ሀዋሳ የመጣችው በጋምቤላ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ እንደሆነ የገለጸችው ናይጎኣ “ እዚህ እንደመጣሁ በመጀመሪያ አካባቢ ሁሉም ነገር አዲስ ነበር የሆነብኝ ፡፡ አካባቢው ፣ ቋንቋ እና ባህሉ ለእኔ አዲስ ነው ፡፡ በሂደት ግን ሁሉን ነገር እየለመድኩ መጣው ፡፡ አሁን ላይ የትምህርት ቤት ጓደኞችን ማፍራት ችያለሁ “ ብላለች ፡፡
ናይጎኣ ከቤተሰቧና ከትውልድ አካባቢዋ ብትለይም አንዳንድ በሩቅ ያሉ ዘመዶቿ በገንዘብ እንደሚደግፏት ትናገራለች ፡፡ ሁኔታዎች ከቤተሰብ እንድትርቅ ቢያስገድዷትም ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች እንደምታሳልፍ የጠቀሰችው ናይጎኣ “ ከትምህርት ቤት ውጭ ባለኝ ጊዜ መጸሀፍትን አነባለሁ ፡፡ የቤት ሥራዎችን እሠራለሁ ፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማዳመጥና የቴሌቪዥን ዝግጅቶችን በመከታተል አሳልፋለሁ “ ብላለች፡፡
የመጣችበት የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ግጭቶችና ወባን የመሳሰሉ በሽታዎች እንደሚስተዋልበት የጠቀሰችው ናይጎኣ ወደፊት ወደ አካባቢዋ የመመለስ ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች “ ወደፊት ነርስ የመሆን ዓላማ አለኝ ፡፡ በዚህም ማህበረሰቡን መርዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እዛ ብዙ ሰዎች በበሽታ ይሞታሉ ፡፡ ወደዚያው ተመልሼ ነገሮችን ማስተካከል አለብኝ “ ስትል የወደፊት ዕቅዷን ገልጻለች፡፡
“ እንደእኔ ከቤተሰብ ርቀው ለሚገኙ ወጣቶች መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ “ የምትለው ናይጎኣ“ የማስተላልፈው ምክር በጣም መጎበዝ እንዳለባቸው ነው፡፡ ጠንክረው ትምህርታቸውን በመቀጠል የተሻለ ቦታ መድረስና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል “ ብላለች፡፡
#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute
ዘገባ: ሊሻን ዳኜ
ቪዲዮ:ሸዋንግዛው ወጋየሁ