ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ወገን ድርቅ በሌላው ጎርፍ ያስከተለው የአየር ሁኔታ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2016ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ደቡባዊ እና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ጎርፍን ያስከተለው ዝናብ በንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርስ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከጎርፍም ባሻገር የመሬት መንሸራተት እንዲከሰት ማድረጉ ተነግሯል። ከዚህ በተቃራኒ በሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በሰሜን ምሥራቅ አማራ ክልል የቤት እንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ያስከተለና ሰውንም የጎዳ ድርቅ መከሰቱም ተሰምቷል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ተቋም የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ እንዲህ ገጽታው የተለያየ የአየር ሁኔታ መስተዋሉ የተለመደ ነው ወይ የሚለው በቀዳሚነት ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነበር። ባለሙያው፤ «“አሁን በምንገኝበት በተለይም በጋ በምንለው ከጥቅምት እስከ ጥር ባለው ወራት በደቡብ አጋማሽ ማለትም በሶማሊ፣ ሲዳማ፣ ጉጂ፣ ቦረና እና ደቡብ ምዕራብ የአገራችን አካባቢዎች ሁለተኛ የዝናብ ወራቸው ሲሆን 45 በመቶ ዓመታዊ ዝናብ የሚያገኙት በዚህን ወቅት ነው። ይህንኑን በማስመልከትም ባለፈው ነሐሴ ወር ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ የትንበያ ማስጠንቀቂያ ይፋ አድርገን ነበር።» በማለት ሁኔታውን አብራርተዋል።
ትንበያው በሚዘጋጅበት ጊዜ ታሳቢ የሚደረጉ የተለያዩ የአየር ሁኔታ ገጽታዎች እንዳሉ ነው ባለሙያው የሚናገሩት። «የአየር ሁኔታ ገጽታ በአንድ አገር ወይም በአንድ አህጉር ብቻ የሚወሰን አይደለም። በአየር ውስጥ እና በውኃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በኛ አገር በእያንዳንዱ ወቅት በሚኖረው የዝናብ መጠንና ስርጭት ላይ አዎንታዊም አሉታዊም ተጽእኖ ያሳድራሉ። እነዚህ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ከግንዛቤ ውስጥ ገብተው ትንቢያው ይዘጋጃል።»
አክለውም ለምሳሌ የምሥራቅ እና መካከለኛ ፓሲፊክ ውቂያኖስ ከመደበና በላይ መሞቅ እንዲሁም ሰሜናዊ እና ምዕራባዊ የሕንድ ውቂያኖስ ከመደበኛ በላይ የመሞቅ አዝማሚያ ሲያሳይ በአገራችን ደቡባዊ አጋማሽ ከመደኛ በላይ ዝናብ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ይህ ደግሞ በደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለተከሰተው ቅጽበታዊ ጎርፍም ጭምር ምክንያት ነው ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ፣ አማራ.፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር እና ምሥራቅ እንዲሁም መካከለኛ ኦሮሚያ አካባቢዎችም ወቅቱን ያልጠበቀ የዝናብ መጠን ሊኖር እንደሚችል አስቀድሞ ትንበያው መኖሩን ዶ/ር አሳምነው ያስረዳሉ። በያዝነው ጥቅምት ወር በእነዚህ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ነው ያመለከቱት። ይህ ደግሞ በምርታማነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊና አዎንታዊ ሚናዎች ይኖሩታ።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የበጋ የዝናብ ወቅት ዝናብ የማግኛ ጊዜያቸው ላልሆነው እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ ላሉ አከባቢዎች ደግሞ መሰል ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት አይጠበቅም። እንደውም በሰሜን ምሥራቃዊ አማራ ክልል አካባቢዎች ለተፈጠረው የዝናብ አጥረት ሁኔታም ምክንያት ያሉትን አስቀመጥዋል። «ክረምት ላይ ኤልኒኖ በሚፈጠርበት ጊዜ በተለይም ሰሜን የአገራችን አካባቢዎች ለዝናብ እጥረት ይዳረጋል። ውቅያኖሱ እየሞቀ በሄደ ቁጥር የዝናብ ወቅቱ ቶሎ ይቋረጣል በነዚህ አከባቢዎች። በምሥራቅ አማራ ላይ የዝናብ እጥረት የተከሰተውም ከዚሁ አኳያ ነው።» በደቡብ ኢትዮጵያ የባሮ እና ኦሞ ወንዞች ሙላትን፤ በተለያዩ አካባቢዎች ደግሞ የመሬት ማንሸራተትን ያስከተለው ዝናብ በሰዎች መደበኛ ሕይወት ላይ ቀውስ ማስከተሉን ከሰሙኑ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ