1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች፤ "አጎቴ ነው የደፈረኝ"

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 2014

በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር ግቢ ውስጥ አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እያገገሙበት ይገኛሉ ፡፡ በተለይም የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ማረፊያና ማገገሚያ ማዕከሉ ከመጡት መካከል አብዛኞቹ በታዳጊነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

Äthiopien Lishan Dagne
ምስል S. Wegayehu/DW

ውይይት፤ "አጎቴ ነው የደፈረኝ"

This browser does not support the audio element.

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ታዳጊዎች በዚህ ሥፍራ የስፖርት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ፣የሕክምናና የሥነ ልቦና ድጋፍም ይቀርብላቸዋል፡፡ ጥቃቱን ባደረሱባቸው ግለሰቦች ላይም በማህበሩ አማካኝነት ክስ በመመሥረት በሕግ እንዲቀጡ ይደረጋል፡፡ በዛሬው የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅታችንም በዚሁ የማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ከሚገኙት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሁለት ታዳጊዎች ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

ታዳጊዎቹ  ለዚህ ዘገባ ሲባል ሥማቸው የተቀየረው ታዳጊ ፊያሜታ ገረመው እና ቢታኒያ ደጀኔ ናቸው ፡፡ ፊያሜታ ገረመው የ9ኛ ክፍል ተማሪና የ15 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ቢታንያ ደጀኔ ደግሞ የ4ኛ ክፍል ተማሪና የ13 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ፊያሜታ ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ የመጣችው አጎቷ ባደረሰባት የአስገድዶ መደፈር የተነሳ ጉዳዩን የነገረችው ሰው ወደ ማዕከሉ እንዳመጣት ትናገራለች  ፡፡ በተመሳሳይ ታዳጊ ቢታንያ ደጀኔም  እንደ ፊያሜታ ሁሉ ወደ ማዕከሉ የመጣችው በጎረቤታችው ሰው በተፈፀመባት የአስገድዶ መደፈር ምክንያት መሆኑን ገልጻለች፡፡

ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ቢታኒያና እና ፊያሜታ በተፈፀመባቸው የአስገድዶ መደፈር ለጊዜው አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ቢሆንም እንዲህ አይነቱን ድርጊት ግን በዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ በተለይም የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ሲያጋጥም በተለይ እንደዋነኛ ችግር የሚታየው ተስፋ የመቁረጥ ሥሜት መሆኑን የምትናገረው ፊያሜታ ክስተቱን የሕይወት ፍጻሜ አድርጎ መመልከት አይገባም ትላለች፡፡አያይዛም ታዳጊ ሴቶች ራሳቸውን ከአስገድዶ መደፈር ጥቃት ለመጠበቅ የጾታዊ ትንኮሳ ሙከራ የሚያደርጉባቸው ሰዎች ሲያጋጥማቸው በቶሎ ለቤተሰብ ወይም ለሚቀርቡት ሰው ሊጠቁሙ ይገባል ብላለች ፡፡

ፊያሜታም ሆነች ቢታንያ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ባገኙት የሕክምና ፣ የሥነልቦና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ትምህርታቸውንም መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱባቸው ግለሰቦች የሀዋሳ የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር የህግ ባለሙያ አማካኝነት በእሥር ተቀጥተዋል  ብለዋል፡፡

ፊያሜታና ቢታንያ አሁን አጋጥሞአቸው የነበረውን ችግር ከመሻገራቸው በተጨማሪ በቀጣይ ቢታኒያ የኮሚፒዩተር ሳይንስ ፊያሜታ ደግሞ የህክምና ዶክተር የመሆን ፍላጎት እንዳላቸውና ለዚህም እንደሚጥሩ  ገልፀዋል፡፡

ሊሻን ዳኜ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW