ዕድሜው በአንድ ዓመት የተራዘመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተስፋ እና ሥጋት
ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን «የነፃነት፣ የመለየት እና ሀገር የመመሥረት ጥያቄዎች» በአጀንዳነት ቢቀርቡለት እንደማያስተናግድ አስታወቀ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜው ለአንድ ዓመት የተራዘመለት ኮሚሽን፤ ሥራውን የሚሠራው በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሥራውን ከዚሁ ማዕቀፍ ሳይወጣ እንደሚያከናውን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከ«ቁጥጥሩ ውጪ የሆኑ ነገሮች» መኖራቸውንና አስቻይ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ተጨማሪ በተሰጠው ጊዜ ሥራውን ለመጨረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጿል። ሆኖም ግን አሁንም ሥራው «በትክክል በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልቃል ለማለት ያስቸግራል» ሲሉ የሥራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
ከሀገረ መንግሥቱ ወጣ ያሉ ጥያቄዎች በአጀንዳነት አይስተናገዱም
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን «ዐበይት» ያላቸውን የሦስት ዓመታት ሥራዎቹን ዛሬ ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ካቀረበ በኋላ ከጋዜጠኞች ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል ከታሰበው በላይ የተለጠ ሀሳብ በአጀንዳነት ቢቀርብለት በምን መልኩ ምላሽ ይሰጣል የሚለው ይገኝበታል።
የተቋሙ ዋና የሥራ ኃላፊ - ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ እንዲህ ያለው ጥያቄ ቢቀርብ «የማይስተናገድ» ነው በማለት መልሰዋል። «የሀገር መመሥረት ጥያቄ ወጣ ባለ መልኩ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆነ ካለ ወደ አጀንዳ የመቅረቡ ጥያቄ አጠያያቂ ነው የሚሆነው። ስለነፃነት ጥያቄዎች፣ ወይም ስለመለየት የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አያስተናግድም» [ኮሚሽኑ] ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት ገብረ ሥላሴ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ኮሚሽኑ «ሕዝብን ሲያመካክር እና ሲያወያይ የሰበሰባቸውን ግን ሀገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ የማይገቡ ያሏቸውን ገዳዮች እንጥላቸዋለን ማለት አይደለም» ብለዋል። እነዚያን አጀንዳዎች «ለሚመለከታቸው ለክልላዊ መንግሥታትም ሆነ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምናስረክብ ይሆናል» ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ውክልና ባይኖርም የኢትዮጵያ ሕዝብን ይወክላል - ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ የኮሚሽኑ ሥራ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አልተጀመረም ተብሏል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ተወካዮች የሌሉበት መሆኑ ተጠቅሶ ይህ ለሥራቸው እንቅፋት አይሆንም ወይ በሚል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፤ ምክር ቤቱ ሌሎች ብዙ አዋጆችንም ማጽደቁን በመጥቀስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ይወክላል የሚል ላሽ ሰጥተዋል።
«ትግራይ [ክልል] ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ጊዜ በጣም በርካታ አዋጆች ወጥተዋል። ይህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመው እነሱ [ትግራይ ክልል] ጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው። ይህንን ከእነሱም ጋር ስንነጋገር «አዎ ከአሁን በፊት በምክክሩ አላመንበትም ነበር፣ ነገር ግን በኋላ ስናየው እኛ በዚያ ሂደት ውስጥ የወጡ አዋጆችን የፌዴራል መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን ያስደረጋቸውን አዋጆች በሙሉ እኛ እየተጠቀምንባቸው ነው። ስለዚህ የምክክሩን ሂደት እንቀበላለን' ብለው ራሳቸው ርዕሠ መሥተዳድሩ ባሉበት በዚህ ላይ ተነጋግረናል። ስለዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያን ነው የሚወክለው በአሁኑ ሰዓት» ብለዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ አማራ ክልል አንድ የታጣቂ ክንፍ አግኝተው እንደነበር አረጋግጠዋል
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ገና ያልተጀመረበት እና አስከፊ ቀውስ ውስጥ ያለው አማራ ክልል ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችን በተመለከተ «የፋኖ ታጣቂዎችን አግኝቻለሁ ብለዋል፣ ሊከፋፍሉን ይፈልጋሉ» የሚል ስሞታ እንደሚቀርብባቸው የገለፁት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን «ማንንም መከፋፈል ጭራሽ አይፈልግም» ብለዋል።
ያም ሆኖ ግን አማራ ክልል ውስጥ ያለ አንድ ታጣቂ ቡድን ማግኘታቸውን አልሸሸጉም። ያገኙትን አካል ማንነት ግን በስም አልጠቀሱም። አክለውም እዚያው ክልል ውስጥ አንድ የታጣቂ ቡድን መሪ ግለሰብንም በተደጋጋሚ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
«እኔ ፋኖ መሆናቸውንም አላውቅም። አንድ ታጣቂ ቡድን - አዎ ራሳቸው ደውለውልኝ አነጋግረውኝ የምክክር ኮሚሽኑን ሥራ ተገንዝበናል፤ ገለልተኛ መሆኑን ተገንዝበናል፣ በዚህ መሠረት አጀንዳችንን ለእናንተ አቅርበን ወደ ውይይት የሚቀርብልን ከሆነ፣ መሣሪያችንን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን የሚል ጥያቄ በቀጥታ ለእኔ በግል ቀርቦልኛል - ይህን ሰውዬ በተደጋጋሚ አግኝቻቸዋለሁ» ብለዋል።
የኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራዎች በጊዜው ይጠናቀቁ ይሆን?
ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተለይተው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ለአሥፈፃሚው አካል እና ለሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ በአዋጁ ተጠቅሷል። ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት ገብረ ሥላሴ «እኛ እምነታችን እነዚህ ውሳኔዎች በሕዝቦች ተሰብስበው ከወጡ በኋላ የመጀመርያ ሥራችን ሕዝብ የወሰናቸውን ጉዳዮች ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው» ብለዋል። ታጣቂዎችና ከሂደቱ ውጪ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መምጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ከኮሚሽኑ «ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች» አሉ ብለዋል። በዚህ ምክንያት ሥራው «በትክክል በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልቃል ለማለት ያስቸግራል» ሲሉ ተደምጠዋል።
በዛሬው መግለጫ 57 የፖለቲካ ድርጅቶች ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እየሠሩ ስለመሆኑ፣ በ10 ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከ1,260 በላይ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ መቅረባቸው፣ ኮሚሽኑ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ሥራዎቹን በተጨመረለት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ