1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝቋላን ከሳህላ ሰየምት የሚያገናኘው ድልድይ በወንዝ ተወሰደ 

ረቡዕ፣ ነሐሴ 13 2012

በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሁለት ወረዳዎችን የሚያገናኘው የተከዜ ተንጠልጣይ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፣ የክልሉ ባለስልጣናትና የፌደራሉ መንገዶች ባለስልጣናት ደግሞ በየፊናቸው “ድልድዩ በእኔ አይተዳደርም” እያሉ ነው፡፡

Symbolbild | Überschwemmung
ምስል picture alliance / Geoff Renner/robertharding

የብረት ድልድይ ተሰብሮ በወንዙ ከተወሰደ ሳምንት ሆነዉ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሁለት ወረዳዎችን የሚያገናኘው የተከዜ ተንጠልጣይ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፣ የክልሉ ባለስልጣናትና የፌደራሉ መንገዶች ባለስልጣናት ደግሞ በየፊናቸው “ድልድዩ በእኔ አይተዳደርም” እያሉ ነው፡፡ የሰቆጣ፣ የዝቋላና የሳህላ ሰየምት ነዋሪዎች በስልክ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወረዳ የሆኑትን ዝቋላና ሳህላ ሰየምትን የሚያገናኘው የተከዜ ተንጠልጣይ የብረት ድልድይ ተሰብሮ በወንዙ ከተወሰደ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡

በመሆኑም ነዋሪዎቹና የመንግስት ሰራተኞች የእየለት ኑሯቸውን ለመስራት መቸገራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቀዋል፡፡

በተለይ አቶ ማሩ የተባሉ የሳህላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪ በተለይ ወላዶቹንና ሌሎች ወደ ከፍተኛ ህክምና የሚላኩ ወገኖችን ወደ ህክምና ማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን፣ ነጋዴዎች ተንቀሳቅሰው መስራት እንዳልቻሉ አብራርተዋል፡፡ የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን እሸቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ለተፈጠረው ችግር በአሁኑ ሰዓት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይኖረው አመልክተው ጊዜያዊ መፍትሔ ያሉትን ግን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ድልድዩን የገነባውና በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የፌደራሉ መንገዶች ባለስልጣን ስለሆነ ጉዳዩ በዚያ በኩል የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው የዚህ ድልድይ ይጠገንልኝ ጥያቄ ካሁን በፊትም መቅረቡን አስታውሰው ሆኖም ድልድዩን የሚያስተዳድረው የክልሉ መንግስት በመሆኑ አይመለከተንም ነው ያሉት፣ ጥያቄው አግዙን ከሆነ ግን በዚያ መንገድ መጠየቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ከተከዜ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የግድቡ ውሀ በሚጨምርበት ወቅት ድልድዩ የመዋጥ ስጋት እንደነበረበትም ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊትም በስፋት ያነሱ ነበር፡፡

 ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW