ዓለም አቀፍ ቀውስ እንዳይቀሰቅስ ያሰጋው የአሜሪካ እና አውሮጳ ባንኮች ኪሳራ
ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015
ሦስት የአሜሪካ ባንኮች በተከታታይ በኪሳራ ሲዘጉ በጎርጎሮሳዊው 2008 የተቀሰቀሰው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ዳግም ሊመጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ አጭሯል። የምጣኔ ሐብት እና የፋይናንስ ባለሙያዎች የዘንድሮው የባንኮች ቀውስ እንደቀደመው እንዳልሆነ እየተነተኑ ለማስረዳት ቢሞክሩም ሥጋቱ አሁንም ገሸሽ አላላም። ለዘመን አመጣሹ የማይዳሰስ የዲጂታል ገንዘብ (የክሪፕቶ ከረንሲ) ዘርፍ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲልቨርጌት ባንክ፤ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አገልጋዩ ሲሊኮን ቫሊ ባንክ እና ሲግኔቸር ባንክ ግን በራቸው ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል።
የአሜሪካው ሲልኮን ቫሊ ባንክ የገጠመውን ቀውስ መቋቋም ተስኖት የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጣልቃ ከመግባቱ በፊት በአገሪቱ 16ኛ ግዙፍ ባንክ ነበር። ከአራት ዐሥርተ ዓመታት በፊት የተቋቋመው ባንክ ዋንኛ ትኩረት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሆነው ቆይተዋል። በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ጠባይ በባንክ ባለሙያዎች አስጊ የሚባሉት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም የባንኩ ዋንኛ ደንበኞች ነበሩ።
በተለይ የአሜሪካ መንግሥት ከዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ እንዳይደገም ተግባራዊ ያደረገው ጥብቅ መመሪያ ላይ የተደረገ ለውጥ ሲልኮን ቫሊ ባንክ ለገጠመው ቀውስ የራሱን ሚና ተጫውቷል። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የፈረሙት የደንበኞች ጥበቃ መመሪያ ከ250 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጥሪት ባላቸው ባንኮች ላይ ጥቅብ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚያዝ ነበር። መመሪያው ግን የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር መሻገር አልሆነለትም።
የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ያልጣሙት የትራምፕ መንግሥት ይኸኛውንም ሻረው። የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ከ250 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጥሪት ያላቸው እንደ ባንክ ኦፍ አሜሪካ እና ቼስ የመሳሰሉ ተቋማት ላይ የሚደረገውን ጠንካራ ቁጥጥር በነበረበት ሲያስቀጥል በአነስተኛ ባንኮች ላይ የሚደረገውን በአንጻሩ ቀልብሶታል።
ውሳኔው ከተላለፈ ከሁለት ዓመታት በኋላ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን ሲያምስ ሲልኮን ቫሊ ባንክ በደንበኞቹ ተቀማጭ ገንዘብ አበጠ። የደንበኞቹ ተቀማጭ 189 ቢሊዮን ዶላር የደረሰበት 2021 ሲሊኮን ቫሊ ባንክ በታሪኩ ከፍተኛ ትርፍ ያጋበሰበት እንደነበር ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል። ሲልኮን ቫሊ ባንክ በበኩሉ በደንበኞቹ ተቀማጭ ገንዘብ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ገዛ። ከቦንዶቹ ወለድ የሚገኘው ገቢ ደንበኞች እና ሲልኮን ቫሊ ባንክ እንደየ ድርሻቸው የሚከፋፈሉት ትርፍ ነው። ይሁንና በዚህ ወቅት ድንገት የአሜሪካ መንግሥት የወለድ ምጣኔን ከፍ አደረገ። ይኸ ባንኩ የገዛቸውን ቦንዶች ዋጋ የሚቀንስ ነበር።
የባንኩን የቁልቁለት ጉዞ ሲከታተል የቆየው የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛ ቤን አይሰን "የወለድ ምጣኔ ከፍ ሲል የቦንድ ዋጋ ይቀንሳል። ሲሊኮን ቫሊ ባንክን ጨምሮ ባንኮች በእጃቸው ከፍተኛ ቦንድ ቢኖርም ኪሳራ ገጠማቸው። ስለዚህ ድንገት ሲሊኮን ቫሊ ባንክ ለቦንዶቹ የከፈለው እና በወረቀት ላይ ያላቸው የዋጋ ተመን ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተሻገረ። ይኸ ሲሊኮን ቫሊ ባንክን ለውድቀት የዳረገው ኪሳራ ጅማሮ ነው" በማለት ተናግሯል።
ውድቀቱን ያፋጠነው በባንኩ እጅ የሚገኙ ሰነዶች ዋጋ ሲቀንስ ገንዘባቸውን የሚያስቀምጡ ደንበኞች ቁጥር አብሮ ማሽቆልቆሉ ጭምር ነው። ከባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ አብዛኛው ከ250 ሺሕ ዶላር በላይ ባላቸው 37,000 አካውንቶች የተያዘ መሆኑ ሌላው ራስ ምታት ነው። በአሜሪካ ሕግ እስከ 250 ሺሕ ዶላር የተቀመጠባቸው አካውንቶች ባንኩ አንዳች ችግር ቢገጥመው የፌዴራል ተቀማጭ ገንዘብ ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን የመድን ዋስትና የተሰጣቸው ናቸው። የመድን ዋስትናው ከዚያ በላይ ገንዘብ የተቀመጠባቸውን አካውንቶች አያካትትም።
ባንኩ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ያስከተሉ ሰነዶች በእጁ እንደሚገኙ የካቲት 29 ቀን፣ 2015 ለመንግሥት ሲያሳውቅ የውድቀት ሰዓታቱ መቁጠር ጀመሩ። ይህ ለአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች የቀረበ ሪፖርት በአገሪቱ የአክሲዮን ገበያ የባንኩ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል። ደንበኞቹ ከባንኩ የነበራቸውን ተቀማጭ ለማውጣት ተጣደፉ። አብዛኞቹ ባንኩ ከሌሎች መሰል ተቋማት በተለየ ለአገልግሎቱ የመረጣቸው ትርፋማም ያደረጉት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ነበሩ።
ደንበኞች እስከ 45 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተቀማጭ ገንዘባቸውን ለማውጣት ሲሞክሩ የባንኩ አክሲዮኖች ዋጋ በከከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ ነበር። በስተመጨረሻ የሲልኮን ቫሊ ባንክ ጥሬ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተሟጠጠ። ይኸን የቁልቁለት ጉዞ በአይነቁራኛ ሲከታተል የቆየው የአሜሪካ መንግሥት እና የካሊፎርኒያ ባለሥልጣናት መጋቢት 1 ቀን፣ 2015 የሲሊኮን ቫሊ ባንክን ተቆጣጠሩ።
የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት እና ቅርንጫፎች ተዘጉ። የባለሥልጣናቱ ርምጃ የፈጠረው ድንጋጤ ባንኩን ብቻ ሳይሆን ደንበኞችን ጭምር ለትርምስ የዳረገ ነበር። ደንበኞች በቀጥታ ከአካውንቶቻቸውም ሆነ ከባንኩ ተንቀሳቃሽ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ተቀማጫቸውን ማውጣት አልቻሉም።
ሲሊኮን ቫሊ ባንክ በተዘጋ በ48 ሰዓታት ውስጥ መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ሲግኔቸር ባንክ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጠመው። የሲግኔቸር ባንክ ውድቀት አንድም በሲልኮን ቫሊ ባንክ ኪሳራ የተቀሰቀሰ ነው። በኒው ዮርክ እና አካባቢው ትልቁ አበዳሪ እንደሆነ የሚነገርለት ሲግነቸር ባንክ ባለው በአሜሪካ መንግሥት የመድን ዋስትና የማይሰጠው ከፍተኛ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን እና በስራው እንደ ክሪፕቶ የቴክኖሊጂ ዘርፎች የሚሰጠው ብድር ደንበኞቹን ለሥጋት የዳረጉ ጉዳዮች ነበሩ። በሲሊኮን ቫሊ ባንክ ድንገተኛ ውድቀት የተደናገጡ የሲግኔቸር ባንክ ደንበኞች ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማውጣታቸውን አንድ የቦርድ አባል ለአሜሪካው ሲኤንቢሲ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ቅድሚያ በሁለቱ ባንኮች የአገሪቱ ሕግ በሚያዘው መሠረት ዋስትና የሰጠው እስከ 250 ሺሕ ዶላር ተቀማጭ ላላቸው ደንበኞች ብቻ ነበር። በቀናት ልዩነት ግን ዋስትና የሌላቸው እና ከተጠቀሰው መጠን በላይ በባንኮቹ ያስቀመጡ ደንበኞች ገንዘባቸውን ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል። የከሰሩት ባንኮች ደንበኞች ገንዘባቸውን ማግኘት የቻሉት በጎርጎሮሳዊው 2008 ተፈጥሮ የነበረው አይነት ቀውስ ለመቋቋም በራሳቸው በባንኮች ክፍያ ከተመሠረተ ዋስትና ነው።
ፕሬዝደንት ጆ ባደይደን "በእነዚህ ባንኮች ተቀማጭ ያላቸው ሁሉም ደንበኞች ከኪሳራ ይኸ በእነዚህ ባንኮች የሚገለገሉ በመላ አገሪቱ የሚገኙ እና ደመወዝ እና ወጪያቸውን መክፈል ፣ ሥራዎቻቸውንም መቀጠል የሚፈልጉ አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን ይጨምራል። ምንም አይነት ኪሳራ በግብር ከፋዮች ትከሻ ላይ አይወድቅም። ከዚያ ይልቅ ገንዘቡ ባንኮች ከሚከፍሉት የተቀማጭ የመድን ዋስትና ፈንድ የሚመጣ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የባንኮቹ ኃላፊዎች እንደሚባረሩ የገለጹት ፕሬዝደንቱ "የባንኮቹ ባለወረቶች ከኪሳራ አይጠበቁም። ባንኮቹ ሥጋት እንዳለባቸው እያወቁ አምነው ገብተውበታል። አውቀው የተቀበሉት ሥጋት ለኪሳራ ሲዳርግ ባለወረቶች ገንዘባቸውን ያጣሉ። ካፒታሊዝም የሚሰራው እንዲያ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የአሜሪካው ቀውስ አትላንቲክን ተሻግሮ ከናጠጠችው ስዊትዘርላንድ ሲደርስ ሰለባ ያደረገው የ167 ዓመት ባለጸጋ ባንክን ነው። ዋና መቀመጫውን በዙሪክ ከተማ ያደረገው ክሬዲት ስዊስ ባንክ ከ50,000 በላይ ሠራተኞች 1.4 ትሪሊዮን ዶላር ጥሪት ያለው ነበር። በጀርመን እና አሜሪካ ጨምሮ በ50 አገሮች ከ150 በላይ ቅርንጫፎች የነበሩት ክሬዲት ስዊስ በርካታ ባለጸጋ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ደንበኞቹ ነበሩ።
የክሬዲት ስዊስ ባንክ ቀውስ መነሾ ሲሊኮን ቫሊ እና ሲግነቸር ባንኮችን ለውድቀት ከዳረጋቸው የተለየ ነው። ባለፈው ዓመት ከክሬዲት ስዊስ 10 በመቶ ድርሻ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር የገዛው የሳዑዲ አረቢያ ማዕከላዊ ባንክ ተጨማሪ ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ቀድሞም ችግር ውስጥ የነበረውን ተቋም ወደ ውድቀት አፋፍ ገፋው። በጎርጎሮሳዊው 2022 ባንኩ የኪሳራ ሥጋት ተጋርጦበታል የሚል ወሬ ተዛምቶ ደንበኞች በቢሊዮን ዶላሮች እንዲያወጡ አድርጓል። ደንበኞቹ በአሜሪካ መክፈል የነበረባቸውን ግብር እንዲያሸሹ አመቻችቷል የሚለውን ጨምሮ በበርካታ ቅሌቶች እየተወነጀለ በቢሊዮን ዶላሮች ቅጣት ከፍሏል። ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ኪሳራ ገጥሞት ነበር። የባንኩ የአክሲዮን ዋጋም አሽቆልቁሎ ነበር።
ካፒታል ኤኮኖሚክስ በተባለው የጥናት ተቋም የአውሮጳ ዋና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አንድሪው ኬኒንግሐም "ክሬዲት ስዊስ ከሌሎች አገሮች የፋይናንስ ዘርፎች ጋር በርካታ ግንኙነት አለው። አሜሪካ እና አውሮጳን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ይሰራል። በስዊትዘርላንድ ያለው ክሬዲት ስዊስ ችግር ውስጥ ከወደቀ ፈተና የሚገጥማቸው በርካታ ተበዳሪዎች እና ተቀጥላዎች አሉት" ብለው ነበር።
በስተመጨረሻ ክሬት ስዊስ ባንክ በአገሪቱ መንግሥት ጣልቃ ገብነት በ3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ለተገዳዳሪው ዩቢኤስ ተሸጧል። ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው ዩቢኤስ ከውድቀት አፋፍ የሚገኘውን ክሬዲት ስዊስ ባንክ ለመግዛት የተገደደው በአጠቃላይ የባንክ ዘርፉ ላይ ሊፈጠር የሚችል ቀውስ ባሰጋቸው የስዊትዘርላንድ መንግሥት ባለሥልጣናት ግፊት ነው። የክሬዲት ስዊስ ሊቀመንበር አክሰል ሌሕማን "ያለንን ኃይል እና አቅም ሁሉ አሰባስበን ባንኩን ለመታደግ ሞክረናል። ጊዜ ግን አልፈቀደልንም። የየካቲት ሁለት ሣምንታት ዕቅዳችንን አሰናክለውታል። ይኸ እጅግ ያሳምመኛል። ለዚህ ደግሞ እጅግ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።
ክሬዲት ስዊስን የጠቀለለው ዩቢኤስ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሥራ መደቦች በመላው ዓለም እንደሚያጥፍ ይጠበቃል። ገንዘባቸውን ያጡ የክሬዲት ስዊስ ባለድርሻዎች በለቅሶ እና በተቃውሞ ሆድብሶታቸውን ቢገልጹም መፍትሔ አላገኙም። የአሜሪካ እና የአውሮጳ ባንኮች እና ባለሥልጣናት በጥፍራቸው ቆመው ሲከታተሉት የቆዩት ተከታታይ ቀውስ ጋብ ቢልም ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘቱ ግን ማንም እርግጠኛ አይደለም። በተለይ በመላው ዓለም የበረታውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የብሔራዊ ባንክ ገዥዎች የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ቀደፊትም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚያሳድሩት ጫና የሥጋት ምንጭ ነው።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ