1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረኝነት በጀርመን

ማክሰኞ፣ ጥር 9 2015

ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ጀርመናውያን 90 በመቶው ዘረኝነት በጀርመን ያለ ችግር መሆኑን እናውቃለን ሲሉ አረጋግጠዋል።ከውጭ ዜጎች 22 በመቶው ደግሞ በቀጥታ የዘረኝነት ሰለባ እንደነበሩ ተናግረዋል።በ2022 በይፋ ከተመዘገቡት ፖለቲካዊ መነሻ ካላቸው 1,042 የጥቃት ወንጀሎች ሁለት ሦስተኛ ያህሉ ዘረኛ ጥቃቶች መሆናቸው አሀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።

Reem Alabali-Radovan Lagebericht "Rassismus in Deutschland"
ምስል Christian Ditsch/epd-bild

ዘረኝነት በጀርመን

This browser does not support the audio element.

በጀርመን ማኅበረሰብ ውስጥ ዘረኛ ጥቃት ብቻ ሳይሆን፣የዕለት ተዕለት ስልታዊ ዘረኝነት አሁንም  ያሉ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን በቅርቡ ይፋ የተደረገ አንድ አዲስ ዘገባ ጠቁሟል።የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን  ትኩረት ነው። ሪም አላባሊ ራዶቫን በጀርመን መራሄ መንግስት ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴታና የፌደራል ጀርመን የፍልሰት፣የስደተኞች፣የውኅደትና የፀረ-ዘረኝነት ኮሚሽነር ናቸው። አላባሊ ራዶቫን በጀርመን የዘረኝነት ይዞታ ላይ ያተኮረውን የመንግሥታቸውን ዓመታዊ ዘገባ ይፋ ባደረጉበት ጋዜጣዊ መግለጫቸው «ሰዎችንና በጀርመን መሠረታዊ ሕግ የተደነገገውን ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚያጠቃ ሲሉ ነበር ዘረኝነትን የገለጹት። ኮሚሽነሯ  ዘረኝነትን «በዲሞክራሲ ላይ የተጋረጠ ከባድ አደጋ»ም ብለውታል ።የጥቃቱ ሰለባዎችም የተሻለ ድጋፍ እንደሚያሻቸውና ለዘመናት ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ የቆየው በውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሱ አድልዎና ማግለል ከከዚህ ቀደሙ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። መስሪያ ቤታቸው ለዚህ ጥናት መጠይቅ ካደረገላቸው ጀርመናውያን 90 በመቶው ዘረኝነት በጀርመን ያለ ችግር መሆኑን እናውቃለን ሲሉ አረጋግጠዋል።ከውጭ ዜጎች  22 በመቶው ደግሞ በቀጥታ የዘረኝነት ሰለባ እንደነበሩ ተናግረዋል።በጎርጎሮሳዊው 2022፣በይፋ ከተመዘገቡት ፖለቲካዊ መነሻ ካላቸው 1,042 የጥቃት ወንጀሎች መካከል ሁለት ሦስተኛ ያህሉ ዘረኛ ጥቃቶች መሆናቸው አሀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።ሆኖም ነጻ የሚባሉ የምክር አገልግሎት ሰጭዎች እንዳሉት ግን አካላዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚጠቁሙ 1,391 የስልክ ጥሪዎች ደርሰዋቸዋል።  ባብል ኤፋው በጀርመን ዘረኝነትን ለመወጋት ከ30 ዓመታት በፊት የተቋቋመ   መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። ከዛሬ 40 ዓመት በፊት አንስቶ ጀርመን የሚኖሩት የድርጅቱ መስራችና ሃላፊ ዶክተር መኮንን ሽፈራው በጥናቱ የተጠቀሰውን በጀርመን የዘረኝነት ሰላብ የሆኑትን  ቁጥር ከፍተኛ ብለውታል። ዘረኝነት በመታገል ሂደትም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኟቸው የቆዳ ቀለማቸው ከጀርመናውያኑ የተለየ ሰዎች በሙሉ ጀርመን ውስጥ በተለያየ መንገድ የዘረኝነት ሰላባ መሆናቸውን መረዳት እንደቻሉ ገልጸዋል። 
የአላባሊ ራዶቫን ዘገባ ዘረኝነት በጥላቻና በጥቃት ብቻ የሚገለጽ አይደለም ይላል ።ይልቁንም ሰዎችን ከስራና ከገበያው ዓለም በተለያየ መንገድ በማግለል ፣በፖሊስ ጭካኔ እንዲሁም በትምሕርት ቤቶች ወይም በህክምናም ጭምር የሚገለጽ መሆኑን ያስረዳል። ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሂጃብ የምታደርግ ሴትና ስሟ የጀርመን የሆነ ሌላ ሴት ጀርመን ውስጥ ለአንድ ክፍት የስራ ቦታ ቢወዳደሩ ሂጃብ የምታደርገው ለቃለ መጠይቅ የምትጠራበት እድል የጀርመን ስም ካላት ጋር ሲነጻጸር በአራት ጊዜ ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ነው ኮሚሽነሯ የተናገሩት ።ዶክተር መኮንንም  ከዚህ ጋር የተያያዙ እውነታዎችን አካፍለውናል። የሪም አላባሊ ራዶቫን መስሪያ ቤት በአንድ ወቅት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከተሳተፉት አንድ ሦስተኛው ወደ ጀርመን የሚካሄድ የሙስሊሞች ፍልሰት መገደብ አለበት ሲሉ 27 በመቶው ደግሞ በርካታ ሙስሊሞች ጀርመን ይኖራሉ የሚል መልስ ሰጥተዋል።  የቆዳ ቀለማቸው በጠቆረ ሰዎች ላይ ስለሚፈጸም ዘረኝነት ፣በተካሄደ የዳሰሰ ጥናት የተሳተፉ 886 ሰዎች ደግሞ የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ ወይም ደግሞ በሌሎች ላይ ሲደርስ እንዳዩ ተናግረዋል። ጉዳዩን ለሚመለከታቸው ሃላፊዎች ያመለከቱት ደግሞ ባለስልጣናት አቤቱታቸውን ባስተናገዱበት መንገድ ደስተኛ እንዳልሆኑ ነው ያስረዱት።አንዳንዶች ደግሞ ችግር ያስከትልብናል ብሎ በመፍራትም ወይም በፍርሃት ይሁን ወይም የተፈጸመባቸው ወንጀል መሆኑን ባለማወቅ ለባለስልጣናት ከመናገር ይቆጠባሉ።ዶክተር መኮንን እንደሚሉት በአንዳንድ ሁኔታዎች አንድ ሰው ዘረኝነት እንደተፈጸመበት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ማሰመኑ ከባድ ወይም የማይሳካ ሊሆን ይችላል።
 በጀርመን ዘረኝነት በየአጋጣሚው የሚነሳ ችግር መሆኑን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የእስያ ዝርያ ባለቸው ነዋሪዎች ላይ የደረሰው የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ከተካሄደባቸው 700 እስያውያን ግማሽ ያህሉ የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ አስረድተዋል። መቀመጫውን በርሊን ያደረገው ዘረኝነትን ለመከላከል የተቋቋመው የባብል ኤ ፋው መስራች ዶክተር መኮንን ዘረኝነትን ለመከላከል ፖለቲካው ብቻ መፍትሄ አይሆንም ይልቁንም  ችግሩ እንዲፈታ የሁሉም ዜጋ ትብብር ያስፈልጋል ይላሉ። የጀርመን የፀረ ዘረኝነት ኮሚሽን ሃላፊ  አላባሊ ራዶቫን መስሪያ ቤታቸው በጀርመን ዘረኝነትን ለመከላከል የሚያስችል የምክር አገልግሎትን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ ስለፀረ ዘረኝነት ፖሊሲ  መንግሥትን የሚያማክሩ የባለሞያዎች ቡድን እንዲቋቋም ለማድረግ፣በኢንተርኔት የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ላይ ጠንከር ያሉ ሕጎችን ለማውጣት እና የፌደራል ግዛቶች የከተሞችና የአካባቢ ባለስልጣናት መሪዎች በጉዳዩ ላይ ይበልጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ ማቀዱን ተናግረዋል።  

ምስል Boris Roessler/dpa/picture alliance
ምስል DW/Yilma Hinz
ምስል Rome/Photoshot/picture alliance

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW