1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዘምዘም ባንክ ካፒታሉን 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ አክሲዮኖች እየሸጠ ነው

ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነጻ ባንክ የሆነው ዘምዘም ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ አክሲዮኖች ለዲያስፖራ እየሸጠ ነው። ባንኩ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ሁለት ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ይኖርበታል። የሸሪአ መርህ የሚከተሉ ባንኮች፣ አጠቃላይ ሐብታቸው፣ ተቀማጭ እና የደንበኞቻቸው ቁጥር ቢጨምርም መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች አሉ

የዘምዘም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች
ከ100 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የዘምዘም ባንክ ካፒታል እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2017 ድረስ ብቻ ሦስት ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር እንድሪስ ዑመር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል፦ Zamzam Bank

ዘምዘም ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ አክሲዮኖች እየሸጠ ነው

This browser does not support the audio element.

ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያሳድጉ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠላቸው ቀነ-ገደብ የሚያበቃበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሔድ ዘምዘም ባንክ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ አክሲዮኖች እየሸጠ ይገኛል። ቀነ-ገደቡ በተለይ በማዕከላዊው ባንክ “ትናንሽ” ተብለው የተደለደሉትን የሚመለከት ሲሆን የተከፈለ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2018 ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን ያወጣው ሚያዝያ 4 ቀን 2013 ነበር። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባንኮች የቀራቸው አስር ወራት ገደማ ነው። ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን ካወጣ ጀምሮ ዘምዘም ባንክ ቅድመ-ሁኔታውን ለማሟላት “ካፒታል ማሳደጊያ የፕሮጀክት ቢሮ ከፍቶ” ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የባንኩ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር እንድሪስ ዑመር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ በተጓዙባቸው የተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሐዋላ እና ካፒታሉን ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ሲያከናውኑ እንደቆዩ የተናገሩት አቶ እንድሪስ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በብር አክሲዮኖች እንዲገዙ መፍቀዱ ተጨማሪ ዕድል እንደፈጠረ ገልጸዋል።

ከ100 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የዘምዘም ባንክ ጠቅላላ ሐብት 16.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን አቶ እንድሪስ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ባንኩ ከደንበኞቹ የሰበሰበው ተቀማጭ 11.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ባለፈው ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር አትርፏል። የዘምዘም ባንክ ካፒታል እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2017 ድረስ ብቻ ሦስት ቢሊዮን ብር ቢደርስም በብሔራዊ ባንክ በተወሰነው መሠረት የተከፈለ ካፒታሉን ለማሳደግ ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ ማሰባሰብ አለበት።

ለምን ዲያስፖራ?

ዘምዘም ባንክ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ላይ ያተኮረው “በሀገሩ ኢንቨስት ማድረግ እንዲችል እና በሀገሩ የባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ” እንዲያበረክት ዕድል ለመስጠት እንደሆነ የዘምዘም ባንክ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ መሐመድ አሕመድ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የወለድ ነፃ ባንክ “ኢንደስትሪ በጣም ያልዳበረ” እንደሆነ የጠቀሱት አቶ መሐመድ ዕገዛ ለማድረግ የሚፈልጉ የዲያስፖራ አባላት መኖራቸውን ዘምዘም ባንክ በመገንዘቡ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል።

አቶ እንድሪስ ባለፉት ዓመታት “ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በእኛ ሀገር በተጨባጭ መተግበር የሚችል የሚያዋጣ፣ ትርፋማ ቢዝነስ መሆኑን፤ በገበያውም ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል” መታየቱን ይናገራሉ።ምስል፦ Zamzam Bank

ዘምዘም ባንክ በአሁኑ ወቅት 17,000 ገደማ ባለ አክሲዮኖች አሉት። ባንኩ ሽያጭ የጀመረው የአክሲዮን ግብይቱን የመቆጣጠር ሥልጣን ካለው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝቶ እንደሆነ አቶ መሐመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “እነዚህ ነባር አክሲዮኖች ከሕዳር 2017 በፊት ማሟላት የሚገባንን ዝቅተኛ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ አውጥተናቸው ከነበሩት አክሲዮኖች ናቸው። ከዚያ በኋላ ሌላ አዳዲስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ ያቀረብናቸው አይደሉም” ሲሉ አስረድተዋል።

ዘምዘም ባንክ ወደ ሥራ የሚያስገባውን ፈቃድ የተረከበው ጥቅምት 02 ቀን 2013 ይናገር ደሴ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሳሉ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለረዥም ዓመታት የተከተለውን ግትር አቋም ቀይሮ የሸሪአ መርህን መሠረት ባደረገ መልኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚያቀርቡ ተቋማት ወደ ገበያው እንዲገቡ ከፈቀደ በኋላ የባንኮቹ ቁጥር እየጨመረ ነው።

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ሲስፋፋ ምን ተለወጠ?

አቶ እንድሪስ ባለፉት ዓመታት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ “በተጨባጭ መተግበር የሚችል የሚያዋጣ፣ ትርፋማ ቢዝነስ መሆኑን፤ በገበያውም ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል” መታየቱን ይናገራሉ። “እጅግ ከፍተኛ የሆነ የደንበኞች ፍላጎት እንዳለ በተግባር” መታየቱን የገለጹት አቶ እንድሪስ “ምንም ካልነበረበት ደረጃ ተነስቶ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እዚህ ደረጃ ለመድረስ በጣም ብዙ ተደክሞበታል። ውጤቱም ቀላል ነው ብለን የምናስበው አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ 3.5 ትሪሊዮን ብር ሲደርስ የወለድ ነፃ ባንኮች በአንጻሩ እስከ ነሐሴ 2017 ባለው ጊዜ ወደ 392 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል። ኢንዱስትሪው 27 ሚሊዮን ደንበኞች አሉት። በኢንዱስትሪው አራት ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንኮች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ስምንት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በተመሣሣይ የሥራ ዘርፍ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ወደ 22 የሚሆኑ ንግድ ባንኮች ለወለድ ነፃ ባንክ ብቻ በተመደቡ ቅርንጫፎች እና መስኮቶች አገልግሎት እያቀረቡ ነው።

ለወለድ ነፃ ባንክ የተከፈቱ 933 ቅርንጫፎች፤ ወደ 10,000 የሚጠጉ መስኮቶች መኖራቸውን እንደ አዎንታዊ ውጤት የሚጠቅሱት አቶ እንድሪስ “ከሚጠበቀው እና መድረስ ከሚገባው አኳያ ግን በጣም ብዙ መሠራት ያለባቸው ነገሮች” አሉ የሚል እምነት አላቸው።

በወለድ ላይ የተመሠረተ የባንክ ሥራ ለረዥም ዓመታት በዘለቀበት የኢትዮጵያ ገበያ የወለድ ነፃ ባንክ ሲገባ “ራሱን የቻለ፤ የራሱ የሆነ eco system መገንባት” አስፈልጎታል። መፍትሔ የሚሹ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት እንድሪስ “ለምሳሌ የወለድ ነፃ የባንክ ሥራዎች አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ (Comprehensive legal framework) እና ከተደራራቢ ግብር ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች አሉባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ባንኮች ሲቋቋሙ ሥራቸውን የሚሠሩበት እና ፈቃድ የሚሰጥበት አቅጣጫዎች” ቢኖሩም ከወለድ ነፃ የባንክ ሥራ “አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፉ ምን መምሰል አለበት” የሚለው ከቁጥጥር ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው።  የወለድ ነፃ የባንክ ኢንዱስትሪ ሥርዓት የማበጀቱ ሒደት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን የገለጹት አቶ እንድሪስ “ከዚህ በኋላ በሚኖረው ምዕራፍ ብሔራዊ ባንክ እና መንግሥትም ትልቅ ትኩረት ሰጥተውት የፋይናንስ አገልግሎት አካታችነትን ለማሳደግ እየተሰራበት ሲመጣ ትልቅ ለውጦች ይታያሉ” የሚል ዕምነት አላቸው።

ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያሳድጉ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠላቸው ገደብ ሰኔ 23 ቀን 2018 ያበቃል። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ከወለድ ነፃ የባንክ ሥራ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትን ጨምሮ ተቋማዊ ተግዳሮቶች አሉበት። አሁን በዘርፉ እያገለገሉ የሚገኙት በአብዛኛው በግል እና በውጪ ሀገራት የተማሩ እና የሰጠኑ ባለሙያዎች ናቸው። አቶ እንድሪስ የወለድ ነፃ ባንክ ኢንዱስትሪን ለመደገፍ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሥርዓተ-ትምህርት ተቀርጾ ባለሙያዎች ማሰልጠን እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ወለድ ነፃ ባንኮች ትርፍን ከሚያካትቱ ተከታታይ ክፍያዎች በኋላ ንብረት በባንክ ወደ ደንበኛ የሚሸጋገርበት ሙራባሃ የተባለ የብድር ሥርዓትን ጨምሮ በተወሰኑ የአገልግሎት አይነቶ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው እየተባሉ ይተቻሉ። ባንኮቹ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ውስንነት እንዳሉባቸው የሚያምኑት አቶ እንድሪስ አዳዲስ አገልግሎት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይህ በተራው የተማረ የሰው ኃይል እና የሕግ ማዕቀፍ ይፈልጋል። ባንኮቹ ተደራሽነታቸውን ለማስፋፋት እና ቅርንጫፎች ለመክፈት የሚያስፈልጋቸው ገንዘብም ሌላው ፈተና ነው። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ባለፉት ዓመታት በባንኮች የብድር ምጣኔ ላይ ተጥሎ በቆየው ገደብ ምክንያት ብዙ ባንኮች ቅርንጫፍ ከመክፈት ለመቆጠብ ተገደዋል።

መንታ የባንክ አሠራር ሥርዓቶች

በፋይናንስ ዘርፉ የተዘረጉ አንዳንድ የአሠራር ሥርዓቶች በወለድ የሚሠሩትን እና የሸሪአ መርህ የሚከተሉ ባንኮችን ዕኩል የሚያስተናግዱ አይደሉም። እንደ ግምዣ ቤት ሠነድ ያሉ የመንግሥት የዕዳ መሣሪያዎች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኩል ሲሸጡ በቀዳሚነት የሚሳተፉት ባንኮች ናቸው። በጎርጎሮሳዊው 2025/26 የመጀመሪያ ሁለት ወራት ማለትም በጥር እና የካቲት ገንዘብ ሚኒስቴር በገበያው አራት ዐይነት የመንግሥት የግምዣ ቤት ሠነዶች በጨረታ ሸጦ 111 ቢሊዮን ብር ገደማ ተበድሯል።

የዕዳ ሠነዶቹን በመግዛት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የጡረታ ፈንዶች 80% ድርሻ ይዘዋል። ሌሎች የንግድ ባንኮች 13.5% ድርሻ ሲኖራቸው የተቀረው በኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተያዙ ናቸው። የብድር ሠነዶቹ ከ28 እስከ 364 ባሉት ቀናት ሲጎመሩ ወለድ ይከፈልባቸዋል።

ይህ ግን የሸሪአ መርህን መሠረት አድርገው ከሚሰሩ ኢስላማዊ ባንኮች ሊሳተፉበት የሚችል አይደለም። አቶ እንድሪስ “በወለድ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ እዚያ ላይ መሳተፍ አንችልም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከመንግሥት የግምዣ ቤት ሠነዶች በተጨማሪ ባንኮች እርስ በርስ የሚበዳደሩበት ሥርዓት (interbank money market) በወለድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ “ኢስላሚክ ፊቸር የለውም።”

በጎርጎሮሳዊው 2025/26 የመጀመሪያ ሁለት ወራት ማለትም በጥር እና የካቲት ገንዘብ ሚኒስቴር በገበያው አራት ዐይነት የመንግሥት የግምዣ ቤት ሠነዶች በጨረታ ሸጦ 111 ቢሊዮን ብር ገደማ ተበድሯል።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

“ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንኮች ለምሳሌ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ቢያጋጥማቸው እንደ ሌሎቹ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ሔደው መፍትሔ ሊያገኙበት የሚችሉበት አሠራር አልተሠራም” የሚሉት አቶ እንድሪስ ሁለቱ መንታ የባንክ ሥርዓቶች ዕኩል እንዲሠሩ ለማድረግ “ፈቃደኝነት እና ፍላጎቱ እንዳለ እንረዳለን። የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። እነዚያን ግን ቶሎ እያጠናቀቁ ጎን ለጎን ዕኩል የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳ ከማድረግ አኳያ አሁንም ውስንነቶች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

“እነዚያ ውስንነቶች ከቴክኖሎጂ፣ ከእውቀት ጋር ክፍተቶች እና ተግዳሮቶች ሊኖሩባቸው እንደሚችሉ እንረዳለን” የሚሉት አቶ እንድሪስ “ነገር ግን ክፍተቱ በጣም መስፋት እና እነዚህ ባንኮች ዕድሉን ማጣት አይጠበቅባቸውም። ዋጋ መክፈል አይኖርባቸውም” የሚል አቋም አላቸው።  

ሒደቱ ዘገምተኛ ቢሆንም የኢትዮጵያ ገበያ የውጪ ባንኮች ለመቀበል በመዘጋጀት ላይ ነው። የውጪ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደውን ማሻሻያ በበላይነት ሲመሩ የቆዩት ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከገዥነታው ከመሰናበታቸው በፊት ብሔራዊ ባንክ ከሰኔ 18 ቀን 2017 ጀምሮ የውጪ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች ማመልከቻዎችን መቀበል እንደጀመረ አስታውቋል።

ኬሲቢ ግሩፕ እና ኢክዊቲ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የመግባት ፍላጎታቸውን ያሳወቁ የኬንያ ባንኮች ናቸው። ከጅቡቲ የባንክ ኢንዱስትሪ 45% ድርሻ የያዘው ሬድ ሲ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ባንክ (BCIMR) በተመሳሳይ አዲስ ወደተከፈተው ገበያ የመግባት ፍላጎት እንዳለው በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

የውጪዎቹ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አቶ እንድሪስ በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል የተሻለ አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠብቃሉ። ባንኮቹ ከተመሠረቱባቸው ሀገራት ውጪ የመሥራት ልምድ ያላቸው በመሆኑ የተሻለ አገልግሎት ከሰጡ በኢትዮጵያ ገበያ ጠንከር ያለ ውድድር ሊፈጠር ይችላል። እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ፍላጎቱን በይፋ ያሳወቀ ሙሉ በሙሉ በሸሪአ መርህ ላይ የተመሠረተ ከወለድ ነፃ ባንክ የለም።

ዘምዘም ባንክ በ2030 በሸሪአ መርህ ላይ የተመሠረተ እና ሁሉን አካታች በአፍሪካ ቀዳሚ የወለድ ነፃ ባንክ የመሆን ዓላማ እንዳለው ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት አቶ እንድሪስ ዑመር ይህን ተልዕኮውን ባከበረ መንገድ ሐሳብ ካለው ወገን ጋር በጋራ ለመሥራት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል።

አርታዒ አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW