ዛሬ ገበያ፤ ለሸማቾች ወቅታዊ የገበያ መረጃ የሚያቀርበው ዲጅታል መድረክ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2016መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትካለባቸው ሀገሮች አንዷ ነች። ቀድሞውንም ከፍተኛ የነበረው የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት የብርን የመግዛት አቅም የሚቀንሰው አዲሱ የምንዛሪ ተመን ይፋ ከሆነ ወዲህ ደግሞ እጅጉን ጨምሯል።
በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሱቆች ውስጥ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ መሄዱን ሸማቾች ይገልፃሉ። በብር መዳከም ምክንያት ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጣሸቀጦችም የዋጋ ንረቱ ተባብሷል።
ዛሬ ገበያ እና የዋጋ ውድነት
ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ዛሬ ገበያ የተባለ ዲጅታል መድረክ ለሸማቾች በየቀኑ የዋጋ መረጃ በማቅረብ ላይ ይገኛል።የዛሬ ገበያ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዝሩባቤል ዮሃንስ እንደሚለውም መነሻቸው በየጊዜው የሚታየው የዋጋ ንረት ነው።
«የተነነሳንበት ምክንያት እዚህ ሀገር ያለው የ«ፕራይስ ፍላክቹየሽን»እና «አርቲፊሻል ኢንፍሌሽን» በማየት ነው የተነሳነው።አንዳንድ እቃዎች በእጥረት ምክንያት ሊጨምሩ ይችላሉ። ግን ዝምብሎ መሀል ላይ ባሉ ደላሎች ዝምብሎ ዋጋ ለምን ይጨምራል በሚል ነው የተነሳነው።»ካለ በኋላ፤ ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የዋጋ መረጃ በተደራጀ መንገድ ለመስጠት ዛሬ ገበያን መጀመቸውን ተናግሯል።
በሀገሪቱ ከሚታየው የዋጋ ንረት ባሻገር በግል አንድ ጓደኛው ያጋጥመው የነበረ ችግርም ዘሩባቤል እንገለፀው ለዛሬ ገበያ ሀሳብ መወለድ ሌላው ምክንያት ነው።
«ኤርሚያስ ይባላል ጓደኛዬ ነው።ድሮ ስራ አግዘው ነበር። እሱ ወደ ሆሳዕና አካባቢ ስራ አለው።ኮንትራክተር ነው።በእርግጥ እዚህ ያለው እና እዚያ ያለ ዋጋ ይለያያል ግን እዚህ/አዲስ አበባ/ ሲጠይቅ ዋጋ ይይዙበታል።ስለዚህ እኛ እያጣራን እንልክለታለን።አጣርቶ ይገዛል። በዚህ ምክንያት ዋጋ እያጣራ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል «ፕላትፎርም» ቢኖርስ» የሚል ሃሳብ እንዳደረበት ገልጿል።
ይህ ዲጅታል መድረክ በዕየለቱ የዋጋ ክትትል በማድረግ ለሸማቾች የገበያ መረጃ በመስጠት ተጠቃሚዎች መግዛት በሚፈልጉት ነገር ላይ አቅማቸውን ያገናዘበ የግዥ ውሳኔ እንዲወስኑ ያግዛል።የዕየለቱን የገበያ ዋጋ ለማወቅም የሚያሰማሯቸው ወኪሎች ከተለያዩ የአዲስ አበባ የገበያ ቦታዎች ተዘዋውረው የቀን ዋጋ ይሰበስባሉ።የሚሰበስቡበት መንገድም በቴክኖሎጅ የታገዘ ነው።
በዚህ መልኩ የተሰበሰበውን ይህንን መረጃ ዛሬ ገበያ በተሰኘው ድረ ገፅ ላይ በመጫን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል።የተጠቃሚዎች ምዝገባም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት/8483/ አገልግሎት የስልክ ቁጥርን በመጠቀም የሚከናወን ነው።
የዛሬ ገበያ፤ አጀማመር
የዛሬ ገበያ፤ ሀሳብ የተጀመረው በእሱና በጓደኛው ናሆም ከፍያለው አማካኝነት በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ሲሆን ፤ለሁለት ዓመታት በሙከራ ላይ ከቆየ በኋላ በ2023 ዓ/ም መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ የሚከፈልባቸው የደንበኝነት ምዝገባዎችን ማቅረብ ጀምረዋል። ተጠቃሚዎች ዕለታዊ የሸቀጦች ዋጋ ማሻሻያዎችን እና የኋላ መረጃዎችን /እስከ አምስት ቀናት/ ድረስ በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ መረጃዎችን ይቀበላሉ።ከተዘረዘሩት ምርቶች መካከል ሽንኩርት፣ ፍራፍሬ፣ ፓስታ፣ ጤፍ፣ ሲሚንቶ፣ እና ቀለም ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በዓመት 3000 ሺህ ብር እየከፈሉ የሚጠቀሙ «ቢዝነስ ቱ ቢዝነስ»በተሰኘ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ደንበኞችም አሏቸው።እነዚህ ደንበኞች በነፃ አገልግሎት ከሚያገኙት የበለጠ በርከት ያሉ ቀናትን መረጃ ከዛሬ ገበያ ያገኛሉ። በዚህ ማዕቀፍ ያሉት ደንበኞች ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ሲሆኑ የገበያ መረጃዎችን ለኦዲት እንዲሁም ለጥናት እና ምርምር እንደሚያውሉት ገልጿል።
ዛሬ ገበያ ሲመሰረት በዕለታዊ የፍጆታ እቃዎች በተለይም ምግብ ነክ ነገሮች ላይ ያተኮረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የአገልግሎት አድማሱን ማስፋቱን ይገልፃል።
ለሻጭ እና ለገዥ የፈጠረው ዕድል
ከዌብ ሳይት በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ውጭ ላለው የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም የስልክ የጥሪ ማዕከል መዘጋጄቱን ገልጿል።
ዝሩባቤል እንደሚለው ከአዲሱ የምንዛሬ ተመን ወዲህ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ እና በዚህ ዲጅታል መድረክ የመጠቀም ፍላጎት ጨምሯል።በሌላ በኩል ነጋዴዎች የዋጋ መረጃ ከመስጠት ይልቅ «ዕቃው የለም» የሚል መልስ እንደሚያዘወትሩ አስተውሏል።በዚህም በመረጃ ማሰባሰብ ስራቸው ላይ መጠነኛ እክል እንደገጠማቸው አብራርቷል።
ሸማቾች ሻጮች እና አከፋፋዮች በዚህ ዲጅታል መድረክ ይጠቀማሉ የሚለው ዝሩባቤል፤ይህም ለሻጮች በርካታ ደንበኞችን ለማግኘት፤ ለሸማቾችም አማራጮችን አይቶ ለመግዛት ዕድል መፍጠሩን ያብራራል።
ናሆም ሙሉጌታ ዛሬ ገበያን ከሚጠቀሙ ደንበኞች መካከል ነው።እሱ እንደሚለው ዛሬ ገበያን በመጠቀሙ የንግድ ስራውን በወቅታዊ የገበያዋጋላይ ተመስርቶ ለማካሄድ ረድቶታል።«እኛ የምንሸጣቸው እቃዎች አብዛኞቹ እዚሁ የሚመረቱ ናቸው።እና ዋጋ ለማውጣት «ኮሚፒቴቲቭ»» ለመሆን በየጊዜው ዳታ ለማግኘት እንጠቀምበታለን።ከተመሳሳይ ፋብሪካ ስለሆነ ሁሉም ነጋዴ የሚገዛው ስለዚህ በየ ቀኑ ዋጋ ከፍ ዝቅ ሲል ለማወቅ «ኢንፎርሜሽኑ» ጠቃሚ ነው።»በማለት ገልጿል።
በሌሎች ሀገራት አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ
ዋና ስራ አስፈፃሚው ዘሩባቤል የህግ እና የአስተዳደር ባለሙያ እንዲሁም የዲጂታል ግብይት ልምድ ያለው ሲሆን፤ ተባባሪ መስራቹ ናኦል ከፍያለው ደግሞ የኤሌክትሪክ እና የኮምፒዩተር ምህንድስና ባለሙያ በመሆኑ በዋና የቴክኖሎጂ ባለሙያነት እየሰራ ይገኛል።ይህም ገበያን ከቴክኖሎጅ ጋር ለማጣመር ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ዛሬ ገበያ ፤ በአሁኑ ወቅት በድረ ገፅ እና በጥሪ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ መተግበሪያ በማበልፀግም ወደ ሙከራ ማስገባታቸውንም ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት የገበያ መረጃ የሚሰጥባቸውን የዕቃ አይነቶች የመጨመር ዕቅድ እንዳላቸው የሚገልፀው ዝሩባቤል፤ ለወደፊቱም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ በዋና ዋና የኢትዮጵያ ከተሞች እንዲሁም እንደ ዱባይ ፣ ታይላንድ እና ቻይናን በመሳሰሉ የኢትዮጵያ አስመጭዎች በሚያተኩሩባቸው የውጭ ሀገራት ላይ አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ አላቸው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረ እግዚአብሄር