1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

አስትሮይዶች»ና ሳይንሳዊ ትንታኔያቸው 

ረቡዕ፣ ኅዳር 30 2013

የምንኖርባትን መሬት ጨምሮ በስርዓተ-ፀሐይ ወይም «ሶላር ሲስተም»ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አካላት መኖራቸውን ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።ከነዚህም ውስጥ አለታማ የሆኑ ኮከብ መሳይ አካላት ወይም «አስትሮይድስ» ይገኙበታል።

Vollmond und Wolken
ምስል picture-alliance/B. Coleman/Photoshot.

«አስትሮይዶች»ና ሳይንሳዊ ትንታኔያቸው

This browser does not support the audio element.

 
የየጀርመን ኤሮስፔስ ማዕከል ከሰሞኑ እንዳስታወቀው የእነዚህ አካላት ቁርጥራጭ ሊሆን ይችላል የተባለ ኳስ መሰል እሳት በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል መታየቱን ገልጿል። 
በጀርመን ምዕራባዊ ክፍል አንዳንድ ቦታዎች ያለፈው ሳምንት መገባደጃ በተለምዶ ተወርዋሪ ኮከብ የምንለው አይነት፤ ነገር ግን እሳት መሰልና የኳስ ቅርፅ ያለው ክስተት በምሽት ሰማይ ላይ ታይቷል። 
ያለፈው ሳምንት መጨረሻ በምዕራባዊ የጀርመን ክፍል አንዳንንድ ቦታዎች ያልተለመደ እንግዳ ነገር ተከስቷል። ክስተቱን የተመለከቱ የአይን እማኞች እንደሚሉት ያለፈው እሁድ አመሻሽ ላይ ምንነቱን ያልታወቁት ኳስ መሰል እሳት ከሰማይ ወደ መሬት ሲምዘገዘግ አይተዋል። ይህንንም የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። ይህ ኳስ መሰል ነገር በብልጭልጭታ የታጀበና በውስጡ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ያለው ሲሆን፤ ከአምስት እስከ ሰባት ሰከንድ በዕይታ ውስጥ መቆየቱን ክስተቱን የተመለከቱ ሰዎች ለጀርመን የኤሮስፔስ ማዕከል ገልፀዋል።በዚያው ዕለትም በሰዓታት ውስጥ ወደ 90 የሚሆኑ ይህንን መሰል ክስተቶች መታየታቸውም በዚሁ ማዕከል ተመዝግቧል። ይህ ክስተት ባለሙያዎቹ ምናልባትም ወደ ከባቢ አየር የገባ ኮከብ መሰል ነገር በእንግሊዝኛው አጠራር «አስቴሮይድ»የተባለ ቁርጥራጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል። 
ከ20 በላይ መጻህፍትን ለንባብ ያበቁት የሥነ- ፈለግ ባለሙያው መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ይህ መሰሉ ክስተት የተለመደ ነው ይላሉ።እሳቸው እንደሚሉት በስርዓተ ፀሀይ ወይም «ሶላር ሲስተም»ውስጥ «አስትሮይዶችን»ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አካላት አሉ። እነዚህ የእሳት ኳሶችም ከ«አስትሮይድ» ስብርባሪ የወጡ ሊሆን እንደሚችልም ያስረዳሉ። 
«ስርዓተ ፀሀያችን ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ በውስጠኛው የፅሀይ ስርዓት ውስጥ አለታማ ስሪት ያላቸው አስትሮeዶች አሉ።የበረዶና የዓለት ስሪት ያላቸው ጅራታማ ኮከብ የምንላቸው ኮሜት አሉ።ከኔፕቹን ጀምሮ በአጠቃላይ በውጭኛው ስርዓተ ፀሀይ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካላት አሉ።በአጠቃላይ «ኒር ኧርዝ ኦብጀክትስ»ወይም ለመሬት የቀረቡ አካላት ይባላሉ ኮሚዎች አሉ።አስትሮይዶች አሉ።ሜትዮራይድስ አሉ።ግን አብዛኛው «ፋየር ቦል» እሳታማ ኳሶች ሆነው የሚታዩት ወደ መሬት ከባቢ አየር የሚገቡት የአስትሮይድ ስብርባሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ።ከተለያዩ ፕላኔቶች የወጡ አለቶች ሊሆኑ ይችላሉ።ልክ ወደ መሬት ከባቢ አየር ገብተው ሲቃጠሉ ነው።ሜትየር የሚባሉት ተወርዋሪ ኮከብ መስለው ይታያሉ።በተለይ ከቬኑስ በላይ አብርተው ሲታዩ ደግሞ «ፋየር ቦል» ይሆናሉ።»ብለዋል። 
እንደ ጀርመኑ የኤሮስፔስ ማዕከል ከ 5 ሰከንዶች በላይ የሚታዩት የእሳት ኳሶች በአውሮፓ በአማካይ በዓመት 30 ጊዜ የሚከሰቱ ሲሆን ከተወርዋሪ ኮከብ የበለጠ ረዥምና ብሩህ ናቸው።ይህ ክስተት በተለይም በጥቅምትና እና በታህሳስ ወራት እንደሚከሰትም በማዕከሉ ድረ- ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል። ተመሳሳይ ቁርጥራጭ በጎርጎሮሳዉያኑ ያለፈው ህዳር 19 ላይ በኦስትሪያ ፣ቀደም ሲልም በጥቅምት ወር 2015 ዓ/ም በጀርመን ምስራቃዊ ክፍሎች እና በአጎራባች ሀገሯ ፖላንድ አንዳንድ አካባቢዎች ብዙዎች የተመለከቷቸው ደማቅ የእሳት ኳሶች ታይተዋል።የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል መረጃ እንደሚያሳየው ይህንን መሰሉን ክስተት የሚፈጥሩት «አስትሮይዶች» ጁፒተርና ማርስ በተባሉት ፕላኔቶች መካከል የሚገኙ ሲሆን ፤ከ4.6 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ሥርዓተ-ፀሐይ ወይም «ሶላር ሲስተም»ሲፈጠር እነዚህ ጥቃቅን አካላት ቀደምት ቁሶች ቢሆኑም ጁፒተር በተባለው ፕላኔት ጠንካራ ስበት ምክንያት ራሳቸውን ችለው ፕላኔት መሆን ያልቻሉ አነስተኛ ኮከብ መሳይ ቁርጥራጭ አካላት ናቸው። ሆኖም ግን የዘርፉ ባለሙያዎች «ንዑስ ፕላኔት» በማለት ይጠሯቸዋል። 
እነዚህ ጥቃቅን አካላት የአስትሮይድ ቀበቶ በሚባለው በመካከላቸው በሚገኝ ሰፊ ቦታ ውስጥ ተከማችተው ይገኛሉ። በዚህ ቀለበት ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው «አስትሮይዶች» የሚሰባሰቡ ሲሆን በማርስ እና በጁፒተር ምህዋር መካከል በግምት ከ186 ሚሊዮን እስከ 370 ሚሊዮን ማይል / 300 ሚሊዮን እስከ 600 ሚሊዮን/ ርቀት ላይ ይገኛሉ።በዚህ ስብስብ ውስጥ በሚከሰቱ ግጭቶችም ወደ መሬት የሚደርሱ ቁርጥራጮችንና ብልጭታዎችን ያመነጫሉ ፡፡ 
የምንኖርባትን መሬትን ጨምሮ አጠቃላይ ስርዓተ- ፀሀይ ወይም «ሶላር ሲስተም» የሚባለው ትልቅ ክፍል በውስጡ በርካታ ነገሮችን የያዘ ነው። በዚህ ውስጥ በፀሀይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ መሬትን ጨምሮ ስምንቱ ፕላኔቶች፣ ጨረቃዎች እንዲሁም ፀሀይ ይገኛሉ።ከዚህ በተጨማሪ በውስጠኛው ስርዓተ-ፀሀይ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ አለታማ ስሪት ያላቸው አስትሮይዶችና የበረዶና የአለት ስሪት ያላቸው ጅራታማ ክዋክብትን እንደሚገኙ ባለሙያው ይገልፃሉ። 
ምንም እንኳ በስርዓተ-ፀሐይ ውስጥ በርካታ አስትሮይዶችና ሌሎች አካላት ቢኖሩም ዶክተር ሮዳስ እንደሚሉት ይህንን መሰሉን ክስተት የሚፈጥሩት ግን ለመሬት ቅርብ የሆኑት ብቻ ናቸው። 
በስርዓተ- ፀሀይ ውስጥ የሚገኙ «አስትሮይዶች» ከብናኝ እስከ ግዙፍ መጠን ያላቸው ሲሆኑ፤ አጠቃላይ የስፋት መጠናቸው 930 ማይል (1,500 ኪ.ሜ.) ዲያሜትርን የያዘ ነው ተብሎ ይገመታል ። ይህም መሬት ላይ ከምትታየው የጨረቃ መጠን ከግማሽ በታች መሆኑ ነው። 
ጋስፕራ እና ኢዳ በተባሉ ሁለት ዋና የአስትሮይድ ቀበቶዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በነዚህ ቀበዎች ውስጥ የሚገኙ 
አብዛኛዎቹም ሞለል ባለ ቅርፅና በተረጋጋ ሁኔታ ምህዋር ተከትለው የሚሽከረከሩ ናቸው።ከመሬት ተመሳሳይ አቅጣጫ የፀሐይን ሙሉ ዑደት ዞረው ለማጠናቀቅም« አስትሮይዶች» ከሦስት እስከ ስድስት ዓመታት ይወስድባቸዋል።ያ በመሆኑ ቁርጥራጮቹ ካልሆኑ በስተቀር ትልልቆቹ ከምህዋር ወጥተው ወደ ከባቢ አየር የመግባታቸውና አደጋ የመፍጠራቸው ዕድል እንደ ባለሙያዎቹ አናሳ ነው።ነገር ግን አልፎ አልፎም ቢሆን በዓለማችን ከዚህ ቀደም ያደረሱት ጉዳት መኖሩን የሥነ-ፈለግ ባለሙያው ይገልፃሉ። 
«መሬታችንን ያጠቁ አሉ።በተለይ ዳይኖሰሮችን ያጠፉ የሚባለል አለ።የቅርቡን ማለትም የ1908ቱን ብንመለከት በሳይቬሪያ ሩሲያ የተከሰተውን ወደ 120 ጫማ ማለትም ወደ 37 ሚትር የሚገመት ነው የወደቀው። ክብደቱም ወደ 200 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም 100 ሚሊዮን ኪሎግራም ይሆናል።ወደ 80 ሚሊዮን ዛፎች አቃጥሏል። ወደ 100 አጋዘኖችንም ገድሏል።በጣም በቅርብ 2013 ላይ በሩሲያ አንድ «ሜቲዮራይድ» ወደ መሬት ከባቢ አየር ገብቶ በሰከንድ ወደ 18 ኪሜ መሰለኝ የተጓዘው ብልጭታው እስከ 200 ስኩየር ማይል ያሉ ህንፃዎችን ነው የጎዳው።በጊዜው ወደ 1600 ሰዎችም ተጎድተዋል።ነገር ግን እነዚህ ንዑሳን ናቸው። ቤት የሚያህሉ ትልልቅ ስቴዴየሞችን የሚያህሉም ግዙፍ አስትሮይዶች አሉ።እስካሁን ግን «አስትሮይዶች» ምህዋራቸውን ጠብቀው ይጓዛሉ።እንደ አንድ ቁስም በጣም ይጠናሉ።» 
በጎርጎሮሳዊው 2029 ዓ/ም ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚባል የአስትሮይድ አክስተት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ።ለመሆኑ በዚህ ተፈጥሯዊ ክስተት የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ሳይንሳዊ መላ ይኖር ይሆን? 
«እስካሁን ለመሬት የቀረቡ አካላትን የሚያጠኑ አሉ።እነዚህ ነገሮች ቢመጡ፤ የመሬት የራሷ የፕላኔታዊ መከላከያ አለ።በዚያ ላይ ናሳ፣ሌሎችም የተለያዩ አካላትም ተባብረው ያጠናሉ።ባለፈው አንድ አስትሮይድ ሄደው የማውጣት ክፋይ ይዞ የመመጣት ስራ ሰርቷል።ነገር ግን በጣም አደገኞች ናቸው እነዚህ አስትሮይዶች። ምናልባት ወደ ፊት ከመጡ በምን ይመቱ በኒዩክሌር ይመቱ፣ወይ በጨረር ይመቱ፣መስታውት ተቀምጦ በፀሀይ ጨረር ይቃጠሉ እስካሁን ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። »በማለት ነበር ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የገለፁት። 

ምስል picture-alliance/dpa/NASA/Goddard
ምስል NASA/ZUMA Wire/ZUMAPRESS.com/picture-alliance
ምስል picture-alliance/dpa
ምስል JAXA/AP/picture alliance


ፀሀይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW