1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምህረት አምባ አገልግሎት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2015

የምህረት አምባ በህገወጥ መንገድ ወይም በሃሰተኛ ደላሎች ለሚጠቁ ኢትዮጵያውያን የቆመ ሃገር በቀል ማህበር ነው። ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 200 የሚሆኑ ህፃናት እና ወጣቶችን ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ለማዳን መቻሉን ይናገራል።

የምህረት አምባ አገልግሎት
የምህረት አምባ አገልግሎትምስል E. H. Mekasha

የምህረት አምባ አገልግሎት

This browser does not support the audio element.

ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ወይም ደላሎች ለስራ ውጭ ሀገር መሄድ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መስራት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንም ፈተና ናቸው። የምህረት አምባ በህገወጥ መንገድ ወይም በሃሰተኛ ደላሎች ኢትዮጵያውያን እንዳይጠቁ የሚሰራ ማህበር ነው። የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አደፍርስ /ኤዲ ሃብቴ መካሻ ይባላሉ ። አቶ አደፍርስ ሃብቴ  ከ10 በላይ የመፅሀፍ ትርጉም ወይም ወጥ ስራዎችን ሰርተዋል። ከእነዚህም መካከል እንደ «ኩራተኛው ድመት» እና «አፈርሳታ» የሚባሉት የትርጉም መፅሀፎች ይገኙበታል። አቶ አደፍርስ ስማቸውን የቀየሩት አሜሪካ ከገቡ በኋላ ነው። ይህም « ባህር ማዶ አሜሪካ ስገባ ይህ አደፍርስ የሚለው ስም አወዛጋቢ ጥያቄ የሚፈጥራቸው ሰዎች ስላሉ አንዳንዶችም ደፍረው የነፍጠኛ ስም ሲሉ ይሰማኛል። እኔ ድብልቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ። እና በጠማማ ፖለቲካ የተነሳ ያ ስም እንዳይቀጥል ፈለኩ።» ይላሉ።
አቶ ኤዲ ሃብቴ መካሻ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በተለያዩ የሰዎችን መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን በሚቀርፉ ስራዎች  ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልፀውልናል። ከእነዚህ ማህበራዊ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የምህረት አምባ አገልግሎት ነው። « እኔ እና ባለቤቴ ወይዘሮ ፋንታዬ ግርማ ብዙ ወገኖቻችንን ለመርዳት እንሞክራለን። እና በኛ እስቴት ያለ Love Justice የተባለው አለምአቀፍ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ተባባሪ ለማግኘት ሞክሮ ነበር እና አላገኘም። ከዛ እኛን እርዱኝ ስለን እኔ እና ባለቤቴ ኃላፊነቱን ተቀበልን» ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 200 የሚሆኑ ህፃናት እና ወጣቶችን ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ለማዳን መቻሉን አቶ ኤዲ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምህረት አምባ ስራ በተግባር ምን እንደሚመስል የገለፁልን አቶ አናፍ አመንሲሳ  የምህረት አምባ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ከተመሰረተ ስምንት ወር ገደማ የሆነው ማህበር ትኩረቱን ህፃናት እና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ላይ አድርጎ በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ሰዎች እንዳይታለሉ እየሰራ እንደሆነ ገልጸውልናል። ይህንንም የሚሰሩት Love Justice ከተባለው እና በትብብር አብሯቸው ከሚሰራው አለምአቀፍ ድርጅት ባገኙት ስልጠና ነው። « Love Justice ህገ ወጥ የሰዎችን ዝውውርን ለመከታተል የሚጠቀምበት አንድ ስልት አለ። እኛ ለምሳሌ ኢሚግሬሽን አካባቢ፣ መናኸሪያ አካባቢ ፣ የአዲስ አበባ መግቢያዎች ኬላ ላይ እንሰራለን።  እነዚህ ቦታዎች ላይ ሰዎችን በማጤን እና በማናገር ያ ሰው ህገ ወጥ አዘዋዋሪ ሌላው ደግሞ ተጠቂ መሆኑን አጣርተን ለፖሊስ አሳልፈን እንሰጣለን» 

አቶ  ኤዲ ሃብቴ መካሻ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ፋንታዬ ግርማ ምስል E. H. Mekasha

በውጭ ሀገራት ስራ ፈላጊዎች ዘንድ ያለው የተዛባ መረጃ እና የግንዛቤ እጥረት ትልቁ ፈተና እንደሆነ አቶ አደፍርስ ሃብቴ /ኤዲ ሃብቴ መካሻ ይናገራሉ።  « አረብ ሀገርም ሆነ ከዚህ አሜሪካ ሰዎች ሲሄዱ ብልጭልጭ ያለ ነገር አድርገው፣ አለባበሳቸውን አሳምረው ይሄዳሉ። እንዴት ግን ፈግተው እንደሚኖሩ አይናገሩም። እዛ ያሉ ወጣቶች የሚያዩት ከላይ ከላይ የሚታየውን ነው። የመረጃ አለማግነት አለ።»  በማለት አቶ ኤዲ ጉዳዩ ትኩረት እንደሚሻ ያሳስባሉ። 
አቶ አናፍ ይህንን ስራ ሲሰሩ በሀገር ውስጥ ስራ ፈላጊዎች ዘንድ ያለው የግንዛቤ እጥረት ደግሞ ምን እንደሚመስል የገጠማቸውን በምሳሌ ገልፀውልናል። « ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወዴት ለመሄድ እንደሚችሉ እንኳን አያውቁም። ደላላ ሲጠቀሙ ብዙ ወጪ ሳያወጡ መሄዱን ነው የሚያዩት። ያ ደላላ ግን ከህገ ወጥ አዘዋዋሪ ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል አያስቡም። እኛ ያገኘናቸው ሰዎች እንዲህም አለ እንዴ ብለው ሲደነግጡ ነው የምንመለከተው።» ሌላው ፈተና « የፀጥታ አካላት አለመተባበር ነው» ይላሉ አቶ አናፍ።  ይህም እሳቸው እንደሚሉት ከህገ ወጥ ዝውውሩ ተጠቃሚ የሆኑ  የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች በመኖራቸው ነው።  « እነዚህ ሰዎች መንግሥት ፈቅዶላቸው ሰርቷል ማለት ሳይሆን ስልጣንን ተገን አድርገው ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ሰዎች ወይም የመንግሥት ባለስልጣናት እንዳሉ ነው እዚህ ጋር የምንረዳው።»   በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ላይ በቂ ርምጃ አለመወሰዱ « ያንገበግበኛል» የሚሉት  አቶ አደፍርስ ወይም አቶ ኤዲ ብዙ ፖሊሶች እንደሚደለሉ እና ጉቦ እንደሚቀበሉ ይናገራሉ። « ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ከንቱ ተረት ወደ ገደል መጣል ይኖርበታል። የሚሾመው እኮ ህዝብን ሊያገለግል፣ በህዝብ ግብር ነው ። ግን ቅኖች ፖሊሶች በርቱ» ይላሉ።
ከአንድ ወር በፊት ኢትዮጵያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በተለይም ሴት ሠራተኞችን ወደ ውጭ አገራት ለስራ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ማስታወቋ ይታወሳል። በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም ስልጠናዎች ሲሰጥ ነበር።  ይህ ህገወጥ ስደትንና በሃሰተኛ ደላሎች ከመታለል እንደሚረዳ በመግለጽ አቶ አደፍርስ የመንግሥትን ርምጃ ሳያወድሱ አላለፉም። « ጅማሬው ጥሩ ነው። ሊበረታታ ይገባል። በጭፍን ሁሉንም ነገር ማውገዝ የለብንም።» የሚሉት የምህረት አምባ አገልግሎት ፕሬዚዳንት አቶ ኤዲ ኢትዮጵያ ያሉ የምህረት አምባ አገልግሎት ሰራተኞች ወደ አሳይታ፣ አሶሳ  እና የተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ድረስ እየተጓዙ ሰዎችን ከ ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እየታደጉም እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።  

ልደት አበበ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW