1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረፋና እገታ በቄለም ወለጋ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2015

በአከባቢው የጸጥታ ችግሩ መራዘሙ እና ዘላቂ እልባት ማጣቱ ሰው እንደየአቅሙ ከቅርብ እስከ ሩቅ እየተፈናቀለ አከባቢውን እንዲለቅና እንዲሰደድ እያስገደደው ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን የአዝመራ ወቅት ቢሆንም የሰው የመስራት ፍላጎትም በእጅጉ መውረዱን አንስተው አብራርተውልናል፡

Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

ታጣቂዎቹ የሚዘርፉን ሌሊት ነዉ-ነዋሪ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የሃዋ ገላን ወረዳ ነዋሪዎች ሐብት ንብረታቸዉ በየጊዜዉ በታጣቂዎች እንደሚዘረፍ አስታወቁ።በተለይ የመቻራ ከተማባ የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደሚሉት የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ባለፈዉ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በአካባቢዉ በሸመቁት እራሳቸዉን የኦሮሞ ነፃነት ጦር ብለዉ በሚጠሩት ታጣቂዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት ታጣቂዎቹን ከከተማ አባርረዋቸዋል,።ይሁንና ጨለማን ተገን የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ነዋሪዎችን ያግታሉ፤ ንብረታቸዉንም ይዘርፋሉ።የቄሌም ወለጋ ዞን የፀጥታ ኃላፊም ኦነግ-ሸኔ ያሉት ኃይል ሕዝቡብ እንደሚዘርፍ አረጋግጠዋል።ስዩም ጌቱ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ በመቻራ ከተማ የሰፈራ ጣቢያ ነዋሪ ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ብለው በሰጡን አስተያየት፤ በዚህ አከባቢ የተንሰራፋው ሁከት  ዓመታትን ማስቆጠር ጀምሯል፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት  የጸጥታ ስጋቱ አረጋግቶ ቤት እንኳ የሚያስቀምጥ ሳይሆን ማደሪያቸውንም የስጋት ቦታ አድርጎባቸዋል፡፡

“መረጋጋት የለም፡፡ ዘረፋ ነው የሚካሄድብን፡፡ ብር አምጡ እየተባለ የሌለውን መደብደብ አሊያም ከብት ሽጠህ አምጣ ማለት ነው ያለው፡፡ አሁን ባለው የጸጥታ እጦት ህዝቡ ውጪ ነው የሚያድረው፡፡ ይህም ቤት ውስጥ እንዳንታፈን በሚል ነው ህዝቡ ተሰብስቦ ውጪ የሚያድረው፡፡”

የ7 ሰላማዊ ዜጎች ህይወትን እንደ ቀጠፈ የሃምሌ 04 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ታጣቂዎች በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ መቻራ ከተማ ላይ ጥቃት ከፍተው በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የአከባቢውን ማህበረሰብ ዋቢ አድርገን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም ከዚያ ወዲህ የጸጥታው ፈተና እንደቀጠለበት ነው ባይ ናቸው፡፡ “ከዚያ ወዲህ የተረጋጋ ነገር የለም፡፡ በተለይም አሁን ወጣ ባሉ መንደሮች ላይ ዘረፋ ይፈጸማል፡፡ አምና ጥቃት ደርሶ በርካቶች ያለፉበት መንደር 20 እና ለምለም የሚባል ቀበሌም ዘረፋው ከፍቶ ሰው ተፈናቅለዋል፡፡ ጭር ባለበት ሌሊት ከ5፡00 ጀምሮ ዘረፋው ይፈጸማል፡፡ በተለይም ደህና ብር ያለው የሚባል ሰው እረፍት የለው፤ ይዘረፋል፡፡”

ከዚህው አከባቢ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪም ዘረፋው አሁን አሁን በአከባቢው የተለመደ የሰርክ ተግባር ሆኗል ነው የሚሉት፡፡ “ዘረፋው ተለምዷል ምንም አዲስ ነገር ኤደለም፤ ከርመንበታል፡፡”

በአከባቢው የጸጥታ ችግሩ መራዘሙ እና ዘላቂ እልባት ማጣቱ ሰው እንደየአቅሙ ከቅርብ እስከ ሩቅ እየተፈናቀለ አከባቢውን እንዲለቅና እንዲሰደድ እያስገደደው ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን የአዝመራ ወቅት ቢሆንም የሰው የመስራት ፍላጎትም በእጅጉ መውረዱን አንስተው አብራርተውልናል፡፡ “ነገሩ የመስራት ፍላጎትም ያጠፋል፡፡ ተስፋ የለውም ሰው ለመኖር፡፡”

በዚው ሃዋ ገላን በሚባል ወረዳ ከዚህ በፊት አምና ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. መንደር 20 እና 21 በሚባሉ የሰፈራ ቦታ ታጣቂዎች በሌሊት አደረሱት በተባለ ጥቃት ብያንስ 97 ሰዎች ገደማ በጅምላ መገደላቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ስለአሁናዊው የነዋሪዎች እሮሮ ተጠይቀው ስለዚህ መረጃ የደረሰን ዘገባ የለም ያሉት የቄለም ወለጋ ዞን ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ ተሰማ ዋሪዮ፤ “ያው ዘረፋው አለ፡፡ ኦነግ ሸነ የሚባል ኃይል በጫካ ውስጥ እየዞረ ሰላማዊ ሰው ይዘርፋል፡፡ አሁን ስላልከን ጉዳይ ግን ሪፖርቱ አልደረሰንም፡፡”

በኦሮሚያ ክልል በተለይም ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች ተደጋጋሚ የዘረፋ እና እገታ ዜናዎች ተሰምተዋል፡፡ ይህን ዘረፋ የሚፈጽመው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ያለው ሸነ የተባለ ኃይል ነው በሚል በመንግስት ተደጋጋሚ ክስም ይቀርብበታል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ግን ዘረፋውን እኔ አልፈጽምም በማለት ደጋግሞ ሲያስተባብል ተሰምቷል፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW