1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: በእግሯ የምትፅፈው ተማሪ

05:53

This browser does not support the video element.

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2015

"አካል ጉዳተኝነት ተምሮ ህልምን ከማሳካት ሊያቆም አይገባም" የሚለው እሳቤ በተፈጥሮ ሁለት እጆቿን ያጣችው ተማሪ ኬርያ ጀማል ነው። እጆችዋን ብታጣም ከትምህርት ገበታ ግን ያልቀረችውና ጠንካራ ስብዕናን የተላበሰችው ተማሪ ኬርያ ዘንድሮ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ናት።

ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረገችው ኬርያ ትውልድ እና እድገቷ በድሬደዋ አስተዳደር ስር ባለ የገጠር ቀበሌ ሲሆን በአሁን ሰዓት መስተዳድሩ ለገጠር ሴት ተማሪዎች በከተማዋ ባዘጋጀው መኖርያ ውስጥ ሆና ትምህርቷን በመማር ላይ ትገኛለች። 

የአካል ጉዳት ከአቻዎቿ ነጥሎ ቤት እንዳያስቀራት ወላጆቿ በተለይም እናቷ ይዘው በዚያው በገጠር በሚገኝ ትምህርት ቤት መደበኛ ትምህርት በወቅቱ አስጀምረዋታል። 
የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት የተከታተለችበት የገጠር ት/ቤት እሷ እንደምትለው "ምቹ " ባይሆንም መምህራን እና ጓደኞቿ በሚያደርጉላት ድጋፍ ትምህርቷን ገፍታበታለች። 

የድሬደዋ አስተዳደር የገጠር ሴት ተማሪዎችን ጥረት ለመደገፍ በከተማ ወደአቋቋመው መኖርያ ወይም ሆስቴል የመግባት እድል ያገኘችው ኬርያ ይሄ ድጋፍ "ለአኗኗርም ሆነ ለመማር ምቹ ሆኔታን ፈጥሮልኛል" ብላለች። ይሄ ብቻ ሳይሆን አሁን ትምህርቷን እየተከታተለች ያለችበት የማርያም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ለመማር የሚያስችላትን ልዩ መቀመጫ በማዘጋጀት ያደረጉላት ድጋፍ ትልቅ እንደሆን ታነሳለች።


ሁለቱም እጆቿ ባይኖሩ ባዳበረችው ልምድ እግሮቿን ለመፃፍያነት ተጠቅማ ፤ በቅርብ ያሉ ጓደኞቿ በሚያደርጉላት እገዛ የመማርያ ቁሳቁሶቿን በመያዝ ትምህርቷን እየገፋች ነው።
" እንዲህ ሆኛለሁ ብዬ ተስፋ ቆርጬ  ትምህርቴን አልተውም" የምትለው ታታሪና በብዙ መልኩ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ጠንካራ ስብዕናን የተላበሰችው ኬሪያ አካል ጉዳተኛ ለሆኑ አቻዎቿም የእሷኑ ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ነው መልዕክቷ።

በቅርቡ የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኬሪያን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎችን ወደ አዲስ አበባ ወስዶ ነበር ። ከዝግጅታችን ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለጉዞው ዓላማ የጠየቅናት ኬርያ " ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ እዚያም የሄድኩት ለዚሁ ነው ፤ ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን" ስትል ምላሽ  ሰጥታናለች።

ምቹ ካልሆነው የገጠር ትምህርት ቤት ጀምሮ በትምህርቷ ገፍታ ዛሬ ላለችበት በመድረሷ ጓደኞቿን ፣ መምህራኖቿን እና ወላጆቿን በፅኑ የምታመሰግነው ይህች ብርቱ ተማሪ በትምህርቷ ውጤታማ ሆና "መሪ" መሆን እንደምትፈልግ ገልፃልናለች።

ዘገባ: ሊዲያ መለስ
ቪዲዮ: መሳይ ተክሉ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW