ዘንድሮ ከ287 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶች ተሰርቀዋል-መስሪያ ቤት
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2017
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ287 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደተሰረቀበት አስታወቀ።መንግስታዊው የኤሌክትሪክ ኃይል ተቆጣጣሪና አቅራቢው ድርጅት ከምን ጊዜውም የከፋ ያለው የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶች እና የኃይል ስርቆት ከባለፈው ዓመት ጋር እንኳ ስነጻጸር በአራት እጥፍ ከፍቶ መታየቱን ነው ያመለከተው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እስከ ሃምሌ በተጠናቀቀው የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት 287.5 ሚሊየን ብር (አምስት ሚሊየን ዶላር) በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና በኃይል ስርቆት የደረሰበትን ኪሳራውን በገለጸበት ሪፖርቱ ይህ በዚህ በተገባደደው የኢትዮጵያውን ዓመት በስርቆት ያጋጠመው ኪሳራው ከፍተኛ ስጋት መደቀኑንና የአገልግሎት ተደራሽነት ጥረቶችን ፈተና ውስጥ ስለማስገባቱ ተጠቁሟል፡፡
በስርቆቱ የደረሰው የዘንድሮውየመሰረተ ልማት ጉድለቱ አምና እንኳ ካጋጠመው የ64 ሚሊየን ብር ግድም ኪሳራ ጋር ስነጻጸር በአራጥ እጥፍ ጉዳቱ የከፋ ስለመሆኑም ነው የተመላከተው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዋር አብራር በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት በኤሌክትሪክ መሰረተልማት አውታር እና በኃይል ስርቆት ላይ የሚፈጸም ስርቆት አሳሳቢ ሆኗል ነው ያሉት፡፡ “የኤሌክትሪክ መሰረተልማትም ሆነ የሃይል ስርቆቱ እንደሀገር እጅጉን ጎጂ ነው” ያሉት አቶ አንዋር ይህን ንበረት ከስርቆት የማዳን ትልቁ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ መሆኑን ጠቁመው፤ አገልግሎቱ ግን ግንዛቤን ከማስጨበጥ ጀምሮ ለኤሌክትሪክ መሰረተልማት አውታር ጥበቃ በሚያደርገው አዋጅ መሰረት ስርቆቱን በሚፈጽሙት ላይ ቅጣት እንዲጣል ክትትሎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተፈጸሙ ስርቆትመካከል 216 ሚሊየን ብር ግድም የሚገመተው ኪሳራ የተመዘገበው በኤሌክትሪክ መሰረተልማት ስርቆት ሲሆን 71 ሚሊየን ግድሙ ግን በኃይል ስርቆት የተመዘገበ መሆኑንም ነው የአገልግሎቱ መረጃ ያሳየው፡፡ የጸጥታ ሃይሎች ከተቋሙ ጋር በመስራት 35 ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ ስለመቻሉም ተጠቁሟል፡፡ “በ2017 በጀት ዓመት በኤሌክትሪክ መሰረተልማት አውታሮች እና በሃይል ስርቆት ምክንያት 287 ሚሊየን ብር ግድም የሚገመት ኪሳራ ደርሷል” ያሉት ቃልአቀባዩ፤ በዚህ ተግባር ተሰማሩ ባሏቸው ላይ ተጠያቂነት ለማስከተል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሰረተልማት አውታሮችን ለመጠበቅ የወጣው አዋጅ በስርቆት ላይ ተሰማርቶ በተገኙት ላይ እንደ ወንጀሉ ክብደት ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት ማስቀጣትን ጨምሮ በ50 ሺህ ብር መቀጩ እንዲቀጡ ይደነግጋል፡፡ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶቹ በዋናነት የስርቆት አደጋ የተጋረጠባቸው በአከባቢ ተለይቶ ይታወቅ እንደሆነም የተጠየቁት አቶ አንዋር “መረጃዎቹ ከመላው አገሪቱ የተሰበሰቡ ቢሆንም ገና ዝርዝር ጥናቶች ግን የሚስፈልጉት ነው” የሚል ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ የኤሌክትሪክ መሰረተልማት ስርቆቱ በኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነት ስራዎች ላይ ግን የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል፡፡ “የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ላይ የሚፈጸም ስርቆት ሃይል በተፈለገ መጠን እንዳይሰራጭ ከማድረግም አልፎ ለሌላ ኤሌክትሪካ ማዳረሻ ይውል የነበረው በጀት ለመልሶ ጥገና ስለሚውል ጉዳቱ ግልጽ ነው” ሲሉም አቶ አንዋር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት ካሉበት መሰል ተግዳሮቶች ውጪ ግን በበጀት ዓመቱ ከቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታፊፍ፣ ከንግድ እና የተለያዩ ተቋማት ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ