1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የሜክአፕ ጥቅም እና ጉዳቱ

ዓርብ፣ ጥር 15 2018

ቃል ኪዳን ማንከልክሎት እና ሲፈን አንተነህ በሀዋሳ ከተማ የሜክፕ አርት ሥልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ናቸው ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑት አቤጊያ ያሬድ እና ማይገነት ጠለለ በአንጻሩ ሜክአፕ አሥፈላጊ አይደለም የሚል አምነት እንዳላቸው ይናገራሉ ፡፡ ወጣቶች ሥለሜክአፕ አርት ምን ይላሉ?

በሀዋሳ ከተማ የሜክፕ አርት ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ 2 ወጣቶችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 2 ተማሪዎች ቁጭ ብለው ሲወያዩ
በሀዋሳ ከተማ የሜክፕ አርት ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ወጣቶችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሥለሜክአፕ አርት ምን ይላሉ? ምስል፦ DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የሜክአፕ ጥቅም እና ጉዳቱ

This browser does not support the audio element.

ሥለ ሜክ አፕ አርት የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አመለካከቶች አሏቸው ፡፡ አንዳንዶች አርቱ እራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ በየጊዜው እየተሻሻለና በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ  ሰፊ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ሜክአፕ አርት መጠቀም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ አለው ብለው ያምናሉ ፡፡ ቃል ኪዳን ማንከልክሎት እና ሲፈን አንተነህ በሀዋሳ ከተማ የሜክፕ አርት ሥልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ናቸው ፡፡ ወጣቶቹ  በሳምንት ለአምስት ቀናት በተግባር የተደገፍ የሜክ አፕ አርት ሙያን ይከታተላሉ ፡፡

ወደ ሜክአፕ አርት ሥልጠናው የገቡትም ከልጅነተ ጀምሮ ለሙያው ባላቸው ፍላጎት የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡ ቃል ኪዳን እና ሲፈን እንደሚሉት ሜክ አፕን መጠቀም ለወጣት ወይንም ለትላልቅ ሰዎች ተብሎ የሚለይ ነገር አይደለም ፡፡

ታዳጊ ወጣቶችም ሆኑ ትላልቅ ሰዎች እንደየፍላጎታቸው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የሚናገሩት ሁለቱ ወጣቶች “ ለምሳሌ ወጣቶች የተደበቀ የፊት አካሎቻቸውን በሜክአፕ አማካኝነት ውበታቸው የበለጠ እንዲወጣ እና የሰዎችን አይታ እንዲስብ ማድረግ ይችላሉ ፡፡ በተለይ በተለያዩ ዝግጅቶች አምሮና ደምቆ ለመታየት ሜክአፕ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ፡፡ ለሰዎችም ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡


በዚሁ በሀዋሳ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑት አቤጊያ ያሬድ እና ማይገነት ጠለለ በአንጻሩ ሜክአፕ አሥፈላጊ አይደለም የሚል አምነት እንዳላቸው ለ ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ገልፀዋል፡፡  

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የሜክአፕ አርት ተማሪዎች

03:21

This browser does not support the video element.

አሁን ላይ  ላይ ሜክአፕ የሚጠቀሙ ሰዎች ለቆዳ በሽታዎች እየተጋለጡ እየተመለከትንና እየሰማን ያለበት ጊዜ ነው የሚል መከራከሪያ ሀሳብ የሚያቀርቡት አቤጊያ እና ማይገነት ፊታቸውን አዘውትረው ሜክአፕ የሚሠሩ  ሰዎች  መጨረሻቸው ጥሩ ሲሆን አይስተዋልም ፡፡  

ያለ ሜክአፕ ከቤቱ የማይወጣ ሰው በራሱ አካላዊ ማንነት የማይተማመንና ሜክአፕ ካልተጠቀምኩ አላምርም የሚል ሥነ ልቦናን ይፈጥራል “ ብለዋል ፡፡


ቃል ኪዳን እና ሲፈን በበኩላቸው  አሁን ላይ የሜክአፕ አርት ጥበብ በዓለም ላይ እያደገ እንደሚገኝ ይናገራሉ ፡፡ ዘርፉን ብዙዎች ገበያ እያገኙበት መሆኑን የጠቀሱት ወጣቶቹ “ ሰዎች ሜክአፕ አርትን ብዙውን ጊዜ ከሴት ልጅ ውበት ጋር ብቻ ያያይዙታል ፡፡ ይህ ትክክል አይደለም ፡፡

አርቱ ለተለያዩ አገልግሎቶቹም ይውላል ፡፡ ለምሳሌ የፊልም እና የቲያትር ሥራዎች ላይ የሜክአፕ አርት ራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል ፡፡ በፊልሙ ሁኔታ ተዋናዮችን ሽማግሌ ለማስመሰል  ወይንም ፊታቸው የደማ ፣ የቆሰለ ፣ የጠቆረና የተጎሳቀለ ሰው ለማስመሰል የሚጠቀሙት በሜክአፕ አርት አማካኝነት ነው “ ብለዋል ፡፡


ዘገባ: ትንቢት ሰውነት/  ሸዋንግዛው ወጋየሁ  
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW