1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች : የሴት ልጅ አለባበስ ከፆታዊ ጥቃት ያድናል?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 18 2016

የሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታ ለተለያዩ አይነት ጾታዊ ትንኮሳዎች ብሎም ለጾታዊ ጥቃት ለመዳረግ ገፊው ምክኒያት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የሴት ልጅ አለባበስ ለጾታዊ ጥቃት ሊዳርጋት አይገባም፤ መንስኤውም ሆኖ ሊቀርብ አይችልም የሚሉ አሉ።

ቤቴል ገረመው ፤ ሊዲያ ሰለሞን ፤ ቤቴል አብርሃም ፤ ቤዛዊት ተስፋዬ እና አወያይ ሱመያ ሳሙኤል
ቤቴል ገረመው ፤ ሊዲያ ሰለሞን ፤ ቤቴል አብርሃም ፤ ቤዛዊት ተስፋዬ እና አወያይ ሱመያ ሳሙኤልምስል S. Getu/DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች : የሴት ልጅ አለባበስ ከፆታዊ ጥቃት ያድናል?

This browser does not support the audio element.

ቤቴል ገረመው እና ሊዲያ ሰለሞን የተባሉ ወጣት-ታዳጊዎች የሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታ ለተለያዩ አይነት ጾታዊ ትንኮሳዎች ብሎም ለጾታዊ ጥቃት ለመዳረግ ገፊው ምክኒያት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው የሚል ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል፡፡

ቤቴል አብርሃም እና ቤዛዊት ተስፋዬ የተባሉ ታዳጊ-ወጣቶች ደግሞ የሴት ልጅ አለባበስ ለጾታዊ ጥቃት ሊዳርጋት አይገባም፤ መንስኤውም ሆኖ ሊቀርብ አይችልም ችግሩ ከዚያ ባሻገር ነው ይላሉ፡፡

«የሴት ልጅ አለባበስ ለጾታዊ ጥቃቶች ገፊው ምክኒያት ነው»

የሴት ልጅ አለባበስ ለጾታዊ ጥቃቶች ገፊው ምክኒያት ነው የሚል ሃሳብ ይዘው የቀረቡት ሁለቱ ወጣቶች በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የአለባበስ ትርጉምና እምቅ አቅሙን በማብራራት ነው ክርክራቸውን የጀመሩት፡፡ “ለደስታ ነጭ ልብስ ለሀዘን ደግሞ ጥቁር እንደምለበስ ሁሉ የተገላለጠ ወይም በማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አለባበስ መከተል በራሱ የሚያስተላልፈው መልእክት አለው” ያሉት እነዚህ ወጣቶች የሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታ እራሱን ችሎ የሚያስተላልፈው መልእክት ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የሴቶች የተገላለጠ (ማለትም ገላን የሚያሳይ) ልብስ መልበስ ትኩረትን በመሳብ ሴት ልጅን ትኩረት እንድትስብ በማድረግ ለተለያዩ ትንኮሳዎች ሊያጋልጣት ይችላል ብለዋል፡፡ ይህም ሴት ልጆችን ከአለባበሳቸው ሁኔታ የተነሳ ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ሊዳርጋቸው እንደሚችል አብይ ማሳያ አድርገው ሞግተዋል፡፡

«ሴት ልጅ ምንም ለበሰች ምን ጾታዊ ጥቃት ሊደርስባት አይገባም»

የሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታ ፈጽሞ ለጾታዊ ጥቃት ሊዳርጋት አይገባውም በሚል የሞገቱ ወጣት ሴቶች ደግሞ የሰው ልጅ ያሻውን የማድረግ መሰረታዊ መብትን በማጣቀሻነት አንስተው ሞግተዋል፡፡ “አንድ ሰው የፈለገውን/ችውን ነገር ለማድረግ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው/አላት” ያሉት ወጣቶቹ ማንኛውም ሰው እስከተመቸውና ነጻነት እስከሰጠው የፈለገውን/ችውን የመልመበስ መብት አለው/አላት ብለዋል፡፡ ይህም በተለይም ሴት ልጅን ለጾታዊ ጥቃት ሊዳርጋት አይገባም ያሉት ወጣት ቤቴል እና ቤዛዊት ጾታዊ ጥቃትን ለመታገል በመሰረታዊነት የሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ መስራቱ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሴት ልጅ ምንም ለበሰች ምን ጾታዊ ጥቃት ሊደርስባት አይገባም ነው ያሉት፡፡ ወጣቶቹ ከትንሽ እድሜ እስከ አዛውንት እድሜ ላይ ሆነው በተለያዩ ጊዜያት የሚደፈሩትን ሴቶች እውነታ በምሳሌነት አቅርበው የአለባበስ ሁኔታ ለጥቃት ትልቁ መንስኤ ሆኖ ሊቀርብ አይገባል በማለት ሀሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት ታቅዶ እንጂ ድንገት የሚፈጠር ክስተትም አይደለም ሲሉ ሀሳባቸውን አክለዋል፡፡ “አንዲት ለጥቃት የተዳረገች ልጅ ቁምጣም ይሁን ጂንስ ለብሳ ብትወጣ ለጥቃት ሊዳርጋት የሚችለው ሰውየው አዕምሮ ውስጥ ያለው እውነታ ነው፡፡ ምክኒያቱም ትንኮሳውን ፈልጎና አቅዶ ስለሆነ የሚያደርገው የልጅቷ የተሸፋፈነ ልብስ ማድረግ ጥቃቱን ሊያስቆመው አይችልም” በማለትም ሌላ ምሳሌ አክለዋል፡፡ እናም ይላሉ ወጣቶቹ፤ አንድ ሰው የፈለገው/ችውን የመልበስ መብት እስካለው/ላት ድረስ በዚህ ጾታዊ ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ መስጋት ያልተገባ ነገር ነው፡፡

ቤቴል ገረመው ፤ ሊዲያ ሰለሞን ፤ ቤቴል አብርሃም ፤ ቤዛዊት ተስፋዬ እና አወያይ ሱመያ ሳሙኤልምስል S. Getu/DW

አለባበስ የተቃራኒ ጾታን ፍላጎት የማነሳሳት ኃይሉ ጉልህ ነው?

አይሆንም አለባበስ የተቃራኒ ጾታን ፍላጎት የማነሳሳት ኃይሉ ጉልህ ነው ያሉት ወጣቶች በፊናቸው፤ ህብረተሰቡ ላይ መስራት ተገቢ ነው የሚለውን ሀሳብ ቢቀበሉም የአለባበስ ሁኔታ ለጾታዊ ጥቃት ፈጽሞ ተጽእኖ የለውም በሚለው ሃሳብ አይስማሙም፡፡ የአለባበስ ሁኔታ በማህበረሰብ ዘንድ እራሱን የቻለ አዎንታዊና አሉታዊ አንድምታ እንዳለው በማመልከትም “የሴት ልጅ ጥቃትን በአለባበስ ሁኔታ ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ “የራስን ቤት ከሌባ ለመከላከል በር ቆልፎ መውጣት ግድ እንደሚል ሁሉ ራስን ከጾታዊ ጥቃት ለመከላከል በአለባበሳችን ቁጥብ መሆን ይገባል” የምትለው ወጣት ቤቴል ገረመው ሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታዋን በማስተካከል የጾታዊ ጥቃት ተጋላጭነቷን መቀነስ ትችላለች ነው የምትለው፡፡

“ሴት ልጅ እህት፣ እናትና ሚስት በመሆን በማህበረሰብ ውስጥ የጎላ ሚና እያላት ይህን ባደርግ ያን ባደርግ ለጥቃት ልዳረግ እችላለሁ የሚል ስጋት ላይ ፈጽሞ መውደቅ የለባትም” የምትለው ወጣት ቤተል አብርሃም የማህበረሰብ አካል የሆነች ሴት ልጅ የፈለገችውን ከመልበሷ የተነሳ ለጥቃት መዳረጓ ሊሆን ያልተገባ ነው ትላለች፡፡ በመሆኑም ማህበረሰቡ በራሱ ለሴት ልጅ መሰል መብት መከበር የበኩሉን ሚና ለመወጣት አብዝቶ መስራት እንዳለበትም ትመክራለች፡፡ “ሴት ልጅ የምትደፈረው በለበሰችው አለባበስ ሳይሆን የደፋሪው አእምሮ ውስጥ በተቀመጠ አስተሳሰብ ነው” በማለትም ትሞግታለች፡፡ ይህንኑን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት የሰጠችው ወጣት ቤዛዊት ተስፋዬ በበኩሏ ምንም እንኳ ማህበረሰቡ በአለባበስ ዙሪያ በአእምሮው የሳለው ነገር ብኖርም፤ ከጾታዊ ጥቃት ጋር የሴት ልጅ አለባበስን ማገናኘት ዋናው ምክኒያት እንዲዘነጋ ያደርጋል ባይ ናት፡፡ “ምንም ትልበስ ምንም ያለ ፈቃዷ እጁን ሊያነሳባት አይገባም” የምትለው ቤዛዊት አለባበስን እንደ የሴቶች ጥቃት መንስኤ ማቅረብ ጥቃቱ እንኳን ደረሰባት ብሎ ከመደገፍ አይተናነስም በማለትም ሀሳቡን ኮንኗለቸች፡፡ ወጣት ቤዛዊት “የሴት ልጅ ሰውነት እቃ አይደለም፡፡ የራሷ ነው፡፡ እሷ በተመቻት መንገድ መልበስ፤ በተሰማት መንገድ ሰውነቷ ላይ የመጠቀም መብት አላት፡፡ ሌላውን ወገን ሊገፋፋ ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ የማብራራት ግዴታም ልኖራት አይገባም፡፡ ሰብዓዊ መብቷን ተጠቅማ እራሷን የመግለጽ መብት አላት” በማለትም ሞግታለች፡፡ እናም መቅደም ያለበት ምን ለብሳ! ሳይሆን ለጥቃት መዳረግ የለባትም በሚለው ዋናው ጽንሰ ሃሳብ ላይ ነው ትላለች፡፡

ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ዘመቻ በኢትዮጵያ

የሴት ልጅ የአለባበስ ሁኔታ ለጥቃት ሊዳርጋት ይችላል በሚል ሃሳብ የተሟገቱ ወጣቶች ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ አለባበስ ማስተካከል አንዱ ትንኮሳን የመከላከያ መንገድ እንጂ ፈጽሞ ትንኮሳን መከላከያ መንገድ አይደለም ነው ያሉት፡፡

የሴት ልጅ ጥቃት ፈጽሞ ከአለባበስ ሁኔታ ጋር ሊያያዝ አይገባም ያሉ ወጣቶች በበኩላቸው፤ ማህበረሰቡ አለባበስን ፈጽሞ እንደ ጥቃት መንስኤ ከማንሳት መቆጠብ አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ማህበረሰቡ ሰዎችን መቅረጽ ላይ ሲሰራ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡ እናም ሴት ልጅ ለጥቃት የተዳረገችው በለበሰችው የአለባበስ ሁኔታ ነው በሚል የሚደርስ ጥቃት ለድርድር የሚቀርብ ሳይሆን ምህረት የለሽ ሊሆን ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አወያይ፡ ሱመያ ሳሙኤል

አዘጋጅ፤ ሥዩም ጌቱ

 

 

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: አልባሳቱና ታሪኮቻቸው

03:45

This browser does not support the video element.

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW