የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት ተራዘመ
ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2017
ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት በጥሩ ፈጽሟል የሚሉ በዛ ያሉ አስተያየቶች የተደመጡበት የምክር ቤቱ ውሎ ከአካታችነት፣ ከገለልተኝነት እንዲሁም ወደ ትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡት አካላትን ወደ ምክክሩ በመሳብ ሂደት ችግሮች እንዳሉበትም ትችት ቀርቦበታል። በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ 288 የምክር ቤት አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን በሦስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።
በምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎች
በአወንታም በአሉታም፣ በተስፋም፣ በሥጋትም፣ በድጋፍም፣ በተቃውሞም ውስጥ ያለፉት ሦስት ዓመታትን በሥራ ላይ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ተግባራትን፣ የአጀንዳ መለየት እና ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራዎችን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ስለማጠናቀቁ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል። በአማራ እና ትግራይ ክልሎች እንደሌሎች አካባቢዎች ሥራቸውን በትክክል ለመፈፀም መቸገራቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ዝርዝር ሥራቸውን ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ «ሥራችንን ጨርሰን ነው እዚህ የተገኘነው» በማለት የቻሉትን ሁሉ መሥራታቸውን ገልፀዋል።
ይህንን ተከትሎ በነበረው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ በአብዛኛው የኮሚሽኑን ሥራ የሚደግፉ አስተያየቶች ተንፀባርቀዋል። የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑ አንድ የምክር ቤት አባል በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ኮሚሽኑ የአካታችነት፣ ግልጽና የጋራ ግብ ያለው ስለመሆኑ፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስን፣ የፀጥታ፣ የሰላም እና የተረጋጋ ሁኔታ አለመኖርን በመጥቀስ ኮሚሽኑ ደካማ አፈፃፀም ነበረው ብለዋል።
«አሁን ባለው ሁኔታ አማራ ክልል ሕዝብ ከፍተኛ የመንፈስ ሕመም ውስጥ ገብቷል። ከጦርነት ያላገገመ ሕዝብ ነው። ከክልሉ ውጪ ያለው አማራ ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት እስከ ዛሬም ባላቆመ መንገድ የማንነት ተኮር ተጠቂ ሆኗል። ስለዚህ ሀሳቡን የሚገልጽበት አስቻይ ሁኔታ የለም።»
ሌላ አንድ የምክር ቤት አባል በእሥር ላይ ሆነው ያልተፈረደባቸው የጊዜ ቀጠሮ እሥረኞች ጉዳይ መላ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም ከዚህ አንጻር ጥያቄ ቀርቦበታል።
ኮሚሽኑ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነትም በአወንታም በአሉታም በምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ ተንፀባርቆበታል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያለው ችግር መፈታት እንዳለበት ተደጋግሞ ተጠይቋል
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ይህንን ሥራ ማከናወን ፈታኝ መሆኑን የገለፁ የምክር ቤት አባላት፣ ጉዳዩን ደጋግመው ባማንሳት መፍትሔ ያሻዋል ብለዋል። ኮሚሽኑ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በሕወሓት መሳሳብ ምክንያት ሥራውን በትግራይ ክልል ማከናወን እንዳልቻለ ቢገልጽም የትግራይ ሕዝብም አጀንዳዎቹን ሊያቀርብ፣ ሊወያይም ይገባል፣ ይህንን ማድረግ ነበረበት የሚል ትችት ከአንድ የምክር ቤት አባል ቀርቦበታል።
«አካታች ማለት ሁሉን አቀፍ ፣ ሁሉንም አካል የሚያካትት መሆን አለበት። የትግራይ ሕዝብ ግን በሽግግር መንግሥት ነው እየተመራ ያለው እና ሕዝቡ መወያየት አለበት። አጀንዳውን ማቅረብ አለበት።»
ኮሚሽኑ ከምክክር ሂደቱ ውጪ የሆኑት ወደ መድረኩ ሊመጡ ይገባል ብሏል
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኃላፊ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተቋሙ በተሰጠው ተጨማሪ አንድ የሥራ ዓመት ሥራቸውን ለማጠናቀቅ እንደሚንቀሳቀሱ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
«አሁንም ውስጣዊ ጫና የለም ማለት አይደለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ውይይቱ መምጣት አለባቸው። የታጠቁ ኃይሎች ወደ ምክክሩ መምጣት አለባቸው። እነዚህ በየደረጃው መቀረፍ አለባቸው።»
በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በተለይ ከተቃዋሚው አብን አባል ለኮሚሽኑ በመንግሥት አስቻይ ሁኔታ አልተፈጠረም በሚል ለቀረበው ጠንከር ያለ ትችት ምላሽ ሰጥተዋል። ልንፈታ እየሠራን ያለነው የ50 እና 60 ዓመታት ችግሮችን ነው በማለት ጉዳዩ ከመንግሥትም፣ ከፓርቲም በላይ የሆነ የጋራ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ ሰፋ ባለ ሁኔታ ሊታይ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ