ዜጎች ከመንግስት የዘንድሮ ዓመታዊ ዕቅድ ምን ይጠብቃሉ?
ዓርብ፣ መስከረም 23 2018
የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት የመንግስትን አመታዊ እቅድ በሚቀጥለው ሰኞ ያቀርባሉ። የህዝብ ተወካዮች እና የሚንስትሮች ምክር ቤቶችም የሚከፈቱት በዚያው ቀን ነው። ለመሆኑ ሰዎች ከመንግስት ዓመታዊ ዕቅድ ምን ይጠብቃሉ?መንግሥት በዓመቱ የትኞቹን ተግባራት ቢከውን ይበጃል? ሰኞ የሁለቱን ምክር ቤቶች ሥራ የሚያስጀምሩት ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ንግግራቸው ምን ላይ ያተኩር ይሆን?
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሰኞ መስከረም 26 ቀን ይከፈታል።በዚህም የሀገሪቱ ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሁለቱን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን የሚከፍቱ ሲሆን መንግሥት በዓመቱ የሚያከናውናቸውን ዐበይት እቅዶችንና አቅጣጫዎችን ይፋ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ያልተፈታ የግጭት ቀውስ ውስጥ፣ ጉልህ የሰላም እጦት እንዲሁም መፈናቀል፣ እገታ እና መሠል ዕድገት ጎታች በሆኑ ችግሮች ውስጥ አልፋለች። የኑሮ ውድነቱም በተጨባጭ የዜጎችን ሕይወት እየፈተነ ቀጥሏል።በዚያው መጠን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ ተጠናቆ መመረቅ፣ ሰሞኑን እየተቀመጡ ያሉ ግዙፍ የልማት መሠረተ ልማቶች ተስፋ የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል።ኢትዮጵያ በዚህ የ 2018 ዓመት የሀገራዊ ምክክር የሥራ ውጤትን ትጠብቃለች፣ ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫንም ታከናውናለች ተብሎ ይጠበቃል። ይህን ለማድረግ አመቺ የፀጥታ ኹኔታ የለም የሚሉ የፖለቲካ ማሕበር ስብስቦች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ።ለመሆኑርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በንግግራቸው ምን ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ? የኢትዮጵያ መንግሥትስ በዓመቱ ምን ምን መሠረታዊ ተግባራትን ቢከውን ይበጃል? የተወሰኑ ሰዎችን አስተያየት ጠይቀናል።
ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ የመንግሥት ሥራ ቢሆን ይሻሉ
"ዋናው ሰላም ነው። በሰላም ላይ ቢሠሩ ጥሩ ይመስለኛል። ሰላም ነው ዋናው። ምክንያቱም ሰላም ከሌለ እኔ ጋር ባይደርስም ሌላው ጋር በሚደርሰው ነገር እረበሻለሁ። ስለዚህ ሰላም ላይ ቢሠሩ። የሀገር ዕድገትም በርግጥ ያስፈልጋል። ግን ሰላም ከሌለ ደግሞ ዕድገት ምንም ማለት አይደለም።"
"ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላም ነው። ያው ሰላም ስንል ደግሞ መንግሥት ብቻውን ሊሠራው አይችልም። ሕዝብም እርስ በርስ ቅንነት፣ ሁሉም እንደ ወንድም እንደ እህት፣ እንደ አባት እንደ ልጅ ተያይቶ የእኛ አመለካከት ወደ ቅንነት ሊመለስ ካልቻለ መንግሥት ብቻውን ሊሠራው የሚችለው ሥራ ይኖራል ብየ አልገምትም። እና መጸለይ ነው በየግላችን፤ እና ከአንተ የሚጠበቀውን ማድረግ ነው።"ብለዋል።"በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ነው ዋናው የናፈቀን አንደኛው። ሁለተኛው የኑሮ ኹኔታ። የዋጋ ግሽበቱን በተቻለ መጠን ቢያረግበው [መንግሥት] ሰው በሰላም መኖር ይችላል። ሁለቱ ነገሮች ከተስተካከሉ እዚህች ሀገር ላይ ሌሎች የሚስተካከሉ ነገሮች ይመስለኛል።"ነው ያሉት።"መንግሥት ሰላም ላይ [ቢሠራ]። ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ብዙ መሥራት የምትችለውን ነገር አንደኛ እንዳትሠራ ያደርግኻል፣ ሁለተኛ ደግሞ የሠራኸውንም ነገር ያበላሽብሃል። የሰው ሕይወት ደግሞ ከሁሉ ነገር በላይ ነው። ለሰው ሕይወት ትልቅ ትርጉም መስጠት አለበት።"ብለዋል።
ቢደረጉ ይበጃሉ የሚባሉ ሌሎች ጉዳዮች
"በዓለም የመጣ ነው - የኑሮ ውድነት። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተጋኗል። በተወሰኑ በሸማቾች [ማህበራትና አቅራቢዎች] ማኅበረሰቡ ብዙም ባይባል ትንሽ ቅናሽ ያለው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ይታያል። ግን በቂ አይደለም። እንደዚያም ሆኖ ሳይበላ የሚያድር ኢትዮጵያዊ ስላለ በዚያው ልክ ቢስፋፋ። የሚሉትን ደግሞ [ርእሠ ብሔሩ] እንሰማለን።"
"ከዚህ ከዓባይ [ግድቡ] ጋር በተነሳ ሲደራደሩ አይተናቸዋል [ርእሠ ብሔር ታዬ]። ጥሩ ሰው ይመስሉኛል። ጥሩ አመለካከት ያላቸው ይመስለኛል። ግን እሳቸው ያወራሉ እንጂ የሚተገብሩት ሌሎች ናቸው። አንዱ ችግሩ የሚፈጠረው ምንድን ነው - ከላይ ያለው ያወራል ታች ያለው ነገሮችን እስካልፈጸመ ድረስ ነገሮች እንደተበላሹ ነው የሚቀጥሉት።"ብለዋል።
"ሁሉ ነገር በውይይት፣ በንግግር ቢፈታ። ከጎረቤት ሀገርም ጋር ከሌላውም እንደዚያ ቢሆን ጥሩ ነው።""ሰላም የሚሠራው በሰላማዊ መልኩ ነው። ታግሶ፣ ችሎ የሚጠይቁትን ጥያቄ መልሶ፤ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማድረግ አለበት መንግሥት። ያ ሲሆን የመነጋገር ባሕል ከዳበረ ሰዎች መሣሪያ ለምን ያነሳሉ? ሁሉም ሰው እንደ ሀገሩ ከተቆጠረ፣ ተናግሮ መሰማት ከተቻለ መሣሪያ አያነሳም። መሣሪያ ካላነሳ ደግሞ ሰላም ነው።"ብለዋል።
ርዕሠ ብሔሮች በቀደሙት ዓመታት ምን ብለው ነበር?
የኢ. ፌ.ዲ.ሪ የቀድሞ ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴበተከታታይ ዓመታት አድርገዋቸው በነበሩ የሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግሮቻቸው ሰላም፣ ንግግር፣ ድርድር፣ የመንግሥት ዐበይት የሥራ እቅዶች መሆናቸውን ሲገልፁ ነበር። "የሀገርን ህልውና እና የሕዝባችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደዚሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ችግሮች በብሔራዊ መግባባት ሊፈቱ ይገባል" የሚለው የ2014 ዓ.ም ንግግራቸው ይጠቀሳል።
"ብሔራዊ መግባባት ይፈጠር ዘንድም ታጋሽነት፣ መተማመን፣ መመካከር፣ ሕብረትና አንድነት እና የክርክር ባህሎችን ማዳበር ይኖርብናል" ሲሉም "በአመፅ እና በጠመንጃ ትግል አልያም ንፁሃንን በማሸበር የሚገኝ ሥልጣን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የማይፈጠሩ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፣ስልጣን ሰጪውም ሆና ነሺው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው" በማለት ፖለቲከኞች ሰላማዊ የፉክክር መድረክን ብቻ እንዲመርጡ ጠይቀው ነበር።
የቀድሞዋ ርእሠ ብሔር በ2016 የመጨረሻው የሥልጣን ዓመታቸው "ጦርነት አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም" በማለት "ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በጥበብ፣ በአርበኝነት፣ በሥልጣኔ ለዓለም ያበረከተችው መልካም ሥራ ባለቤት የመሆኗን ያህል አሁን ላይ "ራሳችንን በሚያቀጭጭ እና ራሳችንን በራሳችን በሚያወድም" ሁኔታ ላይ እንገኛለን ማለታቸው ይታወሳል።ባለፈው ዓመት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ርእሠ ብሔር ሆነው የተሾሙት ታዬ አጽቀ ሥላዴ የዚያኑ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ጉባኤን ሲከፍቱ "የምትሻገር ሀገር በማይሻገር ሀሳብ ስትናጥ ቆይታለች" ብለው ነበር። አክለውም የሚታረም እና የሚታረቅ የፖለቲካ ልዩነት እንደማይታረምና እንደማይታረቅ ተደርጎ በመሠራቱ ሀገር በማይጠራ የፖለቲካ ሳንካ እንድትንገላታ ተገዳለች" በማለት በመንግሥት በኩል "የሰላም በሮች ሁሉ የተከፈቱ ናቸው" ሲሉ ችግሮች በሰላማዊ አማራጭ ብቻ መፈታት እንደሚገባቸው አሳስበው ነበር።
ዛሬስ ? የፌታችን ሰኞ ባለፈው ዓመት ከተናገሩት ምን ያህሉ ተተገበረ? የትኛውስ ተሳካ? የዚህ ዓመት የመንግሥት ሥራ ትኩረትስ ምን ይሆን የሚለው ከንግግራቸው ይታወቃል።
ሰለሞን ሙጨ
ነጋሽ መሀመድ
ፀሐይ ጫኔ