1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የሀሰት መረጃን እንደ ፖለቲካ ስልት፤ በዲጅታል መድረኮች

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017

ከ80 በላይ በሆኑ ሀገራት መረጃ በመስብሰብ የኦክስፎርድ የበይነመረብ ተቋም በመገናኛ ብዙሃን መረጃ ማዛባት ላይ የሰራው የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው ፤የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የህዝብ አስተያየትን በመጠምዘዝ በዓለም ላይ ለዲሞክራሲ ስርዓቶች ስጋት እየሆኑ መጥተዋል።

Südafrika Smartphone Social Media
ምስል imago images/Pond5 Images

የሀሰት መረጃን እንደ ፖለቲካ ስልት፤ በዲጅታል መድረኮች

This browser does not support the audio element.

ሬዲዮ፣ ጋዜጦች፣ ቴሌቪዥን እና መጽሔቶችን የመሳሰሉ  የተለመዱት የመገናኛ ብዙሃን በበይነመረብ እና በዲጂታል የመገናኛ ብዙሃን ዕድገት ተፅዕኖ ስር ከመውደቃቸው በፊት፤ ፖለቲካ የሚካሄደው ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ነበር።በተለመዱት የመገናኛ ብዙሃን ዘመን ፣ ፖለቲከኞች  የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማራመድ መራጮችን ለማሳመን አሳማኝ የንግግር ችሎታዎች ወሳኝ ተደርገው ይታዩ ነበር። ከአሥርተ ዓመታት በፊት፣ የተከታዮችን ቀልብ ለመያዝ  ወይም ተጽዕኖ ለማሳደር የቃል ንግግርን በብልህነት መጠቀም ትልቅ ጉዳይ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት  የፖለቲካ ዘመቻዎች ስኬት ቁልፍ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ሆነዋል።ከጎርጎሪያኑ 2014 እስከ 2022 ባሉት ጊዚያት በኢትዮጵያ  የተዛባ የበይነመረብ መረጃ ያለውን ሚና የሚመረምር መፅሃፍ  በመፃፍ ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በፈቃዱ ሀይሉ፤እንደሚለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወደ መድረኩ ሲመጡ አፈናን በማስቀረት አወንታዊ ሚና ያላቸው ቢመስሉም እንደሚጠበቀው አልሆነም።

የተዛባ መረጃ የምዕራቡን ዓለም ተቋማትም ሳይቀር እያናጋ ነው

ይህም በጠንካራ  የዲሞክራሲ አለት ላይ  የተገነባነው የሚባለውን  የምዕራቡ ዓለም ተቋማትም ሳይቀር እያናጋ ነው።የሚለው በፈቃዱ ለዚህም ትራምፕ በምርጫ ተሸንፈው በነበረበት ወቅት ደጋፊዎቻቸው ካፒቶል ድረስ በመሄድ ያደረሱትን ሁከት በምሳሌነት  ይጠቅሳል።ከዚህ በተጨማሪ በምዕራቡ ዓለምየቀኝ ዘመም ብርተኝነት እና አክራሪነትም ፖለቲካ እያንሰራራ መምጣትም አንዱ ፈተና መሆኑን ያስረዳል።ያም ሆኖ የማይካዱ ጥቅሞች አሉት።

በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም ከ80 በላይ በሆኑ ሀገራት መረጃ በመስብሰብ የኦክስፎርድ የበይነመረብ ተቋም  በመገናኛ ብዙሃን መረጃ ማዛባት ላይ የሰራው የዳሰሳ  ጥናት እንዳመለከተው ፤የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የህዝብ አስተያየትን በመጠምዘዝ በዓለም ላይ ለዲሞክራሲ ስርዓቶች ስጋት እየሆኑ መጥተዋል።
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚደረጉ የተደራጁ የማታለል ዘመቻዎች ጥናቱ በተካሄደባቸው  81 አገሮች ውስጥ ተገኝተዋል፣። ይህም 70 በሚሆኑት ሀገራት በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም ከነበረው ጋር ሲነፃጸር በአንድ አመት ውስጥ 15% ጨምሯል።መንግስታት፣ የህዝብ ግንኙነት ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳሳቱ መረጃዎችን በኢንዱስትሪ ደረጃ እያሰራጩ መሆኑን  ጥናቱ  አመልክቷል።በጥናቱ ከተካተቱ ሀገራት ከ93 በመቶ በላይ በሚሆኑት  (76 ከ 81) የሀሰት መረጃን ህዝብን ለማሳመን እንደ ፖለቲካ ስልት መመልከት የተለመደ መሆኑን ጥናቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያም የተዛቡ መረጃዎች ለፖለቲካ መሳሪያ መሆናቸውን በፈቃዱ በምርምር  ስራው መመልከቱን ገልጿል።

ሐሰተኛ መረጃዎች በእጅ ስልኮች አማካኝነት በቀላሉ ይቀናበራሉ፤ ይሰራጫሉምምስል Jonathan Raa/NurPhoto/picture alliance

በዲጅታል መድረኮች መንግስታት የተሻለ ተጠቃሚዎች ናቸው

በኢትዮጵያ በ2018 ዓ/ም የመጣው  የፖለቲካ ለውጥ በአብዛኛው የተመራው በበይነመረብ በተለይበማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የነበረ ሲሆን፤ከድህረ ኢህአዲግ በኋላም የበይነመረብ መረጃ  በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖው ቀጥሏል።ነገር ግን የበይነመረብ የተዛባ እና የሀሰት መረጃ  በዚያው ልክ በመጨመሩ ይነገራል።ይህም በተቃውሞ ጊዜ እንዲሁ የታለፉት የተዛቡ መረጃዎች ቆይተው በሀገሪቱ ቀውስ  ማስከተላቸውን ገልጿል።
እነዚህን ዲጅታል መድረኮች መንግስት፣የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣የስቪል ማህበረሰቦች እና ግለሰቦች  የሚጠቀሙ  ቢሆንም፤ የበለጠ  ሀብት እና የሰው ሀይል ያለው የበለጠ ይጠቀምበታል። በኢትዮጵያ አንፃር ደግሞ የበለጠ ሀብት ያለው መንግስት በመሆኑ  በሰፊው ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።ይህም የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።
በኢትዮጵያ ከመንግስት ባሻገር የመንግስት ተችዎችም ተመሳሳይ መንገድ መከተላቸውን ያስረዳል።

በዴሞክራሲ እና በጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች

ይህ መሰሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጭ የመረጃ እና የመረጃ ምህዳር መዛባትእየጨመረ መምጣት ደግሞ በፈቃዱ እንደሚለው በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በሀገር ሰላም እና በጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት መድረኩን በሃላፊነት መጠቀም አንዱ መፍትሄ መሆኑን ገልጿል።በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት መድረኩን በሃላፊነት መጠቀም አንዱ
መፍትሄ መሆኑን ገልጿል።
የመረጃ አረዳድን የሚያሳድጉ ትምህርቶችን በትምህርት ተቋማት መስጠትም በረጅም ጊዜ ሌላው የረዝም ጊዜ መፍትሄ መሆኑን ጠቁሟል።መንግስትን የራሱን  መረጃዎችን ለሴራ ትንታኔ እንዳይጋለጡ ግልፅ መረጃ ማቅረብም ጠቃሚ መሆኑን አመልክቷል።ያ ካልሆነ ግን የተዛባ መረጃ የሚያደርሰው ጉዳይ የሚቀጥል ነው ይላል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕከሉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW