1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመት ያስቆጠረው ወረርሽኝና ክትባቱ

ማክሰኞ፣ ጥር 25 2013

የዓለም የጤና ድርጅት ኮሮና ተሐዋሲ የዓለም አሳሳቢ ስጋት መሆኑን ይፋ ካደረገ አንድ ዓመት አስቆጠረ። በዚህ ጊዜ ውስጥ መላው ዓለም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በየፈርጁ የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት ኤኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያናጋ ርምጃዎችን ሲወስድ ታይቷል። መከላከያ ክትባትም በከፍተኛ ፍጥነት መዘጋጀቱ ተሰምቷል።

Impfstoff Pfizer-BioNTech COVID-19
ምስል Christof STACHE/AFP

ዓመት ያስቆጠረው ወረርሽኝና ክትባቱ

This browser does not support the audio element.

 

ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 22 ቀን የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንተርኔት ባካሄደው ኮቪድ 19ኝ የተመለከተ ጉባኤ መላውን ዓለም ስጋት ላይ በጣለው ተሐዋሲ የተያዙት ከመቶ ሚሊየን ማለፋቸውን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገልጸዋል። ተሐዋሲው የዓለም ከፍተኛ አሳሳቢ የጤና ችግር መሆኑን ይፋ ካደረጉ ዓመት እንደሞላው በማስታወስ አሁን የሚታየውን ዘርዝረዋል።

«በወቅቱ አሁን ኮቪድ 19 ብለን በምንጠራው ተሐዋሲ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች የሚገመት ነበር። ከቻይና ውጭም የሞተ ሰውም አልነበረም። በዚህ ሳምንት ደግሞ በተሐዋሲ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 100 ሚሊየን ደርሷል። ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ከመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ይልቅ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተመዘገበው በተሐዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ይላል።»

የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽን ተቀስቅሷልና በስፋት ሳይዛመት እንከላከል የሚል ማስጠንቀቂያውን ባስተላለፈበት ወቅት ለስጋቱ ጆሯቸውን የሰጡት ሃገራት እንዳሉ ሁሉ ችላ ያሉ እንደነበሩም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ዛሬ በተሐዋሲው ያልተነካ ሀገር የለም። በተለይም በመላው አውሮጳና በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ሃገራት የተሐዋሲው መስፋፋት ያሳደረው ተፅዕኖ ጠንከሯል። በዚህም ምክንያት ሃገራት ተሐዋሲውን ለመከላከል የሚያስችለውን ክትባት በየበኩላቸው ለዜጎቻቸው ለማቅረብ እየተረባረቡ ነው። የተለያዩ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የየራሳቸውን ምርምር በማካሄድ ይበጃል ያሉትን ክትባት ለማቅረብ ጥድፊያ ላይ ናቸው። እስካሁን ክትባቱን ለዜጎቻቸው ለማድረስ የሞከሩት በኤኮኖሚው አቅማቸው የጠነከረው ሃገራት መሆናቸው ከዓለም የጤና ድርጅት በኩል ትችትን አስከትሏል። ከሳምንታት በፊት ትዝብታቸውን በይፋ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር የኮሮና ተሐዋሲን ለዓለም አስጊነት ይፋ ያደረጉበትን ዓመት በዘከረው ባለፈው ዓርብ በተካሄደው ስብሰባ ላይም በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተውታል።

ምስል Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

«ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ክትባቶች ሌላ የዕድል መስኮት ከፍተውልናል። አላግባብ ልንጠቀምበት ግን አይገባም። እንደታየው ወረርሽኙ የዓለማችንን ኢፍትሀዊነት አጋልጧል። አሁንም ወረርሽኙን ለማስቆም የሚያስችለው መሣሪያ፤ ክትባት ማለት ነው፤ ይህንኑ ኢፍትሀዊነት ሊያባብሰው ይችላል።»

ባለፉት ወራት መንግሥታት የግል ኩባንያዎች እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች ውጤታማ ክትባት ለማግኘት በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር አፍስሰዋል። በቻይና፣ በአውሮጳውያን ሃገራት፣ በሩሲያ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ተመራማሪዎች በርካታ ክትባቶች ተዘጋጅተዋል። እስካሁን ፋይዘር፣ ባዮንቴክ እንዲሁም ሞደርና የተባሉት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ያዘጋጇቸው ክትባቶች እውቅና ተሰጥቷቸው በተለያዩ ሃገራት እየተሰጡ ነው። ሩሲያ በበኩሏ ሁለት ክትባቶችን አቅርባለች። እስካሁን ከቀረቡት የኮቪድ 19 ክትባቶች ግማሽ የሚሆኑት በቻይና እና በዩናይትድ ስቴትስ ተመራማሪ ቡድኖች የተዘጋጁ ናቸው። በምርምር የተገኙ ክትባቶች እውቅና ማግኘታቸውን ተከትሎ አቅም ያላቸው ሃገራት ለጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በዕድሜያቸው መግፋት ምክንያት ለተሐዋሲው ይጋለጣሉ ለሚባሉት ወገኖች ለማዳረስ እየጣሩ ነው። እስካሁን ክትባቱን ለበርካቶች በማዳረስ ቀዳሚ የሆነችው እስራኤል ናት።

እንዲያም ሆኖ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ጀርመን እስካሁን ለጤና ባለሙያዎችና በዕድሜያቸው ምክንያት ለተሐዋሲው ሊጋለጡ ይችላሉ ለሚባሉት ወገኖች ሁሉ ማዳረስ እንዳልቻለች ነው የሚነገረው። በዚህም ምክንያት የራሽያና የቻይናን ክትባቶች ለመጠቀም ዝግጅት መኖሩን የጀርመን የጤና ሚኒስትር የንስ ሽፓን ጠቁመዋል። ሩሲያ ፈቃድ ካገኘ ስፑትኒክ ቪ የተሰኘውን የኮቪድ 19 ክትባት 100 ሚሊየን ብልቃጥ ለአውሮጳ ሕብረት ለማቅረብ እችላለሁ ብላለች። ለክትባቱ እውቅና ለማግኘትም ማመልከቻው ለአውሮጳ የመድኃኒት ባለሥልጣን ቀርቧል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚያሳስበው ክትባትን ለሌሎች ሃገራት ማጋራትን በተመለከተ ዶቼ ቬለ ቴሌቪዥን የጠየቃቸው የጀርመን የጤና ሚኒስትር የንስ ሽፓን ኩባንያዎች የመላኪያ ፈቃዱን ካገኙ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

ምስል Jonathan Hordle/PA Wire/empics/picture alliance

«የመድኃኒት ኩባንያዎች በአግባቡ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረጉ መልካም ሀሳብ ነው። በዚህም የትኛው ክትባት አውሮጳ ውስጥ ተመርቶ ወይም ታሽጎ ከአውሮጳ ሕብረት ተላከ የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል። ፈቃድ ማግኘት ማለት እንዳይላክ ታገደ ማለት አይደለም፤ ቢያንስ መመዝገብና እውቅና ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ በበርካታ ጉዳዮች የሚደረግ ሲሆን ለራሳችን ብቻ ልናደርገው ሳይሆን ፍትሀዊ እንዲሆን እንፈልጋለን። የአቅርቦት እጥረት ሲያጋጥም ችግሩ ለአውሮጳ ሕብረት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚደርስ ነው። ምርት ላይ ያለው ችግር ክፍፍሉ ላይ ሊያመጣው የሚችለው ተፅዕኖ ለጊዜው እርግጠኛ ያልሆንበት ጉዳይ ነው።»

የኮቪድ 19ን መዛመት ለመግታት ሃገራት ክትባቱን ለማዳረስ በሚያደርጉት ጥረት መሃል ችግሮች መከሰታቸው ይሰማል። በቂ ክትባት ካለመቅረቡ ሌላ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ለህልፈተ ሕይወት የተዳረጉ መኖራቸውም ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ኖርዌይ ውስጥ 33 ፤ ጀርመን ውስጥም 10 በዕድሜ የገፉት ሰዎች ክትባት ከወሰዱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል። ሆኖም የጤና ባለሙያዎች ሕይወታቸው ያለፈው አዛውንቶች ጉዳይ በቀጥታ ከክትባቱ ጋር አይገናኝም ባይ ናቸው።

ምስል Frank Hoermann/Sven Simon/imago images

በነገራችን ላይ የስዊድና የብሪታንያ የመድኃኒት ኩባንያዎች በጋራ የመሠረቱት አስትራዛኒካ ለኮቪድ 19 መከላከያ ያዘጋጀውን ክትባት ፈቃደኛ በሆኑ 1500 ሰዎች ላይ ሞክሯል። ሆኖም የክትባቱ ሙከራ በቂ የመድኃኒት መጠን ያካተተ አለመሆኑን ሮይተርስ ይፋ አድርጓል። ስህተቱ መፈጸሙን የሚያሳይ መረጃ ያገኘው ሮይተርስ እስካሁን ክትባቱን የወሰዱት ሰዎች ስለገጠማቸው ችግር በተመራማሪዎቹ በኩል የተባለ ነገር አለመኖሩን አመልክቷል። ከክትባቱ ጋር የተገናኙ አንዳንድ አሉታዊ ገጠመኞች ቢኖሩም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት ያግዛል የሚለው ሀሳብ በማመዘኑ ሃገራት በብዛት እንዲቀርብላቸው በማዘዝ እየተጠባበቁ ነው። ጀርመን እስከ መጪው መጋቢት ወር አጋማሽ ድረስ 80 ሚሊየን ክትባት ትጠብቃለች። ክትባቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያዚያ ወር ይደርሳል እየተባለ ነው። በዚህ መሐል ከማናቸውም ማኅበራዊ መስተጋብርም ሆነ ከተለያዩ እንቅስቃሴዎች ታግዶ የሚገኘው ተሕዋሲው እጅግ የተስፋፋባቸው ሃገራት ነዋሪ ክትባቱ ተዳርሶ ወደ ወትሮው የሕይወት መስመር ለመግባት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW