የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አሳሳቢነት
ረቡዕ፣ መስከረም 21 2018
የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ "ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው" - የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት
የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ "የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ሙሉ በሙሉ ባያሟላም" ያንን ለማድረግ "ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው" ሲል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ያወጣው ዓመታዊ የሀገራት የዘርፍ ሪፖርት አመለከተ። መንግሥት ካለፈው የሪፖርት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በጎ ጥረቶችን አሳይቷል ያለው ይህ ኢትዮጵያን የተመለከተው ዝርዝር ሰነድ በዚህ ምክንያት "ኢትዮጵያ በደረጃ 2 ላይ ትገኛለች" ብሏል። በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች ላይ ክስ ማቅረብን እና ጥፋተኛ ማድረግን ጨምሮ የመንግሥት ሕግን የማስከበር እንዱሁም ሕግን የማውጣት ጥረቶች መጨመርን ለዚህ ማሳያ አድርጎ ጠቅሷል። ሪፖርቱ ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል "በውጊያም ይሁን በድጋፍ ሚናዎች ሕፃናትን ለሕገ- ወጥ ምልመላ ወይም ለወታደርነት መያዝ ወይም ማሰርን ማቆም" ይገባል የሚለው ይገኝበታል።
በሪፖርቱ የተዘረዘሩ ጭብጦች ምን ምን ናቸው?
የኢትዮጵያ መንግሥት የሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ጠቋሚዎችን ለማጣራት ጥረቱን ጨምሯል ያለው የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ ሪፖርት ተጎጂዎችን ለመለየት የተደረገው ሥራ፣ በወንጀል ምርመራ ያለውን ትብብር ለማሳለጥ አዲስ የሠራተኛ ቁጥጥር መመሪያ ማዘጋጀቱን እና ሌሎች አወንታዊ ርምጃዎችን ጠቅሶ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ "የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ሙሉ በሙሉ ባያሟላም" ያንን ለማድረግ "ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው" በማለት የደመደመው።
በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሙያ አተያየት
ይህንን ሪፖርት በሚመለከት አስተያየት የጠየቅናቸው "ንጋት ግሎባል ኢኒሽየቲቭ" የሚባል በዘርፉ ላይ የሚሠራ ድርጅት መሥራች እና ኃላፊ አቶ ዳንኤል መለሰ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ በኩል ችግሩን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት "እውቅና ሰጥቶታል ማለት ይቻላል" ብለዋል።
"ደረጃ ሁለት የሚባለው ደረጃ መጥፎ የሚባል ደረጃ አይደለም። በሰው የመነገድ ወንጀል መንግሥት ያስቀጣቸው የሕግ ጉዳዮች እና ጉዳዩን ለመከላከል ያወጣቸው ሕጎች፣ የፖለቲካ ፈቃዱ፣ በርካታ ጉዳዮች ታይተው ነው ይህ ደረጃ የሚወጣው። በጣም ቆንጆ የሚሆነው ደረጃ አንድ ላይ ብንሆን ነበር።"
አቶ ዳንኤል መለሰ እንደሚሉት "የሰዎች ዝውውር የሚቀር ጉዳይ አይደለም።" "አሁን ባለው ኹኔታ ወደ መካከለኛው ምስራቅም ወደ ደቡብ ምስራቅ ኤስያም የሚደረጉ [ሕገ-ወጥ] ጉዞዎች አሉ" ሲሉም ችግሩን ለመቅረፍ አሁንም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መመልከታቸውን ገልፀዋል።
ዋና ዋና ገፊ ምክንያቶችን የተጠየቁት ባለሙያው "ኢኮኖሚ" ወይም በቂ የሥራ ዕድል አለመኖር አንዱ መሠረታዊ ችግር ሲሆን፣ "ወጣቶች ዉጪ ሀገር ሄደው ለመሥራት የሚደፍሯቸውን ሥራዎች እዚህ ለመድፈር አለመሞከር" ሌላኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ለሕገ ወጥ አማራጮች በር የሚከፍቱ የተንዛዙ አሠራሮች መኖር እና መንግሥት ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ውል የፈረመባቸው ሀገራት ቁጥር ሰባት ብቻ መሆናቸውም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አሳሳቢነት
የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው ሪፖርት የሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩ ሴቶችን በቤት ሠራተኝነት እና በወሲብ ንግድ ወንዶችን በጉልበት ብዝበዛ፣ በተለይ በባህላዊ ሽመና፣ በግንባታ፣ በግብርና፣ በግዳጅ ልመና እና በጎዳና ንግድ ላይ እንዲሰማሩ ማስገደዱን ዘርዝሯል።
ሪፖርቱ ካስቀመጣቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል በውጊያም ሆነ በድጋፍ ተግባር ላይ ጨምሮ ሕጻናትን በሕገ-ወጥ መንገድ ለመመልመል ወይም እንደ ወታደርነት ለመጠቀም ማፈንን ወይም ማሰርን ማቆይ ይገባል የሚለው ይገኝበታል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን አጥብቆ በመመርመር ለሕግ ማቅረብ፣ እሥርን ጨምሮ በቂ ቅጣት መጣል፣ ስልጠናን ማስፋት፣ ለተጎጂዎች ተገቢ እንክብካቤ ማድረስ፣ ለባህር ማዶ ተጓዥ ሠራተኞች የቅድመ-ጉዞ ስልጠና መስጠት፣ የመዳረሻ ሀገሮች ጋር ተጨማሪ የሁለትዮሽ የሥራ ስምምነቶችን መፈረም የሚሉትም ይገኙበታል። የሀገር ውስጥ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር በዚያው ልክ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።
"ዘመድ ጋር በመላክ፣ በጓደኞች ትውውቅ ልጆች በከፍተኛ ኹኔታ ከተማ እና ከተማ ቀመስ ወደሆኑ አካባቢዎች ይመጣሉ። ስለዚህ የትምህርት ዕድል አይሰጣቸውም፤ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ሆነው ይቀራሉ። ጉዳዩ [ችግሩ] በጣም ከፍተኛ ነው።"
በአስተዳደር አካላት የሚፈፀሙ ሌሎች አባባሽ ችግሮች
ከሀገር ውጭ በችግር ላይ የሚገኙ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን ለመመለስ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የተደረጉ ጥረቶችን በአወንታ የጠቀሰው የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ ሪፖርት "በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀሎች ውስጥ ሙስና እና ግልጽ ተባባሪነት አሁንም አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው" ብሏል።
"በፖሊስ፣ በኢሚግሬሽን ባለሙያዎች እና በፍትሕ ባለሥልጣናት መካከል የሙስና ሪፖርቶች መገኘት፣ ጉቦ መጠየቅ እና የተጭበረበሩ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች ምቹ ሁኔታን የመፍጠር" ክስተት መስተዋሉን ጠቅሶ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ተሽከርካሪን ተጠቅመው ሕገ- ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በድንበር ሲያጓጉዙ የተገኙ ስምንት ወታደራዊ ባለሥልጣናት እና አንድ ፖሊስ ተከሰው የስምንት ዓመት ከ5 ወር እሥራት እና የገንዘብ ቅጣት" እንደተበየነባቸው ማሳያ ጠቅሷል።
በአሜሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ ብያኔ መሠረት "ሰዎችን ማዘዋወር" ማለት ሰዎችን በኃይል፣ በማጭበርበር ወይም በማስገደድ እንደ የግዳጅ ሥራ፣ ወሲባዊ ብዝበዛ ወይም ባርነት መሰል ተግባራትን በማሠራት የመበዝበዝ ወንጀል ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ