1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለዓመታት ከህመሙ የታገለው አንጋፋ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሲታወስ

ሰኞ፣ ኅዳር 2 2017

በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ዜና አንባቢነት በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። ለረዥም ዓመታት የዶቼ ቬለ የኢየሩሳሌም ዘጋቢም ነበር። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጠንከር ያለ ህመም አጋጣመው ህክምናውን በትዕግሥትና በተስፋ ሲከታተል ቆይቷል። በህመም አልጋው ላይ ሆኖም ግን መጻፍ ትንታኔውን አላቆመም። እሑድ ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ,ም ግን ሞት አሸነፈው።

 አንጋፋ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን
አንጋፋ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንንምስል DW/Z. Mekonnen

አንጋፋው ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሲታወስ

This browser does not support the audio element.

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን የዜና አነባበብ ቅላጼው በብዙዎች ይወደዳል። እናት እና አባቶች በተለይ በቴሌቪዥን ቀርቦ ዜና ከማንበቡ አስቀድሞ በሚያቀርበው የአክብሮት ሰላምታው ትህትናውን እየገለጹ ልጆች ይመክሩበት ነበር።

አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ዜናነህ መኮንንበዶቼ ቬለም ለዓመታት ከኢየሩሳሌም ዘጋቢ ሆኖ በሙያው ቆይቷል። ጋዜጠኝነት ለዜናነህ ድንቅ ሙያ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት እሱው እንዳጫወተኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂው ገጣሚ መንግሥቱ ለማ «ዜናን ዜናነህ አነበበው ማለት» ዘመዳዊ ተሳቢ ነው እያሉ ለተማሪዎቻቸው ያነሱ እንደነበር የሰማው ሁል ጊዜ ፈገግ ያስብለዋል። የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ቀልቡን ይስበዋል፤ በእስራኤላውያን ብሔርተኝነት ይደመማል፤ ኢትዮጵያውያን በየሀገሩ ተበትነው ስለሀገራቸው መቆርቆር አለማቆማቸውን ቢያደንቅም፤ የተሻለ ነገር ለመሥራት ብዙ ይቀረናል የሚል፤ ተቆርቋሪ ዓይነት ሰው ነበር። ዛሬ ስለዜናነህ ነበር እያልን ነው የምናወራው ትናንት ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል። በህመም አልጋው ላይ ዓመታትን አሳልፏል። የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ግለታሪክ የመሰነድ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኘው ተወዳጅ ሚዲያ ባለቤት እንደተረዳነው በእራሱ በዜናነህ ትብብር የተዘጋጀው የሕይወት ታሪኩ አንጋፋው ጋዜጠኛ በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ መስከረም ወር ላይ አደይ አበባና አዲስ ዓመቱን ተከትሎ መወለዱን ያመለክታል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዜናነህ መኮንንፎቶ ከማኅደር ምስል DW/Z. Mekonnen

ዜናነህ የሦስት ሴት ልጆች አባት ነው፤ የልጅ ልጆችንም አይቷል። ሥርዓተ ቀብሩ ነገ ለረዥም ዓመታት በኖረባት እስራኤል ሀገር ቴልአቪቭ ከተማ ይፈጸማል። ለልጆቹ፤ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቹ፤ ጓደኞቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን። ነፍስ ይማር!

በሚያውቀው ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቃለመጠይቅ ለመስጠት ወደኋላ የማይለው ዜናነህ መኮንን በየጊዜው ከሚቀርብባቸው አንዱ ኅብር ራዲዮ የተሰኘው የድረገጽ የዜና ምንጭ ነው። የኅብር ራዲዮ ዜና አቅራቢ ጋዜጠኛ ሀብታሙ አሰፋን በአጭሩ ስለዜናነን ትውስታውንና አስተያየቱን እንዲሰጠን ጋብዘን አነጋግረነዋል። የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW