1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈገው የሱዳን ጦርነት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 2018

በሱዳን የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሳተላይት የሚከታተለው የየል ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ ጉዳዮች ጥናት ላቦራቶሪ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ሚሊሻያዎች የፈጸሟቸውን የጅምላ ግድያዎች ማስረጃዎች እያወደሙና እየደበቁ መሆናቸውን የሚያስረዳ ማስጠንቀቂያ የካተተ ዘገባ አቅርቧል።ሂዩመን ራይትስ ዋች በሱዳን ጦር እስር ቤቶች ሰዎች እየሞቱ ነው የሚሉ ዘገባዎች ደርሰውታል።

Sudan Al Dabbah 2025 | Verteilung von Nahrungsmittelhilfe an sudanesische Flüchtlingsfamilien
ምስል፦ Marwan Ali/AP Photo/picture alliance

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተነፈገው የሱዳን ጦርነት

This browser does not support the audio element.

የሱዳኑ ጦርነትከዓለማችን በእጅጉ የተዘነጋ  ቀውስ መሆኑን  ዓለም አቀፍ ለችግር ደራሽ ኮሚቴ  በምሃጻሩ IRC  የተባለው ድርጅት በ22 ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ያካሄደው አንድ የዳሰሳ ጥናት አረጋግጧል። ኮሚቴው በጦርነት የተመሰቃቀለችውን ሱዳንን በመጪው ጎርጎሮሳዊው 2026 ዓ.ም. ዓለም ሊረሳቸው የማይችል  ሲል ከዘረዘራቸው 10 ሀገራትም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። የዶቼቬለዋ ጄኔፊር ሆሌይስ እንደዘገበችው ከሁለት ዓመት በላይ ጦርነት የሚካሄድባት ሱዳን በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. ሁኔታዎች እየተባባሱ የሄዱባት ሀገር ናት።

የተመድ እንደሚለው ቁጥራቸው 14 ሚሊዮን የሚደርስ ሰዎች በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገራት ተፈናቅለዋል  ቁጥር ከ40 ሺህ እስከ 250 ሺህ sእንደሚደርስ የሚገመት ህዝብ በጢርነቱ እንደሞተ ይገመታል። ውጊያው በመቀጠሉና በሳተላይት ይገኝ የነበረ የኢንተርኔት ግንኙነት በመቋረጡ በርካታ የእርዳታ ድርጅቶችና ታዛቢዎችም ከሀገሪቱ በመውጣታቸው ትክክለኛ አሃዛዊ መረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ።

በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው ውጊያ የሱዳን ጦር አንዳንድ ከተሟቿን በተቆጣጠርባት በኮርዶፋን ሆኗል።ኮርዶፋን አሁን በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተከባለች። 
አክሽን አጌይኒስት ሀንገር የተባለው ረሃብን ለመቋቋም የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነ የእርዳታ ድርጅት የጀርመን ክፍል ዋና ሀላፊ ያን ሴባስትያን ፍሪድሪሽ ሩስት ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የኮርዶፋኑ ጥቃት በፍጥነት ተባብሷል። በርሳቸው አስተያየት «በዲሊንግ እና በካዱግሊና በደቡብ ኮርዶፋን የሚገኙ ማህበረሰቦች መከበባቸው ወሳኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስባቸው እያገደ ነው» በዚያ ሰዎች የሚበሉት የላቸውም የመድኃኒትም አያገኙም።

 በዳርፉር ኤልፋሸር እና በካድጉሊ ረሀብ መግባቱ ታውጇል። በሌሎች ዳርፉር የሚገኙ 20 አካባቢዎች እና ኮርዶፋንም የረሀብ አደጋ ላይ ናቸው። የተቀናጀ የምግብ ዋስትና የሚል መጠሪያ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ IPS የተባለe ድርጅት እንዳለው 21.2 ሚሊዮን ሰዎች ከህዝቡ ግማሽ ያህሉ ማለት ነው፣አጣዳፊ የምግብ ዋስትና እጦት ውስጥ  ናቸው።ይህ አሀዝም በመጪው ጎርጎሮሳዊው 2026 እየተባባሰ እንደሚሄድ ተነግሯል። ዓለም ካልተረባረበ ሱዳናውያን ብቻ ሳይሆኑ አጎራባች ሀገሮችም የችግሩ ሰለባ መሆናቸው እንደማይቀር በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የምሥራቅ እና የደቡባዊ አፍሪቃ ሃላፊ አስጠንቅቀዋል።

የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ሚሊሽያዎች የምዕራብ ኮርዶፋንዋን ከተማ ባባኑሳን እንደተቆጣጠሩ ምስል፦ REUTERS

የአክሽን አጌይኒስት ሀንገር ድርጅቱ ፍሪድሪሽ ሩስት ኮርዶፋን ሁለተኛዋ ኤልፋሸር እንዳትሆን ስጋት አላቸው። በሱዳን የሚፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸውን ድርጊቶች በሳተላይት የሚከታተለው የየል ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ ጉዳዮች ጥናት ላቦራቶሪ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ሚሊሽያዎች የፈጸሟቸውን የጅምላ ግድያዎች ማስረጃዎች እያወደሙ እና እየደበቁ መሆናቸውን የሚያስረዳ አዲስ ማስጠንቀቂያ የካተተ ዘገባ አቅርቧል። ላቦራቶሪው ለዚህም ማስረጃ ያለውን አቅርቧል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የሂዩመን ራይትስ ዋች የአውሮጳ ኅብረት ተጠሪ ፊሊፕ ዳም ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በሱዳን የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግ አልቻሉም ። 

«እውነታው ሁለቱም የግጭቱ ተካፋይ ወገኖች እና አጋሮቻቸው ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግ አልተሳካላቸውም ይህ ብቻ አይደለም የጦርነታቸው ማዕከል ሲቪሎችን ኢላማ ማድረግ ነው። ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ወሲባዊ ጥቃቶች ፣በሆስፒታሎች ፣ በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች እንዲሁም ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ፈንጂዎች ጥቅም ላይ የማዋል ተጠያቂነት የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቢሆንም የሱዳን ጦር ኃይልም በሰላማዊ ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን አድርሷል።» ብለዋል።

በሌላ በኩል የሱዳን ጦር ኃይል ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋር ይተባበራሉ ያላቸውን ሰዎችን በገፍ ማሰሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ዳም ለዶቼቬለ ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት ሰዎቹ የሚያዙትም በዘፈቀደ ነው። ከሚታሰሩት መካከልም የሰብዓዊ አገልግሎት ሠራተኞችም ይገኙበታል። ከዚህ በተቸማሪ በእስር ቤቶች ውስጥ ሰዎች እንደሚሞቱ ዘገባዎች ደርሰውናል ብለዋል።
«የሱዳን ጦር ኃይል በሚያስተዳድራቸው እስር ቤቶች በርካታ ሰዎች ስለመሞታቸው ዘገባዎች ደርሰውናል። የሞት ቅጣቶችም እንደገና ስራ ላይ እየዋሉ መሆኑንም እየተመለከትን ነው።»

በርሳቸው አመለካከት በዚህ ወቅት ላይ የአውሮፓ ኅብረት በሱዳን ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በሚፈጽሙት ወገኖች ላይ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። «ምንም እንኳን እኛና ሌሎችም ልናውቃቸው የምንችል ከሃላፊነቱ እና ከተፈጸሙት ወንጀሎች ጋር በግልጽ የተያያዙ ጉዳዮች ቢኖሩም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በምህጻሩ RSF መሪ ጀነራል ሞሐመድ ዳጋሎን ወይም በትክክለኛ መጠሪያው ሄሜድቲ ላይ የአውሮጳ ኅብረት እስካሁን ማዕቀቦች አለመጣሉ ለኔ አስደንጋጭ ነው።» 

የአውሮጳ ኅብረት ለሱዳን ቃል ከገባው ሰብዓዊ እርዳታ የመጀመሪያውን 100 ቶን በያዝነው በታኅሳስ ወር ለሱዳንዋ ዳርፉር  ከአየር ማቀበል ጀምሯል ። ይህ ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረቢያ ድልድይ በመጪው ጥር ጎርጎሮሳዊው 2026 ዓ.ም. ያበቃል። ወጪውም 3.5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 4.1 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የገንዘቡ ድጋፉ የተገኘው ደግሞ ከአውሮጳ ኅብረት ሰብዓዊ በጀት መሆኑን የኅብረቱ ኮሚሽን አስታውቋል። ይሁንና አክሽን አጌይኒስት ሀንገር ከተባለው የእርዳታ ድርጅት ጃን ሴባስትያን ፍሪድሽ ረስት እንደሚሉት ይህ እርዳታ በውቅያኖስ ላይ እንደሚጣል  ጠብታ የሚቆጠር ነው 
«ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ሆኖ እስካሁን ከሚያስፈልጉት የሰብዓዊ እርዳታ የፋይናንስ ምንጮች 35 በመቶው ብቻ ነው የተገኘው።» 

ዴቪድ ሂል / ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW