1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ዕቁብ መተግበሪያ፤ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የጀማሪ ቴክኖሎጂዎች ውድድር አሸናፊ

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016

በስፔን በተካሄደ ዓለም አቀፍ የጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ውድድር ዕቁብ መተግበሪያ አሸናፊ ሆኗል። መተግበሪያው ኢትዮጵያውያን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ዲጅታል በሆነ መንገድ ዕቁብ የሚጥሉበት ሲሆን፤ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ለፍፃሜ ቀርበው ከነበሩ ከቤኒን፣ ከስፔን፣ ከአይዘርባጃን እና ከአሜሪካ ከመጡ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች መካከል ነው ።

በቅርቡ በስፔን ባርሴሎና በተካሄደ ዓለም አቀፍ የጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ውድድር  ዕቁብ የተሰኜ መተግበሪያ በገንዘብ-ነክ ቴክኖሎጅ ዘርፍ የዘንድሮ አሸናፊ ሆኗል
በቅርቡ በስፔን ባርሴሎና በተካሄደ ዓለም አቀፍ የጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ውድድር ዕቁብ የተሰኜ መተግበሪያ በገንዘብ-ነክ ቴክኖሎጅ ዘርፍ የዘንድሮ አሸናፊ ሆኗል።ምስል eQUB Financial Technologies

ዕቁብ መተግበሪያ የዓመቱ ምርጥ ቴክኖሎጅ

This browser does not support the audio element.


.
በስፔን ባርሴሎና በየዓመቱ በሚካሄደው የሞባይል ወርልድ ኮንግረስ /Mobile World Congress/ዓለም አቀፍ የጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ውድድር  ከኢትዮጵያ ዕቁብ የተሰኘ መተግበሪያ በገንዘብ-ነክ ቴክኖሎጅ ዘርፍ /FinTech category / የ2024 አሸናፊ ሆኗል።
ዕቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ በተባለ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ የተመሰረተው  ይህ መተግበሪያ፤ ኢትዮጵያውያን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካኝነት ዕቁብ የሚጥሉበትን ዲጅታል ቴክኖሎጅ ከሶስት ዓመታት በፊት ፈጥሯል።
ዕቁብ መተግበሪያ ዮሐና ኤርሚያስ እና አሌክሳንደር አባይ ህዝቂያስ በተባሉ ሁለት ወጣቶች በየካቲት 2013 ዓ/ም ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ ከሽልማቱ በፊት ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ መሻሻሎች ማድረጋቸውን የዕቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ተባባሪ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ወጣት አሌክሳንደር ገልጿል።የምትወደውን ሙያ ያገኘችው ዮሃና ኤርሚያስ

«ወደ 2020 አካባቢ ነው የተመሰረተው ዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጅ። ከዚያም ዕቁብ አፕ የሚል መተግበሪያ ወደ ገበያ ይዘን መጥተናል። ይህ መተግበሪያም በፕሌይ ስቶር ለአንሮይድ ተጠቃሚዎች አቅርበን ነበር።አሁን ደግሞ ለአይኦስም ለአፕል ተጠቃሚች ዝግጁ አድርገናል ማለት ነው።በእነዚህም ሶስት አመታትም ጥሩ የሚባሉ «ዲቨሎፕመንቶች»ን አድርገናል።ለምሳሌ ያህል ከተለያዩ ባንኮች ፣ማይክሮ ፋይናንሶች እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ሲeስተማችንን ለብዙሃኑ ተጠቃሚ ተደራሽ ማድረግ ችለናል ይህንን መተግበሪያ ስለዚህ ብዙ የሚባሉ ለውጦችን አድርገናል።ወደ 25,000 ተጠቃሚዎችን ወደ መተግበሪያው አምጥተናል ።»በማለት ከሽልማቱ በፊት ያደረጓቸውን መሻሻሎች አብራርቷል።  

አሌክሳንደር ዓባይ ህዝቂያስ ፤የዕቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጅ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅምስል eQUB Financial Technologies

ከዚህ በተጨማሪ አሌክሳንደር እንደሚለው ዕቁብ መተግበሪያ ሲጀምር በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ብቻ  የተወሰነ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት በሁለት መንገዶች አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ ይገኛል። «አንደኛው ሞዴል በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል «ፕራይቬት» ነው የምንለው የሚተዋወቁ ዕቁብተኞችን ዕቁባቸውን  በዲጅታል መንገድ የሚጥሉበትን ቴክኖሎጅ አቀረብን።ከዚያ በመቀጠል «ሆስትድ» ዕቁብ የምንለው ድርጅቱ ያዘጋጃቸው ዕቁቦች አሉ።ስለዚህ እነዚህ ዕቁቦች ራሳቸውን የቻሉ ይዘቶች አሏቸው።ለምሳሌ ለሰራተኞች ተብለው የተዘጋጁ አሉ።የመንግስትም ሆነ የግል ሰራተኞች በወር ደሞዝ የሚተዳደሩ ከሆነ የወርሃዊ ጥቅሎችን አዘጋጅተን እነሱን የምናስገባበት ማለት ነው።» በማለት ገልጿል።

ይህ ዲጅታል መድረክ በወርሃዊ ገቢ ከሚተዳደሩ ሰዎች በተጨማሪ በቀን ገቢ ለሚተዳደሩም ዕለታዊ ዕቁብ ያዘጋጃል። ዕቁብተኛ በመሆን  አገልግሎቱን ለማግኘት ግን በተጠቃሚዎች ዘንድ ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች አሉ።
«ድርጅቱ በሚያቀርበው መስፈርት መሰረት ማሟላት ያለባቸው ልዩ ልዩ መስፈርቶች አሉ።ለምሳሌ የመታወቂያ፣ የቅጥር ደብዳቤ ሊሆን ይችላል። የቢዝነስ ላይሰንስ የመሳሰሉትን አቅርበው ፤በዚህ መሰረት ድርጅቱ እያንዳንዱን ክፍያቸውን ይከታተላል ማለት ነው።ለነዚህም ግለሰቦች ሀላፊነት ይወስዳል ማለት ነው።»ካለ በኋላ፤ በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ለሚደረግ የግል ዕቁብ ግን ይህንን መስፈርት እንደማይጠይቁ ተናግሯል። 

ዕቁብ መተግበሪያ አሸናፊ የሆነው ለፍፃሜ ከደረሱ አራት የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችን በማሸነፍ ነውምስል eQUB financial technologies

በዚህ ሁኔታ በዕቁብ መተግበሪያ በአሁኑ ጊዜ ከ250 ያላነሱ ዕለታዊ፣ ሳምንታዊ እና ወርሃዊ አከፋፈል ያላቸው ዕቁቦች መኖራቸውን  ያስረዳል።ባለፉት ሶስት ዓመታት መተግበሪያውን ችግር ፈቺ ለማድረግ ሲሰሩ መቆየታቸውን የሚገልጸው አሌክሳንደር፤ ማሻሻያዎችን ለማድረግም ከተጠቃሚዎች በኢሜል እና በስልክ ሀሳብ ይቀበላሉ።በዚህም መተግበሪያው ከተጠቃሚዎች ጥሩ ግብረመልስ እንዳለው ገልጿል።
መተግበሪያው መጀመሪያ ላይ በእንግሊዥኛ ቋንቋ ብቻ የተዘጋጄ ቢሆንም ቆይቶ ግን አማርኛ ቋንቋን አካቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኦሮምኛ፣ የትግርኛ እና የሶማልኛ ቋንቋዎችን ለማካተት እየሰሩ ሲሆን፤ በሂደትም የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ እንዳላቸው አሌክሳንደር ተናግሯል።መተግበሪያውንም ከ«አፕስቶር» ወይም  ከ«ፕሌይ ስቶር» በማውረድ መጠቀም እንደሚቻል ገልጿል።ዕቁብተኛ ለመሆን ደግሞ ተከታዩን ሂደት ማለፍ ይጠይቃል።እቁብዎን በእጅ ስልክዎ

«አንድ ግለሰብ የዕቁብ አፕን ለመጠቀም በቀላሉ የሞባይል ስልክ ያስፈልገዋል።በሞባይል ስልኩ በሚላክለት የሚስጥር ቁጥር የሱ ሞባይል መሆኑን ያረጋግጣል።ከዚያ በመቀጠል የራሱን ስም፣ ሙሉ አድራሻ እና «ቤዚክ» የምንላቸውን የመለያ ጥያቄዎች ይመልሳል።ከዚያ በመቀጠል የራሱ የሚፈጥረው ዕቁብ ከሆነ በቀላሉ መፍጠር ይችላል።ጓደኞቹ ጋብዘውት የሚመጣ ዕቁብተኛ ካለ ግብዛውን እዚያው ላይ ማግኘት ይችላል።የኛ ድርጅት ባዘጋጃቸው ጥቅሎች ለመግባት የሚፈልግ ዕቁብተኛ ካለ ደግሞ የተለያዩ የመታወቂያ እና ማሟላት ያለባቸውን ሰነዶች ለምሳሌ የስራ ቅጥር ደብዳቤ ሊሆን ይችላል ፣የንግድ ፈቃድ ሊሆን ይችላል  ከመታወቂያ ጋር ይዞ መጥቶ ውሉን መዋዋል ይችላል።»በማለት ሂደቱን አስረድቷል።

የነ አሌክሳንደር ዕቁብ መተግበሪያ ስፔን ባርሴሎና በተካሄደው ውድድር የተሳተፈው የተለያዩ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችን በመደገፍ በሚታወቀው ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /ITC/ በኩል  የተሳትፎ ዕድል በማግኘታቸው ነው።በውድድሩ በዓለም ዙሪያ በርካታ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የተሳተፉ ቢሆንም፤ለፍፃሜ የበቁት ግን ከቤኒን፣ ስፔን፣ አዘርባይጃን እና ከዩኤስ አሜሪካ የመጡ አራት ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች እና የኢትዮጵያው ዕቁብ ናቸው። በመጨረሻም በጎርጎሪያኑ የካቲት መጨረሻ  2024 ዓ/ም ዕቁብ መተግበሪያ በውድድሩ የዘርፉ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል።

መተግበሪያው አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው በዘርፉ ከተወዳደሩት እና ለፍፃሜ ከደረሱ ከቤኒን፣ ከስፔን፣ ከአይዘርባጃን እና ከዩኤስ አሜሪካ ከመጡ አራት ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች መካከል ነው ምስል eQUB Financial Technologies

እንደ አሌክሳንደር ገለጻ፣ በውድድሩ አሸናፊ መሆናቸው  ቁጠባ እና ብድርን ዲጂታል በሆነ መንገድ ተደራሽ የማድረግ ዓላማቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዕድል የሚሰጥ ነው። ከባርሴሎናው ውድድር አሸናፊነት በተጨማሪ፤ መተግበሪያው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችን ለመደገፍ በጌት ፋውንዴሽን እና በሌሎች አጋር ድርጅቶች በተመሰረተው፤ ቢማላብ ኢትዮጵያ /BimaLab Ethiopia/ በተባለው መርሀግብር፤  ከሌሎች የላቀ ስራ ሰርተዋል ተብለው ከተመረጡ አራት ሀገር በቀል ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ጋር የ10ሺህ ዶላር  ሽልማት በቅርቡ አግኝቷል።

ዕቁብ መተግበሪያ፤ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችን ለመደገፍ በጌት ፋውንዴሽን እና በሌሎች አጋር ድርጅቶች በተመሰረተው፤ ቢማላብ ኢትዮጵያ በተባለው መርሀግብር፤ ከሌሎች የላቀ ስራ ሰርተዋል ተብለው ከተመረጡ አራት ሀገር በቀል ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ጋር የ10ሺህ ዶላር ሽልማት አግኝቷል።ምስል eQUB Financial Technologies

ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበራዊ የቁጠባ እና የብድር አገልግሎትን በቀላሉ የማድረስ ዓላማ ይዞ፤ ከሶስት ዓመት በፊት በሁለት ወጣቶች የተመሰረተው ዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጅስ፤ አሁን ከሃያ በላይ ለሆኑ ወጣቶች  የስራ ዕድል ፈጥሯል። በዚህ ዲጅታል መድረክ ከሁለት መቶ  እስከ አስር ሺ ብር መዋጮ ያሏቸው እና በአንድ ዕጣ  ከአምስት ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር ክፍያ ያላቸው ዕለታዊ፣ ሳምታዊ እና ወርሃዊ ዕቁቦችንም እያስተናገደ ይገኛል። ይህንን ስራቸውን አጠናክረው በመቀጠልም ከኢትዮጵያ አልፎ በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት አገልግሎቱን የማድረስ ዕቅድ እንዳላቸው ዋና ስራ አስኪያጁ ያስረዳል። አሌክሳንደር እንደሚለው ዕቁብ ለኢትዮጵያ ልዩ ተቋም ቢሆንም፤ አፍሪቃ ውስጥም በተለምዶ የቁጠባ እና የብድር አገልግሎትን መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚሰጡ  ማህበራት አሉ። በመሆኑም ይህንን ነባር አገልግሎት ዲጅታል በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ፤ ዕቁብ መተግበሪያን ወደ ተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ማስፋፋትን  ታሳቢ ማድረጋቸውን አስረድቷል። 

ወጣቶቹ  የሶስት ዓመት ጉዟቸው ለሽልማት ቢያበቃቸውም አሌክሳንደር እንደሚለው የገንዘብ ድጋፍ ማጣትን  ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲገጥማቸው ቆይቷል። በመሆኑም በዲጅታል ቴክኖሎጅ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ በርትተው እንዲሰሩ መክሯል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

 ፀሀይ ጫኔ

ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW