1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና የአሁኑ ዘመን ጦርነት

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2017

የ21 ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት የአሁኑን ዘመን ጦርነት በብዙ መልኩ ለውጦታል። ከሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሰውሰራሽ አስተውሎት እስከ ሳይበር ጦርነት እና የላቁ የመገናኛ ዘዴዎች ድረስ የዛሬዎቹ የጦር ሜዳ ውሎዎች ከጥቂት አስርተ አመታት በፊት ከነበሩት ሲነፃጸሩ በእጅጉ የተለዩ ናቸው

ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት  የጦርነት ገፅታንም በብዙ መልኩ ቀይሯል
ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት የጦርነት ገፅታንም በብዙ መልኩ ቀይሯልምስል፦ Getty Images

ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና የአሁኑ ዘመን ጦርነት

This browser does not support the audio element.

ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት የሰዎችን  የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማሻሻል አልፎ  የጦርነት ገፅታንም በብዙ መልኩ ቀይሯል።ሰውሰራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቶች እና እራሳቸውን ችለው የሚሰሩ እንደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች  ወይም ድሮኖች  ላይ በማተኮር  ወታደራዊ ቴክኖሎጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን እድገት አሳይቷል። ለመሆኑ  እነዚህን ቴክኖሎጅዎች አደጋዎች ምንድን ናቸው? ከሞራል እና ከመርህ አንፃር የሚነሱ ጥያቄዎችስ?የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ትኩረት ነው።

በዓለም  ላይ የቴክኖሎጂ እድገት የጦርነትን ባህሪን  በመቅረጽ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።ከቀስተ ፣ጎራዴ  እና ጋሻ ፈጠራ እስከ አቶሚክ ቦምብ ልማት ድረስ፤ ፈጠራዎች የጦርነትን ውጤት እና ወታደራዊ ስልቶች ይወስናሉ። የ21 ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት ደግሞ የአሁኑን ዘመን ጦርነት በብዙ መልኩ ለውጦታል። ከሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሰውሰራሽ አስተውሎት  እስከ ሳይበር ጦርነት እና የላቁ የመገናኛ ዘዴዎች ድረስ የዛሬዎቹ የጦር ሜዳ ውሎዎች ከጥቂት አስርተ አመታት በፊት ከነበሩት ሲነፃጸሩ በእጅጉ የተለዩ ናቸው። ፊት ለፊት ከሚደረግ ውጊያ ይልቅ ጦርነቱን የቴክኖሎጅ ብልጫ ሆኗል።

በጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ከ2.7 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ለወታደራዊ አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጪ ተደርጓል።አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን እና ህንድ 60 በመቶውን የአለም  ወታደራዊ ወጭን ይሸፍናሉ። ይህ ወጪ  ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ወደ 10 በመቶ ብልጫ አለው።ነገርግን በአሁኑ ወቅት ውድ ታንኮችበሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሚታገዙት እንደ ድሮን ባሉ ርካሽ የጦር መሳሪያዎች እየተተኩ ነው።የመረጃ ደህንነት -ባለሙያ ኮንስታንዝ ኩርዝ ዩክሬንን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።»ዩክሬን በማይታመን ሁኔታ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በታላቅ ስኬት እየተጠቀመች ነው ።ሩሲያያን ያጠቁባቸው ከተለመደው ወጣ ያሉ ዘዴዎቻቸው  አስደናቂ ነበር።»በዚህ ሁኔታ የዩክሬን ወታደሮች እንደ ቴሙ እና አሊ ኤክስፕረስ ካሉ ርካሽ  የቻይና የችርቻሮ ገበያዎች ሳይቀር ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመግዛት እየገጣጠሙ እና ፈንጂዎችን እያያዙ ተፈላሚቸውን ሩሲያን ያጠቃሉ።በዚህ መንገድ በጥቂት መቶ ዩሮዎች ብቻ የሚሸጥ ሰው አልባ አውሮፕላን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ ታንክን ያወድማል።ከወጭ ቆጣቢነቱ ባሻገር  የአብራሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ ሳይጥል ትክክለኛ ኢላማዎችን እንዲመቱ ያስችላቸዋል።

የሰዎች ክትትል እና ቁጥጥር አስፈላጊነት

ዩክሬን እስከ 2000 ኪሎ ሜትር በሚበሩ ድሮኖች በሩሲያ ጥቃት ስትፈፅማለች።ሩሲያም ዩክሬን ውስጥ ወታደራዊ ቦታዎችን፣ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እና የመኖሪያ ሕንፃዎችን በሚያነጣጥሩ በሰው አልባ አውሮፕላኖች  ትመታለች።በዚህ ሁኔታ ሰው አልባ የሆኑ የአየር ላይ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት፤  ትክክለኛ ጥቃቶችን እና አሁናዊ መረጃዎችን መሰብሰብ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዴት እንደሚካሄዱ መለወጥ አስችሏል።ያም ሆኖ ሙኑክ የሚገኘው የጀርመን ጦር ማሰልጠኛ ዩንቨርሲቲ የደህንነት ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ፍራንክ ዛወር  እንደሚሉት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ብቻውን ጦርነቱን አያሸንፉም።«በድሮኖች ብቻ ቦታዎችን መውሰድ እና መያዝ አትችልም። ለምሳሌ መሬት ላይ ስራ ያስፈልገዋል። በመሠረቱ፣ የዩክሬን ጦር ኃይሎች ግዛትን መቆጣጠር እና መያዝ አለባቸው፣ እና ያ በድሮኖች እና በሮቦቶች ብቻ አይቻልም። »ብለዋል።

ሰውሰራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቶች እና እራሳቸውን ችለው የሚሰሩ እንደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች  ወይም ድሮኖች  ላይ በማተኮር ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት አሳይቷል። አውሮፕላኖች የአብራሪ ህይወትን አደጋ ላይ ሳይጥሉ የክትትል፣ የግንዛቤ እና የተነጣጠሩ የጥቃት ኢላማዎችን የመፈፀም  አቅምን በማሳደግ የአሁን ዘመን ጦርነቶች ዋነኛ ገፅታ ሆነዋል።በአጠቃላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከነባሮቹ አውሮፕላኖች ይልቅ  ረዘም ላለ ጊዜ በመሥራት፣ አደገኛ ወይም ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን መድረስ እና ለውሳኔ ሰጪዎች ቅጽበታዊ መረጃን በመስጠት በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣሉ።እንደ ሽብር እና ጦርነትን በመሳሰሉት ተግባራት በመቀነስ እና ዋስትና ያለው ስትራቴጂካዊ ግቦችን በማሳካት ረገድ ውጤታማ ናቸው።የደህንነት ፖሊሲ ባለሙያው የሆኑት ፍራንክ ዛወር ግን የሰዎች ቁጥጥር ወሳኝ ነው ይላሉ።።«ሊኖረን የሚገባው ዝቅተኛው መስፈርት ሰው አልባ  እና በራሳቸው የሚሰሩ የጦር መሣሪያዎችን  ስንጠቀም ፤ እኛ ማለቴ የጀርመን ጦር ወይም  ኔቶ  ትርጉም ያለው የሰው ልጅ ቁጥጥርን እናረጋግጣለን። ለምሳሌ፣ ሰዎች ተገቢ የሆነ የትእዛዝ ደረጃ አላቸው።»ሲሉ ገልፀዋል።

ሰው አልባ የሆኑ የአየር ላይ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት፤ አሁናዊ መረጃዎችን መሰብሰብ ትክክለኛ ትክክለኛ ዒላማዎችን ይመታሉ።ነገር ግን ሰላማዊ ሰዎችንም ይጎዳሉ።ምስል፦ Sofiia Bobok/AA/picture alliance

ያለሰው የሚሰሩ የጦር ቴክኖሎጅዎች  የስነምግባር ችግር

በሌላ በኩል ሰው አልባ አውሮፕላኖች  በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉበት ጊዜም አለ። በተለይም ተዋጊዎች እና ሰላማዊ ሰዎች በአንድ ላይ በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ የሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ይበረታል።ከዚህ አንፃር በዚህ ቴክኖሎጅ ላይ የሞራል እና የስነምግባር ጥያቄ ይነሳል።በመረጃ እና በስልተቀመር /አልጎሪዝም/ ብቻ እንዲሰሩ የተነደፉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ መረጃዎችን የያዙት ሮቦቶች እና ድሮኖችን የመሳሰሉ ሰው አልባ ማሽኖች ውሳኔ ሊወስኑ የሚችሉት ቅድመው በተሰጣቸው መረጃ ብቻ ነው።ስለሆነም ተዋጊዎችን እና ተዋጊ ያልሆኑትን የመለየት ችሎታ እና እንዲሁም በገሃዱ ዓለም ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በመስረት ትክክለኛ ውሳኔ የመስጠት ችሎታ የላቸውም። ከዚህ አኳያ ያልተፈለገ ውጤት ሊያስከትል ይችላል የሚለው  ስጋት በዚህ ቴክኖሎጅ ላይ ይነሳል።

ገዳይ ሮቦቶች ይቁሙ ዘመቻ የጀርመን ቃላአቀባይ የሆኑት ቶማስ ኩሸንማይስተር  ክትትል ሊደረግ ይገባል ባይ ናቸው።«በእኔ እይታ ይህ አዝማሚያ  ክትትል ሊደረግበት ይገባል። ሰዎች ቀስ በቀስ ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲወጡ ይደረጋሉ።እና ማሽኑ ብዙ ውሳኔዎችን ይሰጣል። እናም በተወሰነ ጊዜ ላይ፤ እኔ ወይስ ማሽኑ? ከሚል ጥያቄ ጋር ይጋፈጣሉ። » ብለዋል።በራሳቸው በሚሰሩ የጦር ማሽኖች ጥገኝነት  እየጨመረ መምጣቱ የሰው ልጅ ውሳኔ በጦርነት ውስጥ ስለሚኖረው ሚና ጥያቄ ያስነሳል። ሰውሰራሽ አስተውሎት  በጦር ሜዳ ላይ የመወሰን አቅም የስነምግባር ማዕቀፎችን እና የተጠያቂነት ስርዓትን ባለሙያዎች እንደገና መገምገም ያስፈልገዋልም ይላሉ።

ኩሸን ማይስተር የሚሰሩበት ፤ገዳይ ሮቦቶችን የማቆም ዘመቻ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በራሳቸው የሚሰሩ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያግድ ወይም ቢያንስ እንዲቆጣጠር እየወተወተ ነው። ​​ነገር ግን እስካሁን ድረስ የተባበሩት መንግስታት አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ አልቻለም።  ለብዙ ባለሙያዎች እነዚህን በሰው የማይታዘዙ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር ሀገራት የመስማማት እድላቸው በጣም ጠባብ ነው። ምክንያቱም ብዙ የጥቅም ግጭቶች አሉ።ለምሳሌ ጀርመን  ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን  በተመለከተ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ስታመነታ ቆይታለች።  ብዙዎችም ከዘመኑ ጋር  አብሮ አለመሄድ ነው ሲሉ  ይከራከራሉ። ነገር ግን የኔቶ ከፍተኛ  አዛዥ  የሆኑት አድሚራል ፒሪ ቫንዲር ጉዳዩ የህይወት ጥያቄ ነው ይላሉ።

«ዩክሬን ውስጥ ታየዋለህ።ስለዚህ ጉዳዩ የሕይወት ጥያቄ ነው። በፍጥነት እና በችሎታ የተካኑ ካልሆኑ  ትሞታለህ። እና ስለዚህ የምናየው ስርዓት እና አዲሱ ቴክኖሎጂ የበለጠ ትክክለኛ እና በጣም ገዳይ ነው።ዛሬ ጦርነቱ  የሚደረገው  በሰው አልባ አውሮፕላኖች ነው።ስለዚህ  ለታቀደው ውጤት  በቀጥታ ወደ ኢላማው ስለሚሄዱ ጠላትን ነጥሎ የመምታት ችሎታ በጣም ወሳኝ ነው።»

የሳይበሩ ዓለም  ጦርነት 

ሌላው ዘመናዊ ቴክኖሎጅ የፈጠረው የጦርነት ገፅታ የሳይበር ጥቃት ነው።ይህ ጦርነት ጥይት የማይጦህበት ቢሆንም በፖለቲካም ይሁን በወታደራዊ መልኩ ሌሎች ሀገራትን ለመጉዳት ይውላል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ  ጦርነት የጀመረችው በሳይበር ጥቃት  ሲሆን ቁልፍ የመገናኛ ሳተላይቶች ስታር ሊንክ የሚባለው የቤሌነሩ ኤለን ማስክ  የሳተላይት ግንኙነት እስኪፈጠር ድረስ ተቋርጠው ነበር።የሳይበር ጥቃቶች በወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ በማህበራዊ ድረ-ገጾች  ላይ ጥልቅ የውሸት ወሬዎችን መስፋፋትን ያካትታል።ስለዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎችጋር  ቀስ በቀስ እየተካተተ በመምጣቱ የሳይበር ጦርነት ስጋት በዓለም ላይ እንዲጨምር አድርጓል።

የሳይበር ጥቃት ጥያት የማይጮህበት የዘመኑ ጦርነት አንዱ ገፅታ ነው።ምስል፦ Andrew Brookes/IMAGO

በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የበለጠ ጥገኛ እየሆን በመምጣታችን ደግሞ የሳይበር ጦርነት እያደገ ነው።በሆስፒታል ላይ የሚደርስ የሳይበር ጥቃት እንክብካቤን ሊያስተጓጉል ይችላል። የኃይል ማመንጫዎች ቁጥጥር ስርዓትን መጥለፍ የኃይል መቆራረጥ ሊያስከትል ይችላል።ለነዚህ ችግሮች እንደ ስታር ሊንክ ያሉ በግል የሚሰጡ መፍትሄዎችም ባለሙያዎች እንደሚሉት የራሳቸው ችግር አለባቸው።«ስታርሊንክ በጣም ውጤታማ እና አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ መንግስታት ለምሳሌ ዋሽንግተን እና ፔንታጎን የጠፈር ችግርን ለመፍታት  ስፔስ ኤክስን ጠይቀዋል። ለብዙ አገሮች ይህንን እራሳችን እንዴት መፍታት እንችላለን? በግሉ ዘርፍ ምን ያህል መታመን እንችላለን? ምን ዓይነት ውሎች ያስፈልጋሉ እና መንግስትስ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ነው»በማለት ገልፀዋል።

ስለዚህ ወሳኝ መሠረተ ልማትን መጠበቅ ብዙ አገሮች መከላከያቸውን ለማጠናከርአዳዲስ ክፍሎችን እየፈጠሩ ነው።ቡንደስዌር የሚባለው የጀርመን ጦር የመረጃ ደህንነት ዋና ኃላፊ ኮሎኔል ጊዶ ሹልቴ የሳይበር ምዳር የማኅበረሰብ ፈተና ነው ይሉታል።-«የማህበረሰቡ አጠቃላይ ፈተና በሳይበር ምህዳር ነው። በአሁኑ ጊዜ እንደ ባህላዊ ግጭቶች  ከወታደራዊ ሀይሎች ጋር የሚደረግ  አድርገን ማየት አንችልም። ይልቁንስ ጥያቄው በጠቅላላ ማኅበረሰቡን  እንዴት ማዘጋጀት እንችላለን የሚለው ነው። »ብለዋል።።

የስነምግባር ማዕቀፎች አስፈላጊነት

በአጠቃላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የጦር የመሳሪያ ቅልጥፍና እና ትክክለኛነት ጨምረዋል። ነገር ግን ሰብአዊነትን ማጉደል እና በጦርነት ውስጥ ያሉ የስነምግባር ችግሮች በጣም አሳሳቢ እና አፋጣኝ ትኩረት የሚፈልጉ መሆናቸው ይነገራልአዲስ ቴክኖሎጂ በመጣ ቁጥርም  ከሰብዓዊነት ይልቅ የኃይል ፉክክር  እያመዘነ እንዳይመጣ እና ውድመቶች እንዳይከሰቱ  የእነዚህን ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም እና አተገባበር የሚቆጣጠሩ አለም አቀፍ ደንቦችን  እና የስነምግባር መመሪያዎችን ማውጣት  ወሳኝ መሆኑን የመብት ተከራካሪዎች ይገልፃሉ።

 

ፀሀይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW