1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የሱስ ተጋላጭ የነበረችው ወጣት

ዓርብ፣ መስከረም 27 2015

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው የአሥራ ስምንት ዓመቷ ሐና ታደለ ላለፉት ሦስት ዓመታት በጎዳና ላይ መኖሯን ትናገራለች ፡፡ ሐና በጎዳና ሕይወት ውስጥ ያለ ሰው ለፆታዊ ጥቃት የመጋለጥና በሱስ የመያዝ እድሉ ሠፊ ነው ትላለች ፡፡

Äthiopien Center of concern
ምስል S. Wegayehu/DW

የሱስ ተጋላጭ የነበረችው ሃና

This browser does not support the audio element.

የወላጅ ቤተሰቦቼን ታሪክ ብዙም አላውቅም ያሳደገችኝ አክስቴ ናት ምትለው ሐና ‹‹ አክስቴ በጡት ካንሰር ታማ መሞቷን ተከትሎ የሚረዳኝ በመጣቴ ችግር ላይ ወደኩ ፡፡ ሥራ ለመቀጠር ብሞክር እንኳን ተያዥ የሚሆነኝ ሰው ላገኝ አልቻልኩም ፡፡ ያለኝ ምርጫ ወደ ጎዳና መውጣት ብቻ በመሆኑ ኑሮዬ ከዚያው ሆነ ›› በማለት ወደ ጎዳና የወጣችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡

በሦስት ዓመት የጎዳና ሕይወቷ ጾታዊ ትንኮሳዎች ይደርሱባት እንደነበር የምትናገረው ሐና ‹‹ በጎዳና በነበርኩበት ጊዜ በተለይ ለጫትና ለአልኮል መጠጥ ሱስ ተጋልጬ ቆይቻለሁ ምክንያቱም በጎዳና ላይ አብዛኞቹ ሱሶች የሚጀመሩት እንደቀልድ ነው ፡፡ ለብርድ ማጥፊያ በሚል አኔን ጨምሮ በወጣት ዕድሜ ላይ ያለነው ጫትና መጠጥ ታዳጊዎች ደግሞ ማስቲች ( ቤንዚን ማሽተት ) ይወስዳሉ ፡፡ ይህን ለሟሟላት ደግሞ የሰው ንብረት እስከመስረቅ የሚደረስበት ሁኔታም ነበር ›› ትላለች ፡፡

ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ማዕከል ውስጥ ሐናን ጨምሮ ለጎዳና ኑሮና ለሱስ የተጋለጡ ታዳጊዎችና ወጣቶች የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተሰጣቸው ይገኛልምስል S. Wegayehu/DW

እነኝህን የሕይወት ፈተናዎች ስትጋፈጥ የኖረችው ሐና ታዲያ በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የተጋላጭ ሕጻናት ማብቂያና እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ከገባች በኋላ ሁኔታዎች እየተቀየሩ መምጣቸውን ትናገራለች ፡፡ ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት በተቋቋመው በዚህ ማዕከል ውስጥ ሐናን ጨምሮ ለጎዳና ኑሮና ለሱስ የተጋለጡ ታዳጊዎችና ወጣቶች የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተሰጣቸው ይገኛል ፡፡ በተጨማሪም የግል ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሏቸው የገላ መታጠቢያ ክፍሎችም ተገንብተውላቸዋል ፡፡  የቴኒስ መጫወቻና የቴሌቪዥን መመልክቻ አዳራሾችም አሏቸው፡፡

በማዕከሉ የሥነልቦና ህክምና ስትከታተል የቆየችው ሐና አሁንም በችግር ምክንያት ተመልሳ ወደ ጎዳና እንዳትወጣ በዚሁ ማዕከል አማካኝነት ቋሚ ሕይወቷን ለመምራት የሚያስችላት ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ድጋፍ የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪ ለመሆን የሚያበቃትን ሥልጠና እየወሰደች እንደምትገኝ የምትናገረው ሐና ‹‹ ሴቶች ጠንከርን እራሳችንን መቀየር እንችላለን ›› ትላለች፡፡ ወጣቶች ሲጀመር ለሱስ የሚያጋልጡ ነገሮችን በምንም መልኩ መጀመር እንደሌለባቸው የምትመክረው ሐና ‹‹ በሱስ ውስጥ ገብተው ከተገኙም ከዚህ መጥፎ ሕይወት መውጣት ይችላሉ ፡፡ እኔ ይሀንን በራሴ አረጋግጫለሁ ፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን ሱሱ ትዝ እያለ ያስቸግረኝ ነበር ፡፡ ነገር ግን ወደዚህ ማዕከል በመምጣትና ገላዬን በመታጠብ ሰውነቴን አያቀዘቀዝኩ አሳልፋለሁ ፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የቤት ውስጥ ጌሞችን በመጫወትና ትምህርታዊ የቴሌቪዥን ዝግጅቶችን እከታተላለው ፡፡ ዛሬ ላይ ከነበሩብኝ ሱሶች በመላቀቄ ነጻ የሆነ ሥሜት ይሰማኛል ›› ብላለች ፡፡

የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪ ለመሆን የሚያበቃትን ሥልጠና እየወሰደች የምትናገረው ሐና ምስል S. Wegayehu/DW

አሁን ላይ በራስ የመተማመን ሥሜቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ የምትናገረው ሐና በቀጣይ ከባጃጅ አሽከርካሪነት ባለፈ የበጎ አድራጎት ድርጅት በመክፈት በሱስ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ለመረዳት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡

አቶ ተስፋ አርጃ የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸውምስል S. Wegayehu/DW

አቶ ተስፋ አርጃ ሐና ታደለን ለመሳሰሉ ወጣቶች ከጎዳና ሕይወትና ከሱስ ለማላቀቅ በሚሠራው ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ድርጅት ውስጥ የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸው፡፡ አቶ ተስፋ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ የመሠረቱ አዳጊዎችና መጣቶች ከሱስ በተጨማሪ በወንጀል የሚሠማሩ ሰዎች ጭምር እንደሚጠቀሙባቸው ይናገራሉ ፡፡ አንዳንዴ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ሞተው ከጎዳና ላይ ሬሳ የሚያነሱበት አጋጣሚ መኖሩን የሚጠቅሱት አቶ ተስፋ ‹‹ መንግሥት ፣ የረድኤት ድርጅቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች  በቅንጅት ከሠራን በጎዳና ላይ የሚገኙ ታዳጊና ወጣቶችን ወደ ጤናማ ሕይወት መመለስ እንችላለን ፡፡ ለዚህም የሐና እና የሌሎች ወጣቶች ሕይወት እንደተሞክሮ ሊታይ የሚችል ነው ›› ብለዋል፡፡

ሊሻን ዳኜ / ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW