፕሮግራም ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ የጀመረችውን ድርድር ወደ መቋጫው የሚያደርስ በመሆኑ ለመንግሥት አንድ እፎይታ የሚፈጥር ነው። ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች የልማት አጋሮች እና አበዳሪዎች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኝ መንገድ የሚጠርግ እንደሆነ መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም ገልጿል።

የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተሰኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ያሉበትን ሥር የሰደዱ ችግሮች ለመቅረፍ የተወጠኑ አምስት የፖሊሲ አላባዎች አሉት። የመጀመሪያው የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ነው።

የብር ምንዛሪ መዳከም ነጋዴዎች ከሀገር ውስጥ ገበያ ሸቀጦች በርካሽ ገዝተው በዓለም አቀፍ ገበያ ሲሸጡ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይረዳል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ግን የኢትዮጵያን ሸቀጥ በዓለም ገበያ የሚሸጡ ነጋዴዎች የሚገዙበት ዋጋ ዝቅ በማለቱ ብቻ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው ሸቀጦች አብዛኞቹ ተጨማሪ እሴት ያልታከለባቸው የግብርና ውጤቶች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አቶ ጌታቸው እንደሚሉት “ሌሎች ሀገራትም በብዛት የሚያመርቷቸው ናቸው።” የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ለማሳደግ መሠረተ-ልማት፣ የማጓጓዣውን ዘርፍ እና ቢሮክራሲውን ማሻሻል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ለገበሬው ማሰራጨት የመሰሉ መዋቅራዊ እና ዘላቂ መዋዕለ-ንዋይ የሚፈልጉ ሥራዎች መከናወን አለባቸው።

እነዚህ የኢትዮጵያ የቤት ሥራዎች “በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ አይደሉም” የሚሉት አቶ ጌታቸው “ኤክስፖርት ካልተሻሻለ ደግሞ ዝንፈቱ መስተካከል አይችልም” ሲሉ የዕቅዱን ፈተና ያብራራሉ።

መንግሥት የሚከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ በማዘመን የዋጋ ግሽበትን መግታት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ባጸደቀው መርሐ ግብር የተካተተ ሁለተኛው የፖሊሲ አላባ ነው። ይሁንና በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እና በምርት ሰንሰለቱ ውስጥ ካሉ ችግሮች ጋር ተደማምሮ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደረገው የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ዋና ተግዳሮት ነው።  

የብር ምንዛቲ ሲዳከም ላኪዎች ከገበያው ሸቀጦች የሚገዙበት ዋጋ ቀንሶ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ተብሎ ቢታመንም ዘርፉ ግን በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተቀፈደደ ነው። ምስል Everyonephoto/Pond5 Images/IMAGO

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የሚከተለው ሥልት “ወጪን በመቆጠብ ረገድ ራሱን አደብ ለማስገዛት ፈቃደኛ ነወይ?” እንዲሁም “ራሱን ፋይናንስ የሚያደርግበት መንገድ የዋጋ ውድነትን ላያባብስ በሚችል መልኩ ቁርጠኝነት አለወይ?” የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ግን ለአቶ ጌታቸው “ጥያቄ የሚነሳበት ነው።” የምጣኔ ሐብት ባለሙያው “የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በማዘመን ብቻ የምታመጣው ነገር አይደለም። ባለበጀት የመንግሥት ክፍሎች ውስጥ ዲሲፕሊን ይፈልጋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን በ2017 ከ10 በመቶ በታች ዝቅ የማድረግ ዕቅድ አለው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር ከሦስት ዓመታት አማካኝ ገቢ ከ15 በመቶ እንዳልበልጥ ይገድባል።

የመንግሥት ወጪዎች ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዳለው “ተገቢ ለሆኑ ኤኮኖሚውን ለማሳደግ ለሚጠቅሙ ነገሮች ብቻ” መዋል ይኖርባቸዋል። “በበጀት ፖሊሲ ውስጥ የማይስተዋሉ በመንግሥት በኩል የሚከናወኑ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎች” ግልጽ ተደርገው፣ ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኗቸው ተለክቶ ተግባራዊ ከሆኑ አቶ ጌታቸው “በተወሰነ መልኩ የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር ይቻል ይሆናል” የሚል ተስፋ አላቸው።

ያም ቢሆን ግን “ኤክስፖርት ከሚያደርገው አራት አምስት እጥፍ ኢምፖርት የሚያደርግን ኤኮኖሚ የውጪ ምንዛሪ ለውጥ በማድረግ የዋጋ ውድነት አያስተናግድም ማለት ግን ተላላነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።  

የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን በማጠናከር ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወጪዎች ማዋል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር ሦስተኛ አላባ ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ መንግሥት የሚሰበስበውን ቀረጥ ምጣኔ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አንድ በመቶ ለመጨመር መወሰኑን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ነባር ቀረጦችን አያሻሻለ አዳዲስ የግብር አይነቶች ሥራ ላይ ቢያውልም የዕቅዱ ስኬት ግን በሀገሪቱ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚመሠረት ነው። በተለይ የሀገሪቱ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ ግብር መሰብሰብ ለሚሻው መንግሥት ኹነኛ ፈተና ይሆናል።

የአከፋፈል ሽግሽግን ጨምሮ የኢትዮጵያን የዕዳ ዘላቂነት መመለስ እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር በመርሐ ግብሩ የተካተቱ ተጨማሪ ሁለት የፖሊሲ ዓላባዎች ናቸው። ብር ሲዳከም በገበያው የምግብ ማብሰያ ዘይትን የመሳሰሉ ሸቀጦች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዘርፍ የተሠማሩ የሪል ስቴት ኩባንያዎችም ዋጋ መከለስ መጀመራቸውን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች የአገልግሎቶቻቸውን ክፍያዎች የዶላር ምንዛሪ ተመን ለውጡን በመከተል እየጨመሩ ነው።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት “የገቢ እና ወጪ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል” ብለዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

አቶ ጌታቸው ከአርጀንቲና እስከ ናይጄሪያ፤ ከሲሪ ላንካ እስከ ኬንያ ቁጥጥር ከሚደረግበት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ወደ ገበያ መር የምንዛሪ ሥርዓት የተሻገሩ ሀገሮች የዋጋ ግሽበት እንደገጠማቸው ይናገራሉ። ይኸ አሁን በገበያው እየታየ እንዳለው በኢትዮጵያም መከሰቱ አይቀርም።

“የዋጋ ጭማሪ በተለያዩ ገቢ ሸቀጦች ላይ መስተዋሉ አይቀርም” የሚሉት አቶ ጌታቸው “አሁን ባለው የዋጋ ውድነት ላይ ተጨማሪ የዋጋ ውድነት ስለሚሆን ቋሚ ገቢ ላላቸው፣ በሀገር ውስጥ ገንዘብ ገቢያቸውን ለሚያገኙ፣ ዝቅተኛ ክፍያ ለሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ ፈተና መፍጠሩ አይቀርም” ሲሉ አስረድተዋል።

ከዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያስጸደቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ መንግሥታቸው ለ2017 ተጨማሪ በጀት እያዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።“በተለይ ለታችኛው ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኛ በየደረጃው የኑሮ ድጎማ በደመወዝ ጭማሪ መልክ የሚደረግ ይሆናል” ያሉት ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ነዳጅ፣ ዘይት፣ ማዳበሪያ፣ መድሐኒትን እንደሚደጉም ገልጸዋል።  

መንግሥት የብርን ተመን በማዳከም ያሳለፈው ውሳኔ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በተለይ የከተማ ነዋሪዎች በኃይል ሊጎዳ የሚችል ቢሆንም ራሱ መንግሥትን ከጫው አይተርፍም። መንግሥት ያለበት 28 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ዕዳ ካለፈው ሰኞ በኋላ በብር ሲመነዘር በከፍተኛ መጠን ያድጋል። የዕዳ ክፍያውም በብር ሲሰላ የዛኑ ያክል መጨመሩ አይቀርም።

ከመንግሥት ውል ገብተው አገልግሎት እና ዕቃ የሚያቀርቡ ተቋራጮች የሚጠይቁት የዋጋ ማስተካከያ፣ ራሱ መንግሥት ከገበያው የሚሸምታቸው ሸቀጦች፣ ዝቅተኛ ገቢ ላለው የሕብረተሰብ ክፍል ሊደረግ የታቃደው ድጎማ ተጽዕኖ የሚያስከትሉ ናቸው። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ “የሽግግር ወቅት ወጪዎችን እና የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያዎች የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ የሚረዳ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ” ከኢትዮጵያ አጋሮች መገኘቱን ገልጸዋል።

የልማት አጋሮች ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ድጋፍ ጫናውን ለማቃለል ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ቢሆንም በራሱ በቂ አይደለም። “ጫናው በአንድ ጊዜ የሚቆም አይደለም። በቀጣይነትም የሚኖር ነው። ድጋፉ ግን የጊዜ ገደብ አለው” የሚሉት አቶ ጌታቸው ጫናውን አስወግዶ እንዴት ወደ ተረጋጋ የኤኮኖሚ ማዕቀፍ መምራት ይቻላል? የሚለው ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW